የአካባቢ ጥበቃ ሳይንቲስቱ ዶክተር ተወልደ ብርሃን ገ/እግዚአብሄር አረፉ

ዶክተር ተወለደ ብርሃን

የፎቶው ባለመብት, SM

የአካባቢ ጥበቃና የሥነ ህይወት ሳይንቲስቱ ዶ/ር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሄር በ83 ዓመታቸው ትናንት መጋቢት11/2015 ዓ.ም ሌሊት ላይ ማረፋቸውን ከልጃቸው እንደሰማ በሳይንቲስቱ ህይወት ዙሪያ መጽሐፍ የጻፈው ዘነበ ወላ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ህልፈታቸውን ከልጃቸው ሮማን ተወልደ ብርሃን እንደሰማ የተናገረው ደራሲው ዶክተር ተወልደ ብርሃን ለረጅም ጊዜ የቆየ ህመም እንደነበረባቸው ገልጿል።

ዶክተር ተወልደ ብርሃን ገ/እግዚአብሄር ማን ናቸው?

የመንግሥታቱ ድርጅት የአካባቢ ጥበቃ ድረ ገጽ ያወጣው ግለ ታሪክ ዶ/ር ተወልደ ብርሃን የካቲት 12/1932 ዓ.ም በትግራይ አድዋ ከተማ አቅራቢያ መወለዳቸው ይገልጻል። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በባዮሎጂ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የወርቅ ሜዳሊያ በመሸለም ጭምር አጠናቀዋል።

በዩናይትድ ኪንግደም ስር በሚገኘው ሰሜን ዌልስ ዩኒቨርሲቲ በእጽዋት ስነ ምህዳር በዶክትሬት ዲግሪ በ1961 ተመርቀዋል። ሳይንቲስቱ የመጀመሪያ ኢትዮጵያዊ የእጽዋት ስነ ምህዳር ባለሙያም ናቸው።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በተለያዩ የአካዳሚ ደረጃዎች የሰሩት ሳይንቲስቱ ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል በነበረችበት ጊዜ የአስመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ሆነው እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ አገልግለዋል።

ከመንግሥት ለውጥ በኋላ የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ስትራቴጂ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ሆነው የሰሩት ዶክተር ተወልደ በ1987 ዓ.ም የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው ተሹመዋል።

ከአካባቢ ጥበቃና ብዝሃ ህይወት ጋር የሚያያዝ ከ30 በላይ ጥናቶችን አሳትመዋል። በተመሳሳይ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ መጽሐፍትንም ጽፈዋል።

ዶክተር ተወልደ ብርሃንና ባለቤታቸው ሱ ኤድዋርድስ

የፎቶው ባለመብት, ONE WORLD AWARD

የምስሉ መግለጫ, ዶክተር ተወልደ ብርሃንና ባለቤታቸው ሱ ኤድዋርድስ

በተጨማሪም የአካባቢ ጥበቃ ስታራቴጂ በመንደፍና በኢትዮጵያና በተቀረውን ዓለም የሥነ ህይወት ሃብቶች ላይ የሚያተኩሩ ጽሑፎችን አዘጋጅተዋል።

ሳይንቲስቱ በርካታ ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ ሽልማቶችን አግኝተዋል።

ዶክትር ተወልደ ብርሃን እንደ አውሮፓውያኑ 2000 ላይ ስዊዲን ስቶኮልም በአካባቢ ጥበቃ በነበራቸው አስተዋጽኦ አማራጭ (Alternative) የኖቤል ሽልማት የወሰዱ ሲሆን በ2006 ሲንጋፖር ላይ ‘champion of the earth’ የሚል ሽልማትን ከመንግሥታቱ ድርጅት ተበርክቶላቸዋል።

የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያው ዶክተር ተወልደ ታላላቅ አበርክቶዎች እንዳሏቸው በሳይንቲስቱ ህይወት ላይ ከሁለት አስርት አመታት በላይ የፈጀና “የምድራችን ጀግና” የሚል መጽሐፍ ያሳተመው ደራሲ ዘነበ ወላ ያስረዳል።

በብዝሃ ሕይወትና የዓለም አርሶ አደሮችን መብት ለማስከበር ያደረጉት ድርድር (community right negotiation) ከአበርከቷቸው መካከል የሚጠቀስ ነው። በተለይ በሁለተኛው ድርድር ከ1.4 ቢሊዮን በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንዳደረገ አመላክቷል።

ይህ ድርድር መነሻው የእህል ዘሮች የባለቤትነት መብት (Patent right)ጋር የሚያያዝ ነው።

"የእህል ዘር የባለቤትነት መብት የኛ ነው የሚሉ ሰዎች ተነሱ። ይኼኔ ዶክተር ተወልደ ‘ገበሬው ጠብቆ ያቆየልን ነገር ለናንተ የባለቤትነት መብት ሊሆን አይችልም’ ብሎ አሳምኖ ይህንን ውጤት አስገኝቷል” ያለው ዘነበ ነው።

በሌላ በኩል የዘረ መል ማሻሻያ በተደረገባቸው ወይም የGMO ምግቦች ያላቸውን ተጽዕኖ በተመለከተ ውጤት ያስገኘ ድርድር አድርገዋል።

ሳይንቲስቱ የዩኬ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ጨምሮ በተለያዩ መድረኮች በመገኘት አካባቢ ጥበቃና ሥነ ህይወት የተመለከቱ ንግግሮችን አድርገዋል።

ባለቤታቸው ሱ ኤድዋርድስ በትውልድ እንግሊዛዊ ቢሆኑም በዜግነት ኢትዮጵያዊ ናቸው። “ዳግም ተጠምቃ የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን እምነት ተከትላ እዚሁ አገር ውስጥ እንዳረፉ” ደራሲ ዘነበ ወላ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ከባለቤታቸው ሶስት ልጆች የወለዱት ዶክተር ተወልደ ብርሃን የተቸገሩ ልጆችንም ያሳድጉ እንደነበር ደራሲው መስክሮላቸዋል።

“ቢያንስ 60 የድሃ ልጆችን፣ በሱ ቤተሰብ ውስጥ በልተው፣ ጠጥተው፣ ተምረው ጨርሰው፣ ወጥተው ራሳቸውን ችለዋል።”

በአንድ ወቅት ዘነበ ዶክተር ተወልደን “ሰው ለመተካት አስበህ ታወቅለህ ወይ?” ብሎ ጠየቃቸው። “እኔ መተካት አለብኝ ብዬ አላስብም። ተፈጥሮ ራሷ የሚንከባከባትን ትፈጥራለች። የበሰለው ያልፍና ጥሬው ይተካል” የሚል ምለሽ ሰጥተዋል።

ዶክተር ተወልደ ብርሃን የዓለምን ደህንነት የጠበቁ ናቸው የሚለው ደራሲው ዶክተር ተወልደ በዓለም ታላላቅ ከሆኑት ሰዎች አንዱ እንደሆኑ ያምናል።

“ወደፊት ዓለም የአከባቢ ጥበቃ ሀሳብ አፍላቂዎችን (Thinker) ስትመዘግብ ከነዛ ውስጥ አንዱ ዶክተር ተወልደ እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ” ብሏል።