ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አዲሱ ሊቀ ጳጳስ በመጀመሪያ ስብከታቸው እምነት ማጣት መስፋፋቱን አሳሰቡ
አዲሱ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ሊዮ 14ኛ ከተሾሙ በኋላ ባካሄዱት የመጀመሪያው የፀሎት እና የስብከት ሥነ ሥርዓት ላይ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት ማጣትን እንድትታገል አሳሰቡ።
ሰዎች ቤተ ክርስቲያንን ጥለው ወደ "ቴክኖሎጂ፣ ገንዘብ፣ ስኬት፣ ኃያልነት ወይም ደስታ" ፊታቸውን እያዞሩ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ቀሳውስት በተለያዩ አካባቢዎች የሃይማኖት ትምህርትን እንዲያስፋፉ ሊቀ ጳጳስ ሊዮ 14ኛ አሳስበዋል።
የ69 ዓመቱ አሜሪካዊው ሮበርት ፕሪቮስት በትውልድ አገራቸው እና ለ20 ዓመታት ባገለገሉባት ፔሩ ሹመታቸው ደስታን ፈጥሯል።
"የቤተ ክርስቲያኗ ታማኝ አገልጋይ ለመሆን መመረጣቸውን" ገልጸው "እምነት ማጣት" የገጠማቸውን ለመድረስ እንደሚሠሩም ተናግረዋል።
"በሕይወት ትርጉም ማጣት እምነት ከማጣት ጋር ይተሳሰራል። ይቅር ባይነትን ማጣት፣ አሰቃቂ የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ የቤተሰብ ቀውስ እና ሌሎችም ማኅበረሰባችንን የሚፈትኑ ቁስሎች እምነት ከማጣት ጋር ይገናኛሉ" ብለዋል በጣልያንኛ ባደረጉት ንግግር።
ወርቃማ ጥለት ያለው ነጭ ለብሰው በሲስቲን ቤተ መቅደስ ያሰሙት ስብከት በቫቲካን በቀጥታ ተላልፏል።
ሹመታቸው ተከትሎ በ10 ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ባሰሙት ንግግር ቤተ ክርስቲያኗ "ሁሌም ለንግግር ክፍት መሆኗን" ገልጸዋል።
ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የቀድሞው ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ እንደሚያደርጉት ሁሉ በዓለም ሰላም እንዲሰፍንም ጠይቀዋል።
"በንግግር አማካኝነት ድልድዮችን እንድንገነባ እርዱን፣ እርስ በእርስም ተባበሩ። ሁሌም በሰላም እንደ አንድ ሕዝብ ሁኑ" ብለዋል።
በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ከአዲሱ ሊቀ ጳጳስ ጋር ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን የአገራት መሪዎች ገልጸዋል። እንኳን ደስ አለዎም ብለዋቸዋል።
የመጀመሪያው አሜሪካዊ ሊቀ ጳጳስ መመረጣቸው "በጣም ያኮራል" ሲሉ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ገልጸዋል።
አዲሱ ጳጳስ የአሜሪካ እና የፔሩ ዜግነት ያላቸው ሲሆን፣ እንደ ቀድሞው ሊቀ ጳጳስ ተራማጅ፣ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ እና ለድሆች የቆሙ መሆናቸው ይነገራል።
ሊቀ ጳጳስ ሊዮ 14ኛ ግርማ ሞገሥ ያላቸው የሃይማኖት መሪ መሆናቸው በብዙዎች የሚጠቀስ ሲሆን፣ ሲሆን ቤተ ክርስቲያኒቷን ወደፊት ያሻግራሉ ተብሎም ይታመናል።
ከሁለት ሳምንት በፊት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የቀድሞው ሊቀ ጳጳስ ወደ ሮም ያመጧቸው ምናልባትም እንዲተኳቸው ፈልገው ይሆናል ተብሎ ተዘግቧል።