ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢትዮጵያውያን አይሁዶች ላይ በተሳለቁ መምህራን ምክንያት ሚኒስትሩ ይቅርታ ጠየቁ
የእስራኤል የትምህርት ሚኒስትር በመምህሮቻቸው ዘረኛ በሆነ መልዕክት መሳለቂያ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ቤተ እስራኤላውያን ሴት ተማሪዎችን ይቅርታ ጠየቁ።
መምህራኑ ለትምህርታዊ ጉዞ ሲባል በተከፈተ የዋትስአፕ የመልዕክት መጋሪያ ቡድን ላይ ነበር በኢትዮጵያውኑ በቤተ እስራኤላውያን ሴት ተማሪዎች ላይ የተሳለቁት።
ሴት ተማሪዎቹ መምህራኖቻቸው “ጥቁር ትምህርታዊ ጉዞ” በሚል በከፈቱት የዋትስአፕ ቡድን ላይ አንዳቸው ለሌላኛቸው መልዕክት ሲለዋወጡ በድንገት ነበር ያገኟቸው።
ከቤተ እስራኤላውያኑ ተማሪዎች መካከል አንዷ ይህንን የመልዕክት ልውውጥ ከአንድ መምህር ጀርባ ሆና በቪዲዮ ቀርጻ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መምህራኑን “አሳፋሪዎች” በማለት በማሰራጨቷ ነው ይፋ የሆነው።
ይህንንም ተከትሎ የእስራኤል ትምህርት ሚኒስትር ዮዋን ኪች በመምህራኑ ድርጊት ማዘናቸውን ገልጸው ተማሪዎቹን በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል።
ይህንን ድርጊት ተከትሎም መምህራኑ ከሥራቸው የታገዱ ሲሆን፣ ክስተቱ ላይ ምርመራ እየተደረገ ነው።
በአሁኑ ወቅት 150,000 የሚደርሱ ከኢትዮጵያ የሄዱ ቤተ እስራኤላውያን በአገሪቱ ውስጥ ይገኛሉ። ለመጀመሪያ ጊዜ ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ቤተ እስራኤላውያን በ1980ዎቹ (እአአ) በሞሳድ አማካይነት ነበር በምስጢራዊ ዘመቻ የተወሰዱት።
ምንም እንኳን ባለፉት ዓመታት መሻሻሎች ቢታዩም ኢትዮጵያውያን አይሁዶች ወደ እስራኤል ከተወሰዱ በኋላ ከቀሪው የአገሪቱ ማኅበረሰብ ጋር ለመቀላቀል ከባድ ፈተና ገጥሟቸዋል። ከፍተኛ መጠን ያላቸውም ሥራ አጥ ሲሆኑ፣ በርካቶች በድህነት ውስጥ መድልዎ እየገጠማቸው መሆኑ ሲዘገብ ቆይቷል።
ባለፈው ሳምንት ሰኞ በደቡባዊ እሰራኤል ኔቲቮት ውስጥ የሚገኘው ሃይማኖታዊ ሁለተኛ ደረጃ ቤት ተማሪዎች እና መምህራን ለሦስት ቀናት የሚቆይ ትምህርታዊ ጉዞ አዘጋጅተው በነበረበት ጊዜ ነው ይህ ዘረኝነት የተቀላቀለበት ሁኔታ የተከሰተው።
በዚህ ወቅትም ከአንዷ መምህር ጀርባ ተቀምጠው የነበሩት ኢትዮጵያውያን አይሁድ ሴት ተማሪዎች መምህርቷ እነርሱን የሚንቋሽሽ አስተያየት የያዘ መልዕት ስትለዋወጥ ተመለከቱ።
አንደኛዋ ተማሪም መምህርቷ ሳታውቅ ከኋላዋ የመልዕክት ልውውጡን በቪዲዮ ለመቅረጽ ችላለች። ከዚያም መምህራኑ ሲለዋወጡ የነበረውን የመልዕክቶቹን ምስል በማያያዝ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ይፋ አድርጋዋለች።
ተማሪዋ “የእዚህ ትምህርት ቤት ‘አስተማሪዎች’፤ እንደ የኢትዮጵያ እስራኤላዊ ማኅበረሰብ አባል ይህን ያህል ወርዳችሁ በማየቴ አዝኛለሁ። መልካም መምህር ሆናችሁ ደኅንነታችን በተጠበቀበት ቦታ እንደሆንን እንዲሰማን ከማድረግ ይልቅ ተቃራኒውን ነው ያደረጋችሁት” በማለት ተማሪዋ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አስፍራለች።
ተማሪዋ ጨምራም መምህራኑ ቤተ እስራኤላውይን ተማሪዎችን የሚያንቋሽሽ የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ከፍተው በተማሪዎቻቸው ላይ ሲሳለቁ ስታይ ለማመን እንደተቸገረች ገልጻለች።
“አሳፋሪዎች ናችሁ፤ ቀጣዩን ትውልድ የምትቀርጹ አስተማሪዎች በመሆናችሁ እና የእኛ አስተማሪዎች በመሆናችሁ አፍሬአለሁ።”
በዚህ ድርጊት ውስጥ የተሳተፉት መምህራን ከሥራ የታገዱ ሲሆን ይቅርታም ጠይቀዋል።
የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህርም “በኢትዮጵያውያኑ ተማሪዎች ላይ የተፈጸመው የከፋ ድርጊት በእጅጉ አስደንጋጭ” መሆኑን ባወጡት መግለጫ ጠቅሰው “የትምህርት ቤቱ አስተዳደርም ክስተቱን በቀላሉ የማያልፈው እና ለዘረኛ አስተያየቶች ቦታ የለንም” ብለዋል።
ጨምረውም ይህን ሁኔታን በተመለከተ “ማድረግ በምንችለው ሁሉ ጠንካራ እርምጃ እንወስዳለን” በማለት በተማሪዎቹ ላይ በተፈጸመው ነገር መዘናቸውን ገልጸዋል።