ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጠቅላይ ሚኒስትር ሱናክ በጥንታዊ ቅርጻ ቅርጾች ውዝግብ ከግሪኩ መሪ ጋር የነበራቸውን ስብሰባ ሰረዙ
‘ኢልጊን ማርብልስ’ በሚል በሚታወቁት ጥንታዊ የግሪክ ቅርጻ ቅርጾች ምክንያት በእንግሊዝ እና በግሪክ መንግሥት መካከል ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ ተፈጠረ።
የግሪኩ ጠቅላይ ሚኒስትር ክሪያኮስ ሚትሶታኪስ ከሪሺ ሱናክ ጋር በለንደን ይገናኛሉ ተብሎ የነበረ ሲሆን የጠቅላይ ሚኒስትር ሱናክ ቢሮ በመጨረሻው ሰዓት ስብሰባውን ሰርዞታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስብሰባው በድንገት መሰረዙ ክፉኛ እንዳሳዘናቸው ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ሚትሶታኪስ ስብሰባውን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር እንዲያካሂዱ የቀረበላቸውን አማራጭም ሳይቀበሉት ቀርተዋል።
የስብሰባው መሰረዝ የተሰማው ሚትሶታኪስ፣ በእምነ በረድ የተሰሩት ጥንታዊ ቅርጻ ቅርጾች ወደ ግሪክ መመለስ አለባቸው ሲሉ ለቢቢሲዋ ላውራ ኩንስበርግ ከተናገሩ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቃለ ምልልሳቸው "የተወሰኑትን የግሪክ ጥንታዊ የጥበብ ሥራዎች በለንደን ቀሪዎቹ ደግሞ በአቴንስ መሆናቸው ሞናሊዛን ለሁለት እንደመክፈል ነው" ብለዋል።
ሚትሶታኪስ ስብሰባው በመጨረሻው ሰዓት በመሰረዙ መበሳጨታቸውን ሰኞ ምሽት ላይ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ጨምረውም በትክክለኝነት እና በፍትሕ ከሚያምኑት ጋር ገንቢ በሆነ ክርክር እና ውይይት ላይ ለመሳተፍ ወደኋላ እንደማይሉም ገልጸዋል።
ሚትሶታኪስ ግሪክ እና እንግሊዝ ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ግንኙነት አላቸው፤ በመሆኑም የሁለትዮሽ ግንኙነታችን ወሰን ሰፊ ነው ብለዋል።
“ ጥንታዊ ቅርጻ ቅርጾቹን በተመለከተ አቋማችን የሚታወቅ ነው። ከእንግሊዝ አቻዬ ጋር በጉዳዩ ላይ፣ እንዲሁም በጋዛ እና በዩክሬን ስላለው ሁኔታ፣ ስለ አየር ንብረት ቀውስ እና ስደትን በተመለከቱ ዓለም አቀፍ ተግዳሮቶች ዙሪያ ለመነጋገር ሞክሬያለሁ” ብለዋል።
ለግሪክ መንግሥት ቅርበት ያላቸው ምንጮች እንዳሉት ሚትሶታኪስ በተፈጠረው ነገር ግራ ተጋብተዋል።
ስብሰባውን ማክሰኞ ዕለት በምሳ ሰዓት ለማካሄድ ታስቦ እንደነበር ቢቢሲ መረዳት ችሏል።
ሚትሶታኪስ እሑድ እለት ከቢቢሲዋ ላውራ ኩንስበርግ ፕሮግራም ጋር ያደረጉት ቆይታ ሱናክን ሳያበሳጭ እንዳልቀረ ተነግሯል።
የእንግሊዝ መንግሥት ስብሰባው መሰረዙን እና የግሪኩ ጠቅላይ ሚኒስትር ፣ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ኦሊቨር ዳውድን ጋር እንዲገናኙ አማራጭ እንዳቀረበ ገልጿል።
አንድ ከፍተኛ የወግ አጥባቂ ምንጭ እንደተናገሩት ቀደም ብሎ ኢልጊን ማርብልን በተመለከተ አስተያየት ከተሰጠ በኋላ ይህን ስብሰባ መቀጠል የማይቻል ነው።
“ አቋማችን ግልጽ ነው። ኢልጊን ማርብል የእንግሊዝ ሙዚየም ቋሚ ስብስቦች ናቸው። መቀመጥም ያለባቸው እዚህ ነው ።ለማንኛውም የእንግሊዝ ፖለቲከኛ እነዚህን ለድርድር ማቅረብ ግድየለሽነት ነው” ብለዋል።
ሚትሶታኪስ ቀደም ብሎ ከሌበር ፓርቲ መሪ ኬር ስታርመር ጋር ተገናኝተው የነበረ ሲሆን ጠዋት ላይ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር እንዲገናኙ የተቀመጠውን ፕሮግራም አልቀበልም ካሉ በኋላ ማክሰኞ ዕለት ወደ ግሪክ ተመልሰዋል።
በተለያየ ታሪካዊ አጋጣሚዎች ከሌላ አገር የተወሰዱ ጥንታዊ ቅርጻ ቅርጾች በዓለም አቀፍ ካሉ ሙዚየሞች ወደ መነሻቸው መመለስ አለባቸው የሚለው ክርክር እየጨመረ መጥቷል።
የግሪክ ጥንታዊ ቅርጻ ቅርጾች ሎርድ ኢልጊን የተባለ የእንግሊዝ ወታደር እና ዲፕሎማት በ19 ክፍለ ዘመን አቴንስ ከሚገኙ ፓርቴኖን ቤተ መቅደስ ያስወጣቸው ናቸው።
ከዚያም ቅርጻ ቅርጾቹ እንደ አውሮፓውያኑ በ1816 በእንግሊዝ መንግሥት ተገዝተው በእንግሊዝ ሙዚየም ተቀምጠው ይገኛሉ።