ዩኬ ኢትዮጵያን ጨምሮ 65 አገራትን ተጠቃሚ የሚያደርግ አዲስ የንግድ ማዕቀፍ ይፋ አደረገች

ዩናይትድ ኪንግደም ኢትዮጵያን ጨምሮ 65 አገራትን ተጠቃሚ የሚያደርግ አዲስ የንግድ ማዕቀፍ መረሃ ግብር መጀመሯን ይፋ አደረገች።

ከጥቂት ዓመት በፊት ከአውሮፓ ኅብረት የወጣችው ዩናይትድ ኪንግደም ያስተዋወቀችው ይህ አዲስ የንግድ ማዕቀፍ ለተጠቃሚ አገራት የንግድ መመሪያዎችን እና ቀረጥን የሚያቀል ነው ተብሏል።

በዚህ የንግድ ማዕቀፍ ተጠቃሚ የሚሆኑት 65 በማደግ ላይ ያሉ አገራት በጥቅል ወደ ዩናይትድ ኪንግደም በየዓመቱ ከሚልኩት 20 ቢሊየን ፓውንድ የሚያወጣ ምርቶቻቸው ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል።

ዛሬ ሰኞ ሰኔ 12/2015 ዓ.ም. ተግባራዊ የተደረገው ይህ አዲሱ በማደግ ላይ ያሉ አገራት የንግድ መረሃ ግብር (ዲሲቲኤስ) ሦስት ቢሊየን የሚደርሱ ዜጎች ያሏቸው ሲሆን፣ ወደ ውጭ የሚልኩትን ምርት አይነት የማስፋት እና መጠኑን ከፍ የማድረግ ፍላጎት ያላቸው ናቸው።

የዩናይትድ ኪንግደም ዓለም አቀፍ ንግድ ሚኒስትር የሆኑት ናይጀል ሃድልስተን የአገራቸውን አዲስ የንግድ መረሃ ግብር አዲስ አበባ ውስጥ ይፋ ያደረጉ ሲሆን፣ ከዚህ ማዕቀፍ ተጠቃሚ ከሚሆኑት ከግማሽ በላዩ የአፍሪካ አገራት መሆናቸው ተነግሯል።

ይህ የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የንግድ መረሃ ግብር በዓለም ላይ ካሉት ቀላሉ እና ሰፊ እድልን የሚፈጥር ነው። በዚህም ሳቢያ ታዳጊ አገራት ከጦር መሳሪያ በስተቀር ሁሉንም ዓይነት ሸቀጦች ከቀረጥ ነጻ መላክ ይችላሉ ተብሏል።

የዩኬ ዓለም አቀፍ ንግድ ሚኒስትር እንዳሉት ይህ ለታዳጊ አገራት የተዘጋጀው የንግድ ማዕቀፍ በየዓመቱ የአገሪቱ ተቋማት በተለያዩ ዓይነት ምርቶች ላይ የዋጋ ቅናሽ እንዲያገኙ በማድረግ በሚሊዮኖች ፓውንድ የሚቆጠር ገንዘብ ያድናል ተብሏል።

ብሪታኒያ ከአውሮፓ ኅብረት ከወጣች በኋላ የወጣው ይህ አዲስ የንግድ ማዕቀፍ ለ65ቱ ታዳጊ አገራት ሰፊ የንግድ ዕድልን ከመፍጠሩ ባሻገር፣ ለዩኬ የንግድ ተቋማት የዓለም አቀፍ የንግድ ዕድልን የሚፈጥር ሲሆን ለአገሪቱን ምጣኔ ሃብትም ዕድገት አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሏል።

አሜሪካ አጎዋ የተባለ ታዳጊ አገራት ከቀረጥ እና ከታሪፍ ነጻ ምርቶቻቸውን እንዲያስገቡ የሚስችል ለዓመታት የቆየ የንግድ መረሃ ግብር ስታካሂድ የቆየች ሲሆን፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ አንዳንድ አገራት ከዚህ ተጠቃሚነት ታግደዋል።

ይህ የዩናይትድ ኪንግደም አዲስ የንግድ ማዕቀፍ ይፋ የተደረገው በትግራይ ከተካሄደው ጦርነት ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ከአጎዋ ተጠቃሚነት እንድትወጣ ከተደረገ ከዓመት በኋላ ነው።

ይህ ኢትዮጵያን ጨምሮ 65 በማደግ ላይ ያሉ አገራትን ተጠቃሚ የሚያደርገው የንግድ መረሃ ግብር (ዲሲቲኤስ) ይፋ የተደረገው የዩኬ ዓለም አቀፍ የንግድ ሚኒስትር ናይጀል ሃድልስተን በኢትዮጵያ ትልቁ የሆነውን የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክን በጎበኙበት ጊዜ ነው።

ከዩናይትድ ኪንግደም ጋር 838 ሚሊዮን ፓወንድ የሚደርስ የንግድ ግንኙነት ያላት ኢትዮጵያ፣ ወደ ዩኬ ለምትልካቸው ምርቶቿ ምንም ዓይነት ታሪፍ አትከፍልም።

ዩኬ ይፋ ባደረገችው በአዲሱ የንግድ ማዕፍ ኢትዮጵያን ጨምሮ ተጠቃሚ የሚሆኑት አገራት፣ ከሌሎች አገራት የሚመጡ ግብዓቶችን በመጠቀም በማምረት የበለጠ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ተገልጿል።