በጦርነት እና በውጥረት የተጀመረው 2014 ዓ.ም. እንዴት አለፈ?

ኢትዮጵያውያን ይህንን የ2014 ዓ.ም ሲጀምሩት በሰሜን የአገሪቱ ክፍል ሲካሄድ የቆው ጦርነት ተባብሶ ቀጥሎ ነበር።

የስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ተጠናቅቆ አብላጫውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ያገኘው ብልጽግና ፓርቲ መሆኑ ታውቆ ነበር።

የትግራይ ኃይሎች ወልድያን እና ሌሎች ስፍራዎችን ተቆጣጥረው ነበር።

አገሪቱ በጦርነት ውስጥ ሆና በተካሄደው ምርጫ በከፍተኛ ድምጽ ያሸነፈው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ብልጽግና ፓርቲ አዲስ ሥልጣኑን የተረከበው በመስከረም ወር መጨረሻ ላይ ነበር።

ብዙም ሳይቆይ ግን የትግራይ ኃይሎች ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች የጥቃት አድማሳቸውን በማስፋታቸው የሚኒስትሮች ምክር ቤት በመላው ኢትዮጵያ የሚፀና አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀ።

አዋጁ ለስድስት ወራት የሚቆይ እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን፣ የተለያዩ ክልከላዎችን እና ግዴታዎችንም ይዞ ነበር።

የትግራይ ኃይሎች በቁጥጥራቸው ስር ባደረጓቸው የአማራ እና አፋር አካባቢዎች የተቀናጀ ጥቃት በመክፈታቸው የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ የክልል ልዩ ኃይሎች፣ ሚሊሻ እና ፋኖ በጋራ እንዲዘምቱ ጥሪ ቀረበ።

የህወሓት ኃይሎች የፌደራል መንግሥቱን በኃይል ለመጣል በማሰብ ወደ አዲስ አበባ ጉዟቸውን አፋጠኑ።

የትግራይ ኃይሎች ማጥቃት እየበረታ መጥቶ ደቡብ ወሎ ከተማ የሆነችው ደሴ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ከተማዋን ኮምቦልቻን ከተቆጣጠሩ በኋላ፣ የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ ከኦነግ ሸኔ ጋር መገናኘታቸውን ገለፁ።

ከዚያም ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ዘልቀው በመግባት በርካታ ቦታዎችን በመቆጣጠር በአፋር በኩል የጂቡቲ ወደብን ከመሃል አገር ጋር የሚያገናኘውን መንገድ ለመያዝ ጥረት አደረጉ።

ይህንንም ተከትሎ አገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት የጉዞ ማስጠንቀቂያ እና ዜጎቻቸው ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ ማሳሰቢያ ሰጡ።

ነገር ግን ባልታሰበ ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሠራዊታቸው የሚያካሂደውን የፀረ ማጥቃት ዘመቻ በቀጥታ ለመምራት ወደ አውደ ውጊያው ሄዱ።

ከዚህ በኋላ ከአዲስ አበባ በሁለት መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የነበሩት አማጺያኑ በመቶዎች ኪሎ ሜትሮች ወደ ኋላ ለማፈግፈግ ተገድደዋል።

የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በህወሓት ኃይሎች ተይዘው የነበሩ የአፋርና የአማራ ክልል ቦታዎችን መልሰው ከተቆጣጠሩ በኋላ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ዘመቻው ወደ ትግራይ እንዳይቀጥል ሠራዊቱን ማዘዙን አስታወቋል።

ምርመራ እና ተኩስ አቁም

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ኢትዮጵያ ዉስጥ በጦርነት ምክንያት የደረሱ የመብት ጥሰቶችን የሚመረምር ኮሚሽን የሰየመው በዚህ ዓመት ነበር።

ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ በኩል የኮሚሽኑን መቋቋም ተቃውሞታል።

ከወራት በኋላ ግን ኮሚሽኑ የኢትዮጵያ መንግሥትን ፈቃድ አግኝቶ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ሊያካሂደው ስላሰበው ምርምራ ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ጋር ተወያይቷል።

