ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ተመድ በኢትዮጵያ የተፈጸመበትን የእርዳታ ምግብ ስርቆት መመርመር ጀመረ
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ በሚያካሂደው የሕይወት አድን የእርዳታ ሥራ ላይ የተፈጸመ የምግብ አቅርቦት ስርቆትን እየመረመረ እንደሚገኝ ተገለጸ።
አሶሺዬትድ ፕሬስ (ኤፒ) የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ አካል የሆነው የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ቢሮ በአገሪቱ የተከሰቱ የእርዳታ ምግብ ስርቆቶችን እየመረመረ እንደሚገኝ ዘግቧል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር የሆኑት ክላውድ ጂቢዳር በአገሪቱ ላሉ አጋር ድርጅቶች በጻፉት ደብዳቤ “በአንዳንድ ገበያዎች የታየው መጠነ ሰፊ የሆነው የእርዳታ ምግብ ሽያጭ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ስጋት እንዲገባው አድርጎታል” ብለዋል።
ዳይሬክተሩ ለእርዳታ የተባሉ ምግቦች ለገበያ መቅረባቸው በተቋሙ ስም ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ከማሳደሩም በላይ ሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው እርዳታ የማሰባሰብ አቅም ላይ ችግር ሊፈጥር ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ስለዚህም በአገሪቱ በእርዳታ የሚሰጥን ምግብ “አላግባብ መጠቀምን እና ከታለመለት ዓላማ ውጪ መውሰድ በአስቸኳይ ማስቆም እጅግ ወሳኝ ነው” ብለዋል።
በኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት የዘለቀው የሰሜኑ የእርስ በርስ ጦርነት ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ ያስከተለ ሲሆን፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ለረሃብ አደጋ ያጋለጠ ነበር።
በዚህ ጦርነት ተሳታፊ የሆኑ አካላት የምግብ እርዳታ በመዝረፍ እና ለተዋጊዎቻቸው በማቅረብ ሲከሰሱ ቆይተዋል።
በጦርነቱ ወቅት የትግራይ ኃይሎች የደቡብ ወሎ ከተማ የሆነችውን ኮምቦልቻን ተቆጣጠረው በነበሩበት ወቅት የሰብዓዊ እርዳታ ማከማቻ መጋዘኖቹ መዘረፋቸውን ገልጾ ነበር።
ድርጅቱ በወቅቱ በመጋዞኖቹ የነበረ የእርዳታ እህልን የዘረፈው የትኛውም አካል እንደነበረ ያለው ነገር ባይኖርም፤ በወቅቱ ግን የትግራይ ኃይሎች ከተማዋን ተቆጣጠረው ነበር።
ከዚህ በተጨማሪ የፌደራሉ መንግሥት ህወሓት የእርዳታ ምግብ ለተዋጊዎቹ እያከፋፈለ ነው የሚል ክስ ሲያቀርብ ነበር።
ጂቢዳር መጋቢት 27/2015 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ላሉ የዓለም ምግብ ፕሮግራም አጋር ድርጅቶች በጻፉት ደብዳቤ፣ አጋር ድርጅቶች የእርዳታ ምግብ ባልተገባ ሁኔታ ጥቅም ላይ ስለመዋሉ አልያም ስለመወሰዱ የሚያውቁት ካለ መረጃ እንዲያጋሩ ጠይቀዋል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር በደብዳቤያቸው ላይ ያለአግባብ ጥቅም ላይ ሰዋለም ሆነ ስለተሰረቀ የእርዳታ ምግብ ክስተት ያሉት ነገር ባይኖርም፣ ምርመራ ከሚደረግባቸው አጋጣሚዎች መካከል በሽራሮ ከመጋዘን ጠፋ የተባለ የእርዳታ ምግብ እንደሚገኝበት ኤፒ የዜና ወኪል ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።
በስም ያልተጠቀሱ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ሠራተኞች በእርስ በእርስ ጦርነቱ ከፍተኛ ጉዳት በደረሰባት ሽራሮ ከነበረ መጋዘን ውስጥ ለ100 ሺህ ሰዎች ሊበቃ የሚችል የእርዳታ ምግብ መጥፋቱ በቅርቡ መታወቁን ለኤፒ ተናግረዋል።
በድርቅ እና በግጭት በተጎሳቆለችው ኢትዮጵያ ከ20 ሚሊዮን የማያንስ ሕዝብ እርዳታ ጠባቂ ለመሆን ተገዷል።