የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ከሴት ልጃቸው ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ በአደባባይ ታዩ

ለረዥም ጊዜ ሴት ልጅ እንዳላቸው ሲወራ የቆዩት የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ለመጀመሪያ ጊዜ አብረዋት በአደባባይ ታዩ።

ስለ ኪም ሴት ልጅ እስካሁን በዝርዝር የሚታወቅ ምንም ነገር የሌለ ሲሆን፣ ስሟም ኪም ቹ-ኢ እንደሆነ ይታመናል።

ሴት ልጃቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ከአባቷ ጋር የታየችው ኪም ጆንግ ኡን ለዓመታት ከምዕራባውያን ጋር በሚወዛገቡበት የጦር መሣሪያ ፕሮግራም ሙከራ ወቅት ነው።

የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ትናንት አርብ የአገሪቱ ትልቁ ነው የተባለው አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳኤል ሙከራ በተደረገበት ሥነ ሥርዓት ላይ ነው ከሴት ልጃቸው ጋር የተገኙት።

አሜሪካ ባወገዘችው የሚሳኤል ሙከራ ላይ አባት እና ሴት ልጃቸው እጅ ለእጅ ተያይዘው ታድመው ነበር።

በዓለም ላይ እጅግ ከፍተኛ ቁጥጥር የሚደረግባትን አገር ስለሚመሩት ኪም ጆንግ ኡን የግል ሕይወት የሚታወቀው ነገር እጅግ በጣም ጥቂት ነው።

ከሴት ልጃቸው ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ የታዩትን የአባት እና ልጅን የተለያዩ ፎቶዎችን የሰሜን ኮሪያው የዜና አገልግሎት ኬሲኤንኤ አሰራጭቷል።

የኪም ጆንግ ኡን ሴት ልጅ የሆነችው ቹ-ኤ ለሕዝብ በይፋ መታየቷ ትልቅ ነገር ነው፣ ሲሉ በዋሽንግተን በሚገኘው የስቲምሰን ማዕከል የሰሜን ኮሪያ ተንታኝ የሆኑት ማይክል ማደን ይናገራሉ።

ሰሜን ኮሪያን በመምራት ከቤተሰባቸው ሦስተኛው ትውልድ የሆኑት ኪም፣ አሁንም በአገራቸው የመሪነት ሥልጣን ላይ ጠንካራ ቁጥጥር እንዳላቸው እያሳዩ መሆናቸውን ተንታኙ ያምናሉ።

ማደን እንደሚሉት ኪም ከሴት ልጃቸው ጋር መታየታቸው “አገሪቱን የሚመራው አራተኛው ትውልድ ከእሳቸው የቤተሰብ ግንድ እንደሚመጣ ለማሳየትም ሊሆን ይችላል” ብለዋል ለቢቢሲ።

መሪው ከልጃቸው ጋር የታዩት “በኪም እና በአመራሩ ከፍተኛ ሰዎች መካከል ባለፈው ዓመት ግጭት መኖሩን የሚያመለክት ሪፖርት መውጣቱን ተከትሎ ነው” ይላሉ።

በዚህም ኪም ለተቀናቃኞቻቸው ማስተላለፍ የፈለጉት መልዕክት “የምትገዳደሩኝ ከሆነ፣ ቦታችሁን ትለቃላችሁ” የሚል ነው።

ማደን እንደሚያምኑት የኪም ሴት ልጅ በአሁኑ ወቅት ዕድሜዋ በ12 እና በ13 መካከል ነው፣ በዚህም ከአራት እና ከአምስት ዓመታት በኋላ ወደ ዩኒቨርስቲ ወይም ወደ ወታደራዊ አገልግሎት ለመግባት ትዘጋጃለች።

ቹ-ኤ በይፋ ስትታይ የአሁኑ የመጀመሪያዋ አይደለም የሚሉት በርካታ የሰሜን ኮሪያ ጉዳይን የሚከታተሉ ባለሙያዎች፣ ቹ ባለፈው መስከረም ላይ በተከበረው የአገሪቱ ብሔራዊ ቀን ክብረ በዓል ላይ በተቀረጹ ቪዲዮዎች ላይ ታይታለች።

ነገር ግን ይህ ከግምት ባለፈ ማረጋገጫ አልተገኘለትም። የሰሜን ኮሪያ ባለሥልጣናትም በቪዲዮው ላይ የታየችው የመሪው ሴት ልጅ ስለመሆኗ ምንም ዓይነት ማረጋገጫ አልሰጡም።

ኪም ጆንግ ኡን ሴት ልጅ እንዳላቸው ለመጀመሪያ ጊዜ የተገለጸው ከዘጠኝ ዓመት በፊት የቀድሞው የአሜሪካ ቅርጫት ኳስ ኮከብ ዴኒስ ሮድማን አወዛጋቢ ጉዞ ወደ ሰሜን ኮሪያ ባደረገበት ጊዜ ነው።

ሮድማን በወቅቱ ከኪም ቤተሰብ ጋር ጊዜ ማሳለፉን በመጥቅስ፣ በባሕር ዳርቻ ላይ ዘና ማለቱንና የመሪውን ሕጻን ልጅ ቹ-ኤን ማየቱን በገለጸበት ወቅት ነበር።

የሰሜን ኮሪያን ጉዳይ በቅርበት የሚከታተሉ ባለሙያዎች እንደሚያምኑት ኪም ሦስት ልጆች ያሏቸው ሲሆን፣ ሁለቱ ሴቶች አንዱ ወንድ ናቸው፤ ቹ-ኤ ደግሞ የመጀመሪያ ልጅ ናት ይላሉ።

ኪም ጆንግ ኡን ቤተሰባቸውን በሚመለከት ሁሉንም ነገር በጥብቅ ምስጢርነት የያዙ መሪ ናቸው።

ባለቤታቸው ሪ ሶል-ጁን ካገቡ በኋላ እንኳን እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ ጋብቻቸውን በምስጢር ይዘውት ቆይተዋል።