የኢትዮጵያ መንግሥትዕ ወደ ትግራይ ክልል የሚደርሰው ሰብአዊ እርዳታ እንዲቀላጠፍ በሚል ከመጋቢት 15/2014 ዓ.ም ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ የሚጸና ግጭት የማቆም ውሳኔ ማሳለፉን አሳውቋል።

ከዚህ በኋላም የትግራይ ኃይሎች የሰብዓዊ እርዳታ ትግራይ የሚደርስ ከሆነ ግጭት ለማቆም እንደሚስማሙ ገልጸው ጦርነቱ ጋብ ብሎ ቆይቷል።

በዚህም ሳቢያ ለወራት ተቋርጦ የነበረው የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት በየብስና በአየር ወደ ትግራይ መግባት ጀምሮ ነበር።

የጋዜጠኞች እና የሌሎች ጅምላ እስሮች

ኢትዮጵያ ከእርስ በርስ ጦርነቱ ጋር በተያያዘ የአስቸኳይ ጊዜ ካወጀችበት ጥቅምት 23/2014 ዓ.ም ጀምሮ 14 ጋዜጠኞችን ማሰሯን ሲፒጄ አስፍሯል።

ኢሰመኮ በበኩሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መሠረት በማድረግ በተለይም በአዲስ አበባ እስር "ማንነትን/ብሔርን መሠረት ባደረገ መልኩ በሚመስል ሁኔታ መከናወኑ እጅግ ያሳስበኛል" ብሎ ነበር።

በእስር ላይ ውለው ከነበሩት ጋዜጠኞች እና ሌሎች ግለሰቦች ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ ክስ ሳይመሰረትባቸው እና ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለሳምንታት እና ለወራት ታስረው ቆይተዋል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በአዲስ አበባ ህጻናትንና አዛውንቶችን ጨምሮ የትግራይ ተወላጆችን ኢላማ ያደረገ የጅምላ እስር እየተካሄደ መሆኑን በመጥቀስ ሪፖርት አውጥቶ ነበር።

ሲፒጄ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በሥራቸው ምክንያት በእስር ላይ የሚገኙ ሁሉንም ጋዜጠኞች በአስቸኳይ እና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፍታት አለባቸው ሲል ጠይቆ ነበር።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥቅምት 25/2014 ዓ.ም ያጸደቀውና ለስድስት ወራት በመላው ኢትዮጵያ ተጥሎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጥር 18 2014 ባካሄደው ስብሰባ እንዲነሳ ወስኗል።

የይህንንም ተከትሎ በእስር ላይ የነበሩት አብዛኞቹ ግለሰቦች ተለቀዋል።

ማንነት ተኮር ጥቃቶች

በዚህ ዓመት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተስተዋለውና በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለህልፈት የዳረገው ዋነኛ ክስተት ብሔር ተኮር ጥቃት ነበር።

እነዚህ ጥቃቶች በየአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች እንዲሁም በክልል እና በፌደራል የፀጥታ ኃይሎች መፈጸማቸውን በየጊዜው የወጡ ሪፖርቶች አመልክተዋል።

በተለይም በቤንሻንጉል ክልል መተከል ዞን በጉባ ወረዳ አይሲድ ቀበሌ ውስጥ የመንግሥት የፀጥታ አባላት እና በሌሎች ተሳትፎ ሲቪል ሰዎች ላይ ግድያና አሰቃቂ ድርጊት መፈፀሙን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሪፖርት አድርጓል።

በኦሮሚያ ክልል፣ ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ውስጥ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ከ300 በላይ የአማራ ብሔር አባላት ተገድለዋል። በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል፣ ቄለም ወለጋ ውስጥ በታጣቂዎች በተፈፀመ ጥቃት በርካታ የአማራ ብሔር ተወላጆች ተገድለዋል።

ሂዩማን ራይትስ ዎችም በሰኔ ወር 2014 ዓ.ም. በምዕራብ ኦሮሚያ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች በታጣቂዎች ሲገደሉ የኢትየጵያ መንግሥት ፀጥታ ኃይሎች ጥቃቱን ለመከላከል በቂ ጥበቃ አላደረጉም ነበር ብሏል።

