ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የማይክል ጆርዳን ጫማ ክብረ ወሰን በሆነ ዋጋ በ 2.2 ሚሊዮን ዶላር ተሸጠ
ዝነኛው የቅርጫት ኳስ ተጨዋች ማይክል ጆርዳን በአንድ ወቅት ተጫምቶት የተጫወተበት ጫማ በ2.2 ሚሊዮን ዶላር ተሸጠ።
ኤይር ጆርዳን የሚል መጠሪያ ያለውና በ2.2 ሚሊዮኝ ዶላር የተሸጠው ጫማ ጆርዳን እንደ አውሮፓውያኑ 1997-98 የውድድር ዘመን ለመጨሻ ጊዜ ተጫምቶት የተጫወተበት ነው።
ይህም ጫማው ታይቶ በማይታወቅ ዋጋ የተሸጠ ውዱ ጫማ ሆኗል።
የማይክል ጆርዳን ፊርማ ያረፈበት ይህ የስፖርት ጫማ ከ2 እስከ 4 ሚሊዮን ዶላር ይሸጣል የሚል ግምት የነበረ ሲሆን እስካሁን ለሽያጭ ከቀረቡ የጆርዳን ንብረቶች በከፍተኛ ዋጋ ከተሸጡት መካከል አንዱ ሆኗል።
እንደ አውሮፓውያኑ በ1998 በአሜሪካ የቅርጫት ኳስ ውድድር የለበሰው ማሊያ ባለፈው ዓመት በ10.1 ሚሊዮን ዶላር በጨረታ ተሽጦ ነበር።
በቅርቡ የተደረገው የጫማ ሽያጭ ጆርዳንን የስፖርት አልባሳቱ በውድ ዋጋ የተሸጡለት ስፖርተኛ አድርጎታል።
ከዚህ በፊት የጆርዳን ጫማ በውድ ዋጋ በጨረታ የተሸጠው እአአ በ2021 በ1.47 ሚሊዮን ዶላር ነበር።
ጥቁርና ቀይ ቀለም ያለው ጫማው ጆርዳን በፍጻሜ ጨዋታዎች የሚጫማው ነበር።
ጆርዳን ‘ጆርዳን’ የተሰኘውን ጫማ ማድረግ የጀመረው እንደ አውሮፓውያኑ በ1984 ከቺካጎ ቡልስ ቡድን ጋር ነው።
በተከታዩ ዓመት ኤይር ጆርዳን I የተሰኘው ጫማ ለገበያ ቀርቧል። እስካሁንም ድረስ ጫማው ከ30 በላይ በሆኑ አይነቶች ቀርቧል።
ጆርዳን 6 የአሜሪካ ቅርጫት ኳስ ውድድሮችን አሸንፏል። ሁለት የኦሎሚፒክ የወርቅ ሜዳሊያዎችን እና በርካታ ሽልማቶችን አግኝቷል።
ማይክል ጆርዳን የምንግዜም ምርጡ የቅርጫት ኳስ ተጫዋች እንደሆነ በስፋት ይታመናል።