ዩኬ የጥገኝነት ጥያቄያቸው ያልተሳካላቸው ስደተኞችን 3 ሺህ ፓውንድ በመክፈል ወደ ሩዋንዳ ልትልክ ነው

ዩናይትድ ኪንግደም በአገሯ የጥገኝነት ጥያቄያቸው ተቀባይነት ያላገኙ ስደተኞችን እስከ 3 ሺህ ፓውንድ በመክፈል ወደ ሩዋንዳ ልትልክ መሆኑን አስታወቀች።

ለመጀመሪያ ጊዜ በዘ ታይምስ ይፋ የሆነው ይህ አዲስ የስደተኞች ዕቅድ የጥገኝነት ጥያቄያቸው ያልተሳካላቸው ስደተኞች በበጎ ፈቃደኝነት ወደ አገራቸው እንዲመለሱና ለዚህም የሚሆን ገንዘብ ይሰጣቸዋል።

የጥገኝነት ጥያቄያቸው በዩናይትድ ኪንግደም ውድቅ ለተደረገባቸው ለማንኛውም ስደተኞች ክፍት ይሆናል ተብሏል።

ይህ ዕቅድ በተለይም ወደ አገራቸው መመለስ በማይችሉ ስደተኞች ላይ ያነጣጠረ ነው።

የዩናትድ ኪንግደም የገንዘብ ሚኒስትር ኬቨን ሆሊንራክ ወደ ሩዋንዳ ለመሄድ ለተስማሙ ስደተኞች የሚከፈለው ክፍያ “የህዝብን ገንዘብ በአግባቡ መጠቀም ይሆናል” ብለዋል።

“እነዚህን ሰዎች ያለ ምንም ጥቅም እዚህ ማቆየት ከዚያ የበለጠ ገንዘብ ያስወጣናል” ሲሉም ለታይምስ ራዲዮ ተናግረዋል።

“እዚህ በህገወጥ መንገድ ከመጣችሁ በዚህች አገር መቆየት አትችሉም የሚለውን መልዕክት ያስተላልፋል” ሲሉም አክለዋል።

“መሰረታዊ ነጥብ ይህ ነው። ማንም ሰው ወደ ሩዋንዳ ለመሄድ 3 ሺህ ፓውንድ ለማግኘት ብቻ ወደዚህ ለመምጣት የሚሞክር አይመስለኝም። “ ብለዋል።

በህገወጥ መንገድ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ገብተዋል የተባሉ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ተልከው ጥያቄያቸው ከዚያ የሚታይበትን የተለየ እቅድም ለመተግበር መንግሥት እየሞከረ ይገኛል።

ይህ እቅድም ከሩዋንዳ የደህንንት ስጋት ጋር በተገናኘ በፍርድ ቤቶች መታገዱ ይታወሳል።

እነዚህን ሙግቶችንም ለማሸነፍ የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት የምስራቅ አፍሪካዊቷን አገር አስተማማኝ አድርጎ የሚፈርጃት ‘የሩዋንዳ ሴፍቲ ቢል’ (የሩዋንዳ የደህንነት ረቂቅን) ለማጽደቅ እየሞከረ ይገኛል።

አዲሱ ዕቅድ ከዚህ ከነበረው የተለየ እንዲሁም በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ እና በፓርላማው በሚጸድቀው ረቂቅ ላይ የተመሰረተ አለመሆኑንም ቢቢሲ ሰምቷል።

የዩኬ የሃገር ውስጥ ጽሕፈት ቤት ቃለ አቀባይ በፈቃደኝነት መመለስ “ህገወጥ ስደትን ለመቅረፍ የምናደርገው ጥረት ዋነኛው ጉዳይ ነው” ብለዋል።

ጥገኝነታቸው ተቀባይነት ያላገኙ ስደተኞች በሩዋንዳ በህጋዊ መንገድ እንዲሰሩ ይፈቀድላቸዋል፤ ሩዋንዳ ሲደርሱም ተጨማሪ ድጋፍ ያገኛሉ ተብሏል።

በዚህ እቅድ ወደ ሩዋንዳ የሚዛወሩ የመጀመሪያ ስደተኞች መቼ እንደሆነ ያልተጠቀሰ ሲሆን ምን ያህል እንደሆኑም የተቀመጠ አሃዝ የለም።