እዚያው ኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ውስጥ በታጣቂ ኃይሎች በተፈጸሙ ጥቃቶች ከ60 በላይ ሰዎች መገደላቸውን፤ ከ70 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን እና ከ20 ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን ኢሰመኮ ገልጿል።

እነዚህ ጥቃቶች በመፈጸም ነዋሪዎችና መንግሥት በሽብርተኝነት የተፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን በተደጋጋሚ ቢወነጅሉም ቡድኑ ግን ይህንን አይቀበልም።

ጥቃት በጋምቤላ ከተማ ላይ

ሰኔ 07/2014 ዓ.ም. የኦነግ ሸኔ እና የጋምቤላ ነጻነት ግንባር ታጣቂዎች የጋምቤላ ክልል ዋና ከተማ ውስጥ ጥቃት ከፍተው ለሰዓታት የቆየ የተኩስ ልውውጥ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር አካሄደው ነበር።

ይህንን ጥቃት ተከትሎ ከ40 በላይ ሰዎች መገደላቸውን በክልሉ የተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ የሚገኙ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በወቅቱ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

በከተማዋ ላይ የተከፈተው ጥቃት በተለይ በክልሉ ምክር ቤት እና በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ጽህፈት ቤት አካባቢ ላይ አትኩሮ የነበረ በመሆኑ፣ ቁልፍ የክልሉን ተቋማት ለመቆጣጠር ያለመ እንደነበር በወቅቱ ተነግሯል።

ታጣቂዎች በጋምቤላ ክልል ዋና ከተማ ላይ በከፈቱት በዚህ ጥቃት የተወሰኑ የከተማዋን ክፍል መቆጣጣር ችለው ነበር።

ነገር ግን የክልሉ እና የፌደራል መንግሥቱ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ አብዛኞቹ የታጣቂው ቡድን አባላት መገደላቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ገልጸው ነበር።

የአልሸባብ ጥቃት

ሐምሌ 13/2014 ዓ.ም የሶማሊያው አስላማዊ ቡድን የአልሻባብ ታጣቂዎች ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር በምትዋሰንባቸው የድንበር ከተሞች ጥቃት ከፍተው ከባድ ውጊያ ተካሂዷል።

በአሸባሪ ቡድንነት የሚታወቀው እና በጎረቤት አገር ሶማሊያ በስፋት የሚንቀሳቀሰው አልሻባብ በአዋሳኝ የድንበር አካባቢዎች እና ወደ ኢትዮጵያ ዘልቆ በመግባት ጥቃቶችን ፈጽሞ ነበር።

የሶማሊያው ታጣቂ ቡድን በኢትዮጵያ ላይ የከፈተውን ጥቃት ተከትሎ የመከላከያ ሠራዊት በወሰደው እርምጃ ከፍተኛ የአልሻባብ መሪዎች መገደላቸውን ገልጿል።

በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከተገደሉት የአልሻባብ ከፍተኛ አመራሮች መካከል የአሜሪካ መንግሥት መገኛውን ለጠቆመ 5 ሚሊዮን ዶላር ወሮታ እከፍላለሁ ያብሎለት የነበረው ፉአድ መሐመድ ካህላፍ ይገኝበታል።

የክልልነት ጥያቄ

የኮንታ ልዩ ወረዳ፣ የምዕራብ ኦሞ ዞን፣ የቤንች ሸኮ ዞን፣ የካፋ ዞን፣ ዳውሮ ዞን እና የሸካ ዞን በጋራ 11ኛውን ክልል በይፋ የመሰረቱት በዚህ ዓመት ነበር።

አምስቱ ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ ከደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ወጥተው የጋራ አንድ ክልል ለመመስረት ሕዝበ ውሳኔ ያደረጉት ከአገራዊ ምርጫ ጋር በአንድነት ነበር።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መስከረም 28/2014 ዓ.ም የተካሄደውን የሕዝበ ውሳኔ ውጤት ባሳወቀበት ውቅት እንደገለጸው፤ በሕዝበ ውሳኔው ላይ ድምጽ ለመስጠት ከ1.3 ሚሊየን በላይ ሰዎች ተመዝግበው 1.2 ሚሊየን በላይ የሚሆኑት ድምጽ ሰጥቷል ብሏል።

