ደጋፊዎች ሮናልዶ በዩናይትድ የገነባውን መልካም ስም አጠልሽቷል አሉ

እግር ኳስ ተጫዋች ጎሎችን ሲያስቆጥር፣ ዋንጫዎችን ሲያነሳ እና ለክለቡ ደስታ ሲያመጣ በደጋፊዎች ልብ ውስጥ መንገሱ አያጠራጥርም።

ሮናልዶ ክለቡን የሚያጣጥል ቃለ መጠይቅ መስጠቱ በክለቡ ውስጥ የገነባውን መልካም ስም የሚያጠለሽ እንደሆነ የማንችስተር ዩናይትድ ክለብ ደጋፊዎች እየገለጹ ነው።

በዩናይትድ ታሪክ የምንግዜም ምርጥ ተጫዋቾች ተርታ እንደሚሰለፍ የሚነገርለት ሮናልዶ፤ የክለቡ ደጋፊዎች ከጎኑ እንደሚቆሙ ይናገራል።

ይህ ግን እውነት ነው? ሞርጋን ሌዊስ የተባለው የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊ በዚህ አይስማማም።

ጎል አስቆጣሪው “አብቅቶለታልም” ሲል ይገልጻል።

ተጫዋቹ ከፒርስ ሞርጋን ጋር ያደረገው ቃለ መጠይቅ የመጀመሪያ ክፍል ረቡዕ ምሽት ተላልፏል። ክለቡ “ከድቶኛል” የሚለውን ጨምሮ የተለያዩ የቃለ መጠይቆቹ አጫጭር ጉዳዮችም ቀደም ብለው ወጥተዋል።

አንዳንዶች አሁንም ሮናልዶን መደገፋቸውን ቢቀጥሉም የ24 ዓመቱ ሞርጋን ግን ክለቡ “እሱን የሚለቅበትን መንገዶች በፍጥነት መመልከት” አለበት ይላል።

“ተጫዋቹን ማስወጣት አለበን። [የእርሱ በክለቡ መቆየት] ከምንፈልገው ነገር የመጨረሻው ነው። ሮናልዶ በፍጥነት መሄድ ያለበት ይመስለኛል” ያለው ደግሞ ሃሪ ኦኮኖር ነው።

ምን ተባለ?

ሮናልዶ ዘንድሮ በክለቡ ውጤታማ ጊዜን እያሳለፈ አይገኝም።

ባለፈው ክረምት ክለቡን ለመልቀቅ ጠይቆ ነበር ሲባል ነበር። ከቶተንሃም ጋር በነበረው ጨዋታ ተቀይሬ አልገባም በማለቱም ከቡድኑ ውጭ እንዲሆን ተደርጓል።

ያለመረጋጋቱ ግን ወደ ማዕበል መቀየሩ የተረጋገጠው አጥቂው ከፒርስ ሞርጋን ጋር ያደረገው ቃለ መጠይቅ ቅንጭብጫቢ ቪዲዮዎች ብቅ ማለት ከጀመሩ በኋላ ነው።

የቃለ መጠይቁ የመጀመሪያ ክፍል ረቡዕ ሲተላለፍ ቀጣዩ ክፍል ትናንት ምሽት ለተመልካቾች ደርሷል።

ሮናልዶ በቃለ መጠይቁ ለአሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ ክብር እንደሌለው ተናግሯል። የክለቡ የቀድሞ ተጫዋቾች የሆኑትን ዋይኒ ሩኒ እና ጋሪ ኔቪልንም ተችቷል። የክለቡ ባለቤቶችም ከሮናልዶ ትችት አላመለጡም።

ክለቡን እአአ በ2005 የገዙት የግሌዘር ቤተሰብ አባላትን “ስለክለቡ ምንም አይጨነቁም” ብሏቸዋል።

ይህንን ጉዳይ ደጋፊዎቹም ለዓመታት ሲያስተጋቡት ነበር። በተደጋጋሚም የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል።

አንዳንዶች ሮናልዶ እና እጮኛው ጆርጂና ሮድሪጌዝ ልጃቸው መሞቱን ተከትሎ ሊታዘንላቸው እንደሚገባ ይጠቁማሉ።

ሃሪ እና ሞርጋንም በዚህ ይስማማሉ። በክለቡ ባለቤቶች ጉዳይም ይስማማሉ። በአሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ ጉዳይ ግን ሮናልዶ የሰጠው አስተያየት መስመር የጣሰ ነው ይላሉ።

“ስለ ክልቡ ባለቤቶች እና የስራ አስፈጻሚዎች ዙሪያ በተናገረው አንዳንድ ጉዳዮች ትስማማለህ” ይላል ሃሪ።

ሮናልዶ “ለቴን ሃግ ክብር የለኝም” ባለበት ቅጽበት ግን ድጋፍን ያጣል።

“አሰልጣኙን ከጀርባ በዚህ መልኩ መውጋት ግን አይገባም። ማንም ከክለቡ በላይ አይደለም” ሲል ያክላል።

የመልበሻ ክፍሉ ምን ይመስላል?

የቀድሞው የማንችስተር ሲቲ ተከላካይ ኔዱም ኦኑሃ ለቢቢሲ ኒውስቢት እንደገለጸው ተጫዋቾች አሁንም ሮናልዶን እንደ አርዓያ ይመለከቱታል።

“እንደ ግለሰብ አሁንም የእሱን እንቅስቃሴዎች ይከታተላሉ። ያስቆጠራቸውን በመቶዎች የሚቆጠሩ ጎሎች ይመለከታሉ። ድሎቹን እና ስኬታማ ተጫዋች የሆነባቸውን መንገዶች ይመለከታሉ” ብሏል።

“አንዳንድ ነገሮች በተለይም አሁን የሚያደርገውን ነገር አይወዱትም። 99.9 በመቶ ተጫዋቾች ይህንን ለማድረግ ቀርቶ ለማሰብ እንደማይችሉም ያውቃሉ።”

ኔዱም እንደሚለው የሚጠቅማቸው ከሆነ ተጫዋቾች መልቀቂያ የሚያስገባን ተጫዋች ይደግፋሉ።

“ከሮናልዶ አንጻር ካየነው ግን የተለየ ነው። ተራ ተጫዋች አይደለም። እሱ ከምርጥ የእግር ኳስ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው።”

“ወስኖ ይህን ቃለ መጠይቅ ስለ ክለቡ ማድረጉ. . . በዚህ ደረጃ ላለ ክለብ የተለመደ ነገር አይደለም” ሲል ይገልጻል።

የደጋፊዎችን ልብ መልሶ መግዛት ይችላል?

በዓለም ዋንጫው ምክንያት ሮናልዶ ወደ ኳታር አቅንቷል።

“ሮናልዶ ወደ ማንችስተር ዩናይትድ በድጋሚ እንዲመለስ ደጋፊዎች ህልም ነበራቸው። ይህም 10 ዓመት አስቆጥሯል” ይላል ሃሪ።

ይህን ከመሰለ ዓመታትን ከተሻገረ ግንኙነት በኋላ አጥቂው በዚህ መልኩ ስለክለቡ በመናገሩ ደጋፊዎች ይቅር የማይሉት እና የማይረሱት ጠባሳ ነው።

“ጊዜ ግን ያክማል” ሲል ያክላል። ሞርጋንም በዚህ ይስማማል።

“አሁን ስሙ ጠልሽቷል። ስሙን አበላሽቷል” ይላል ሞርጋን።

“ከሦስት ወይም አራት ዓመታት በኋላ ብጠየቅ ሌላ ነገር ልናገር እችላለሁ” ሲል ያጠናቅቃል።