ሮበርት ፕሪቮስት አዲሱ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ሊዮ 14ኛ ማን ናቸው?

ትናንት ከሰዓት በቫቲካን ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የተሰባሰበው ሕዝብ የተመረጡት አዲስ ሊቀ ጳጳስ ማን መሆናቸው በይፋ ከመነገሩ በፊት 'ረዥም ሕይወት ለጳጳሳችን' እያለ ድምጹን ጮክ አድርጎ ደስታውን ሲገልጽ ነበር።

የ69 ዓመቱ ሮበርት ፕሪቮስት 267ኛ ሊቀ ጳጳስ ሆነው ሲሾሙ መጠሪያቸውም ሊዮ 14ኛ እንደሚሆን ተነግሯል።

ምንም እንኳ አብዛኛውን የአገልግሎት ዘመናቸውን ያሳለፉት በላቲን አሜሪካ ቢሆንም፣ የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስትያን ለመጀመርያ ጊዜ አሜሪካዊ ሊቀ ጳጳስ መሾሟ ነው።

ሊቀ ጳጳስ ሊዮ 14ኛ ጵጵስናቸውን ከመቀበላቸው በፊት በፔሩ በሚሽነርነት ለረዥም ዓመታት አገልግለዋል።

በ1955 በስፔናዊ እናታቸው እና የፈረንሳይ እና ጣልያን ደም ካላቸው አባታቸው በቺካጎ የተወለዱት ፕሪቮስት፣ በ1982 ቅስናቸውን ተቀብለዋል።

ከሦስት ዓመት በኋላ ወደ ፔሩ ቢያመሩም ወደ አሜሪካ ለተለያዩ አገልግሎቶች ይመላለሱ ነበር።

የፔሩ ዜግነት ያላቸው ፕሪቮስት ከተገለሉ ማኅበረሰብ አባላት ጋር በመስራት እንዲሁም ልዩነቶችን ለማጥበብ በመጣር ይታወቃሉ።

በሰሜናዊ ምዕራብ ፔሩ የአንድ ቤተክርስትያን መጋቢ በመሆን ለ10 ዓመት ያህል ያገለገሉት ፕሪቮስት፣ በካቶሊክ ሴሚናሪ ውስጥ በመምህርነትም ሰርተዋል።

ሊዮ 14ኛ ሊቀ ጳጳስ ሆነው ከተሾሙ በኋላ በተናገሩት የመጀመርያ ንግግር በሞት ለተለዩት ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ያላቸው ፍቅርን ገልጸዋል።

"አሁን ድረስ ደካማውን ነገር ግን በብርታት የተሞላውን የሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ድምጽ ሲባርከን ይሰማናል" ብለዋል።

"በጋራ ከእግዚአብሔር ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን ሁላችንም ወደ ተሻለ ነገር እንሻገር" ሲሉ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ተሰብስቦ ደስታውን ለሚገልፀው ሕዝብ ንግግር አድርገዋል።

በፔሩ በሚሽነሪነት አገልግሎት ላይ ሳሉ፣ ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ በፔሩ ቺክላዮ ጳጳስ አድርገው ሾሟቸዋል።

በምርጫው ላይ በተሳተፉት ካርዲናሎች ዘንድ በላቲን አሜሪካ ጳጳሳትን በመምረጥ እና በመሾም ቁልፍ ሚና ያላቸው የጳጳሳት አለቃ ሆነው በማገልገላቸው በሚገባ ይታወቃሉ።

ሊቀ ጳፓስ ፍራንሲስ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2023 ኤጲስ ቆጶስ አድርገው ከሾሟቸው ከጥቂት ጊዜ በኋላ ካርዲናል አድርገው ሾመዋቸዋል።

የሊቀ ጳጳስ ሊዮ አመለካከቶች ምንድን ናቸው?