በዚህ ዓመት ከተነሱ የክልልነት ጥያቄዎች መካከል አንዱ በደቡብ ክልል የሚገኙት የወላይታ፣ ጌዲኦ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ኮንሶ እና ደቡብ ኦሞ ዞኖችን እንዲሁም የደራሼ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ ቡርጂ እና አማሮ ልዩ ወረዳዎች፤ በጋራ አንድ ክልል ለመመስረት ያቀረቡት ጥያቄ ነው።

እነዚህ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች በየምክር ቤቶቻቸው ያጸደቁትን ውሳኔ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቅርበው ይሁንታን አግኝተዋል።

በዚህም የደቡብ ክልል ለሁለት ተከፍሎ የአገሪቱ አጠቃላይ ክልሎች ወደ 12 ይደርሳሉ።

የድርድር ፍላጎት እና ዝግጅት

በመንግሥት እና በህወሓት መካከል የሚደረገው ጦርነት እየተካሄደ ባለበት ወቅት ሁለቱም ወገኖች ወደ ድርድር ጠረጴዛ እንዲመጡ የተለያዩ አካላት ግፊት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ይህንንም ተከትሎ መንግሥት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ድርድር ለማድረግ ፈቃደኛ መሆኑን አስታውቋል።

ከዚህ በኋላ የፌደራል መንግሥቱ ሰባት አባላት ያሉትን ተደራዳሪዎች ይፋ ማድረጉን ተከትሎ የትግራይ ኃይሎች ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ሲያደርጉት የነበረውን ጦርነት ለማብቃት በኬንያ መንግሥት አሸማጋኝነት በሚካሄድ ድርድር ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን አስታወቀዋል።

የፌዴራል መንግሥት ድርድሩ በአፍሪካ ኅብረት ስር መካሄድ አለበት ሲል የትግራይ ኃይሎች በበኩላቸው በኅብረቱ ላይ እምነት እንደሌላቸው በመግለጽ በኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እንዲመራ ጠይቀዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተመረጡት ሰባት የመንግሥት ተወካዮች የድርድር ማዕቀፍ ይፋ አድርገዋል።

የህወሓት በኩልም ለድርድሩ ዝግጁ መሆናቸውንና አስፈላጊ በሆበት ጊዜ ከፍተኛ የቡድኑ አመራሮችን ለመላክ ፈቃደኛ መሆናቸውን አሳውቀው ነበር።

የጦርነቱ ማገርሸት

በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ኃይሎች መካከል የሚካሄደው ጦርነት ከወራት የተኩስ አቁም በኋላ መልሶ ተቀስቅሷል።

ለአምስት ወራት ጋብ ብሎ የነበረው ጦርነት ነሐሴ 18/2014 ዓ.ም. አገርሽቶ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ውስጥ ጦርነት እየተካሄደ ይገኛል።

ለትግራይ ክልል አዋሳኝ በሆነችው የሰሜን ወሎ ከተማ ላይ የህወሓት ኃይሎች ከተለያዩ አቅጣጫዎች ጥቃት በመክፈታቸው "የሕዝብን ከፍተኛ ፍጅት ለማስወገድ ሲባል" የፌደራሉ መንግሥት ሠራዊት ከተማዋን ለቆ መውጣቱን አሳውቋል።

የትግራይ አመራሮች ግን በመንግሥት ሠራዊት ተከፈተብን ያሉትን ጥቃት ለመከላከል "በተደረገ የፀረ ማጥቃት ዘመቻ" የቆቦ ከተማንና በዙሪያዋ ያሉ በርካታ ስፍራዎችን ተቆጣጥረው በመንግሥት ኃይሎች የተከፈተባቸውን መጠነ ሰፊ ጥቃት እየተከላከሉ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ በኋላም በምዕራብ ትግራይ፣ በዋግ ኽምራ እንዲሁም ከኤርትራ ጋር አዋሳኝ በሆኑ ስፍራዎች ጦርነቶች ተቀስቅሰው ውጊያ እየተካሄደ ይገኛል።