ሎስ አንጀለስ ከተማ “የስደተኞች መጠለያ” እሆናለሁ ስትል አወጀች

ለስደተኞች ድጋፍ ለመስጠት የተደረገ ሰለማዊ ሰልፍ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ለስደተኞች ድጋፍ ለመስጠት የተደረገ ሰለማዊ ሰልፍ

በአሜሪካ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ የሆነችው ሎስ አንጀለስ “የስደተኞች መጠለያ ነኝ” ስትል አስታወቀች።

ከተማዋ ከተመራጩ ፕሬዝዳት ዶናልድ ትራምፕ ጋር በስደተኞች ጉዳይ ውዝግብ ውስጥ ልትገባ ትችላለች እየተባለ ነው።

የከተማዋ ምክር ቤት “መጠለያ ከተማ” የተሰኘ ረቂቅ አፅድቋል። ይህ ረቂቅ የፌደራል መንግሥት የስደተኞች ጉዳይ ባለሥልጣናት በከተማዋ ሃብት እንዳይጠቀሙ ያግዳል።

የሎስ አንጀለስ ትምህርት ቤቶች ለሰነድ አልባ ስደተኞች እና ለተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ተማሪዎች “መጠለያ” ይሆናሉ ሲትልም ከተማዋ አውጃለች።

ከሁለት ወር በኋላ በዓለ ሲመታቸው የሚፈጸመው ትራምፕ በርካታ ስደተኞችን ከአሜሪካ እንደሚያባርሩ ቃል ገብተዋል።

የትራምፕ ቀኝ እጅ የሆኑት ቲም ሆማን የፌደራል መንግሥት ስደተኞችን ለማስወጣት የሚያደርገውን ጥረት በሚቃረን መልኩ “የስደተኞች መጠለያ እንሆናለን” የሚሉ ከተሞችን አስጠንቅቀዋል።

እነዚህ ከተሞች ስደተኞች ላይ የሚወሰደውን እርምጃ መግታት እንደማይችሉም ከዚህ ቀደም አስታውቀዋል።

ከፎክስ ቴሌቪዥን ጋር ከቀናት በፊት ባደረጉት ቃለ ምልልስ “ስደተኛ ወንጀለኞችን ወደ መጡበት እንዳንመልስ የሚያስቆመን ነገር የለም። ብታግዙንም ባታግዙንም ሥራችንን እንሠራለን” ብለዋል።

“መጠለያ ከተሞች” ለፌደራል መንግሥቱ የስደተኞች ጉዳይ መሥሪያ ቤት የሚሰጥ ገንዘብን ይገድባሉ።

ቦስተን እና ኒው ዮርክን ጨምሮ ሌሎችም ግዛቶች ሃብታቸው በፌደራል መንግሥት የስደተኞች ጉዳይ ባለሥልጣናት ጥቅም ላይ እንዳይውል ገደብ እንደሚጥሉ ቃል ገብተዋል።

የትራምፕን መመረጥ ተከትሎ ብዙ ትምህርት ቤቶች ለስደተኞች “መጠለያ” መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ከሜክሲኮ ድንበር 225 ኪሎሜትር የምትርቀው የሎስ አንጀለስ ከተማ የትምህርት ቤቶች አካባቢ ፀረ ስደተኞችና ፀረ ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች ያላቸውን ውሳኔዎች የሚገዳደሩ ሕጎች አሏት።

እነዚህም በዚህ አካባቢ ያሉ ተማሪዎችና ወላጆችን የሚጠብቁ እንዲሁም ለስደተኞች ጉዳይ ባለሥልጣናት የሚሰጥ መረጃን የሚገድቡ ናቸው።

የከተማዋ ምክር ቤት አባል ኒታያ ራማን “በፍርሃት አንሮጥም። በሁሉም ዓይነት መንገድ እንታገላችኋለን” ማለታቸውን ኤልኤ ታይምስ ዘግቧል።

በዚህ ውሳኔ ከተማው ከትራምፕ ጋር መጋጨቱ አይቀርም። ትራምፕ ከሥልጣን ዘመናቸው መነሻ አንስቶ ስደተኞችን ለማባረር ቃል ገብተዋል።

ሎስ አንጀለስ በሕግነት የሚቀበለው ረቂቅ፣ ስደተኞችን ለማስወጣት ጥቅም ላይ የሚውል ገንዘብ ከከተማዋ እንዳይወሰድ ያደርጋል። ከፌደራል መንግሥት የስደተኞች ጉዳይ ባለሥልጣናት ጋርም ከተማዋ አትተባበርም።

የከተማዋ ምክር ቤት አባል ኒታያ ራማን ለቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ “የከተማዋን ግብዓት ተጠቅመው ስደተኞችን ማስወጣት አይችሉም” ብለዋል።

የከተማዋ አመራሮች ከፌደራል መንግሥት ጋር የሚጋሩት መረጃ ላይም ገደብ ይጥላል።

የከተማዋ ከንቲባ ካረን ባስ ከፈረሙበት በኋላ በይፋ ይፀድቃል።