በካቶሊክ ቤተ ክርስትያን ውስጥ ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ጀምረዋቸው የነበሩ ለውጦችን ያስቀጥላሉ ተብሎ በበርካቶች ዘንድ ይታመናል።

ፕሪቮስት ስደተኞችን፣ ድሆችን እንዲሁም አካባቢን በተመለከተ የሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስን እምነት ይጋራሉ።

ካርዲናል በነበሩበት ወቅት የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስን አቋም ያለምንም ማወላወል ከመሞገት ወደ ኋላ አላሉም ነበር።

የትራምፕ አስተዳደር ሰነድ አልባ ስደተኞችን ወደ ኤል ሳልቫዶር ሲያጓጉዝ ተችተው አቋማቸውን በጽሁፍ ያጋሩ ሲሆን፣ ቫንስ በፎክስ ኒውስ ላይ ቀርቦ የሰጠውን ቃለ ምልልስም እንዲሁ አብጠልጥለው ተችተዋል።

"ጄዲ ቫንስ ተሳስቷል። ኢየሱስ ለሌሎች ያለንን ፍቅር ደረጃ እንድናወጣለት አልጠየቀም" ብለዋል በጽሑፋቸው።

ሮበርት ፕሪቮስት ምንም እንኳ አሜሪካዊ ቢሆኑም እንዲሁም በካቶሊክ ቤተክርስትያን ውስጥ ያለውን መከፋፈል በሚገባ የሚያውቁ ቢሆኑም ቤተክርስትያኒቷን ወደ አንድ ያመጣሉ ተብሎ ተስፋ ተጥሎባቸዋል።

በላቲን አሜሪካ ረዥም ዓመት ማሳለፋቸውን በመጥቀስ ብዙዎች ከአርጀንቲና የተገኙት ሊቀ ጳጳስ የጀመሯቸውን ሥራዎች ያስቀጥላሉ ይላሉ።

ቫቲካን ፕሪቮስት ለረዥም ዓመት በላቲን አሜሪካ ማገልገላቸውን በማስታወስ ከሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ በመቀጠል ሁለተኛው ላቲን አሜሪካዊ ሊቀ ጳጳስ ስትል ጠርታቸዋለች።

በፔሩ በነበሩበት ወቅት ከጾታዊ ጥቃት ጋር በተያያዘ ስማቸው የተነሳ ቢሆንም ያገለግሉባቸው ቤተ እምነቶች እና አብረዋቸው የሰሩ አባቶች ምንም ዓይነት ተሳትፎ የላቸውም ሲሉ ተከላክለውላቸዋል።

አዲሱ ሊቀ ጳጳስ በተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ላይ ያላቸው አቋም ግልጽ አይደለም። ነገር ግን ወግ አጥባቂ የሆኑ ካርዲናሎች ሳይቀሩ ከሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ የለዘበ አቋም እንደሚኖራቸው ያምናሉ።

ሊዮ 14ኛ ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ ጥንዶችን መባረክን በሚመለከት መመርያ ሲያስተላልፉ ምንም እንኳ ጳጳሳት ውሳኔውን እንደሚያገለግሉበት አገር ባሕል እና አውድ አንዲተረጉሙ ቢገልፁም ድጋፋቸውን ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመት ስለ አየር ንብረት ለውጥ በተናገሩበት ወቅት የያኔው ካርዲናል ፕሪቮስት "ከቃል ወደ ተግባር የምንሸጋገርበት" ጊዜ አሁን ነው ብለው ነበር።

የሰው ልጅ ከአካባቢው ጋር "የተናበበ ግንኙነት" መመስረት እንዳለበት ያስተምራሉ።

በቫቲካን የኤሌትሪክ መኪናዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ እንዲሁም ከፀኃይ ብርሃን የሚገኝ ኃይል ስለመጠቀምም በመስበክ ይታወቃሉ።

ሊቀ ጳጳስ ሊዮ 14ኛ፣ ፍራንሲስ ሴቶች ወደ ጵጵስናው እንዲመጡ ለመጀመርያ ጊዜ ውሳኔ ሲያስተላልፉ ድጋፋቸውን ገልፀዋል።