ኡጋንዳ፡ “ተማሪዎቹ በአክራሪዎቹ ከመገደላቸው በፊት የወንጌል መዝሙር እየዘመሩ ነበር”

ኡጋንዳ ውስጥ ባለፈው ሳምንት አርብ በአንድ ትምህርት ቤት ላይ በተፈጸመ ዘግናኝ ጭፍጨፋ በርካታ ሕጻናት መገደላቸው ይታወሳል።

ከሟቾቹ መካከል ብዙዎቹ አዳጊዎች ናቸው።

ለዚህ ጥቃት መቀመጫውን ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ያደረገው አላይድ ዲሞክራቲክ ፎርስ ተጠያቂ ተደርጓል።

ጥቃቱ የተፈጸመበት የአዳሪ ትምህርት ቤት ሲሆን፣ አክራሪዎቹ ጥቃቱን የፈጠሙበት መንገድ ማደሪያ ክፍሎች ላይ ነዳጅ አርከፍክሎ እሳት በመለኮስ እና በገጀራ ሰውነትን በመቆራረጥ ጭምር እንደሆነ ተዘግቧል።

አንዲት ከዚህ ትምህርት ቤት ማዶ ባለ ቤት ነዋሪ የሆነች ሴት ለቢቢሲ ስዋሂሊ ያየችውን መስክራለች።

“ልጆቹ የወንጌል መዝሙር እየዘመሩ ነበር፤ ከዚያ ድንገት ኡኡታ ተሰማ” ብላለች።

ቀጣዩ ዝርዝር ዘገባ አንዳንድ አንባቢዎች የሚረብሽ ሊሆን እንደሚቸል ቢቢሲ አስቀድሞ ማስገንዘብ ይወዳል።

ለአይኤስ ታማኝ ነው የሚባለው እስላማዊ አክራሪ ቡድን አላይድ ዲሞክራቲክ ፎርስ ነፍጥ ያነሳው ከ1990ዎቹ ጀምሮ ሲሆን፣ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ሙስሊሞችን ይጨቁናሉ በሚል ነበር ጫካ የገባው።

ይህ ቡድን የሚንቀሳቀሰው በዋናነት በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውስጥ ነው።

ፖንዱዌ ሉቢሪሃ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚገኘውም በኡጋንዳ እና በኮንጎ ድንበር አቅራቢያ ነው።

ለቢቢሲ ስዋሂሊ ምስክርነቷን የሰጠችው ሜሪ ማሲካ ከጥቃቱ ጀምሮ እንቅልፍ መተኛት እንዳልቻለች ተናግራለች።

“ተማሪዎቹ ሁልጊዜ ከመተኛታቸው በፊት ይጸልያሉ፤ አርብ ዕለት የሆነው ግን ያልተለመደ ነው፤ ጸሎታቸው በድንገት ተቋረጠ” ትላለች ሜሪ ማሲካ።

ይህ የሆነው ምሽት አራት ሰዓት ላይ ነው።

አክራሪዎቹ ወደ ግቢው ገብተው ማደሪያዎቹን በእሳት እያጋዩ ሌሎችን ደግሞ በጭካኔ በገጀራ አካላቸውን ሲቆራርጡ ነበር።

እሑድ ዕለት አንድ ቤትሰብ አባት እና ልጅን የቀበረ ሲሆን፣ አባት የ47 ዓመት የትምህርት ቤቱ ዘበኛ እንዲሁም ልጃቸው የ17 ዓመቱ ማሰሬካ ኤልተን ነበር።

ይህ ቤተሰብ ሌላኛውን የሟች አባት ልጅ አስከሬን እንኳ ማግኘት አልቻሉም። ምናልባት ለመለየት እስኪያቅት ድረስ ክፉኛ በእሳት ተቃጥሎ ሊሆን ይችላል። አልያም ደግሞ ታግቶ ተወስዶ ይሆናል የሚል ግምት አለ።

አማጺያኑ ጥቃቱን ከፈጸሙ በኋላ የተወሰኑ ተማሪዎችን አግተው ወስደዋል።

ቢቢሲ በአካባቢው በተገኘበት ወቅት በድንበር አካባቢ በርካታ ወታደራዊ ኃይል እንዳለ ማስተዋል የቻለ ሲሆን፣ እንዴት አማጺያኑ ይህን የኡጋንዳ ወታደራዊ ኃይል አልፈው ጥቃት ማድረስ ቻሉ የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው።

ቢቢሲ የደረሰውን ጉዳት ለመዘገብ በስፍራው በተገኘ ጊዜ የተወሰኑ ደቂቃዎችን ፎቶ ለማንሳት ተፈቅዶለት ነበር።

በዚያ አጭር ሰዓት ታዲያ በተለይ በሴቶች ማደርያ ክፍል ውስጥ በርካታ ደም ፈሶ፣ የፈሰሰው ደም ደግሞ ወለሉን አጨቅይቶት፤ የጨቀየው ደም ደርቆ ተመልክቷል።

ከገጀራው ጥቃት ለማምለጥ ብዙዎቹ ሲሸሹ ከፍተኛ የአካል ጉዳት፣ የሰውነት መቆራረጥ እንደደረሰ መገመት ይቻላል።

የተወሰኑት የተማሪዎች ማደሪያ ክፍሎች ተቆልፈው የተገኙ ሲሆን፣ ምናልባት ታጣቂዎቹ ጥቃት እንዳያደርሱባቸው ሴት ተማሪዎቹ ከውስጥ ቆልፈዋቸው ይሆናል።

አልያም ታጣቂዎቹ ራሳቸው ሴት ተማሪዎቹን እዚያው ማደሪያ ክፍል ቆልፈውባቸው፣ ነዳጅ አርከፍክፈው እሳት ለቀውባቸው ይሆናል የሚል ግምት አለ።

በማደሪያ ክፍል አልጋዎች ራስጌ እና ግርጌ ላይ የተቆራረጠ የሰው ሥጋ ተለጣጥፎም ይታያል።

ይህ ጥቃት ምሽት አራት ሰዓት ተጀምሮ 5፡30 አካባቢ ሊገባደድ ሲል ሜሪ ማሲካ አንደኛው ጥቃት አድራሽ “ሥራው ተጠናቀቀ?” ብሎ ሲጠይቀው መስማቷን ለቢቢሲ ስዋሂሊ አስረድታለች።

“ጥቃት አድራሾቹ በስዋሂሊ ቋንቋ ነበር የሚነጋገሩት፤ ሲጨርሱ ደግሞ አላሑ አክባር (አላህ ታላቅ ነው) እያሉ ሄዱ” ብላለች።

ሜሪ ማሲካ ጨምራ፤ “ከእነሱ መካከል አንዱ ‘አሁን የሙሴቬኒን አገር አውከነዋል’ ብሎ ሲናገር ሰምቻለሁ” ትላለች።

ጥቃቱን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ ወደ ርዌንዞሪ ተራሮች በርካታ ሠራዊት እንደሚልኩ ዝተዋል።

ኡጋንዳ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚዋሰኑበት ድንበር የሚገኘው ይህ ጫካ አማጺያኑ መሽገውበታል የሚባል ነው።

“ድርጊታቸው የፈሪ በትር ነው፤ ሽብር ነው፤ ተገቢውን ቅጣት ያገኛሉ’ ብለዋል ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ።

ጥቃቱ የደረሰበት ፖንዱዌ የሚባለው አካባቢ ሙስሊሞች እና ክርስቲያኖች በሰላም የሚኖሩበት ሲሆን፣ በሟቾች የቀብር ሥርዓት ላይ በርካታ ሙስሊሞች ተገኝተው ነበር።