ሩሲያ 'ግዙፍ' የኒውክሌር ጥቃት ልምምድ ማድረጓን አስታወቀች

ሩሲያ “ግዙፍ” የኒውክሌር ጥቃት የማድረስ አቅሟን የሚፈትሽ ልምምድ ማከናወኗን አስታወቀች።

ወታደራዊ ልምምዱ ለጠላት የኒውክለር ጥቃት ምላሽ መስጠትን እንደሚያካትት የመከላከያ ሚንስትሩ ሰርጌይ ሾይጉ አስታውቀዋል።

ሚንስትሩ ለፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ልምምዱን በተመለከተ ማብራሪያ ሲሰጡ በመንግስታዊው ቴሌቭዥን ታይተዋል።

ሞስኮ የኒውክለር መሣሪያዎችን እንዳትሞክር ከሚያግዳት ዓለም አቀፍ ስምምነት መውጣቷ በአገሪቱ ፓርላማ ማጽደቁን ተከትሎ የተደረገ ልምምድ መሆኑ ተሰምቷል።

ሩሲያ እና አሜሪካ በመደበኛነት የኒውክለር ዝግጁነታቸውን የሚያሳይ አምሳለ ልምምድ ያከናውናሉ። ሞስኮ ልምምዷን የምታከናውነው ጥቅምት መጨረሻ ላይ ነው።

የዘንድሮው ልምምድ “በስትራቴጂክ ሃይሎች ላይ ግዙፍ የኒውክሌር ጥቃት ማድረስ እና ለጠላት የኒውክልር ጥቃት ምላሽ መስጠትን” እንደሚያካትት ሾይጉ ለፕሬዝዳንት ፑቲን ተናግረዋል።

በክሬምሊን መግለጫ መሠረት “ተግባራዊ የባሊስቲክ እና የክሩዝ ሚሳኤሎች ሙከራም” ተካሂዷል።

ያርስ የተባለው አህጉር አቋራጭ ባልሰቲክ ሚሳኤል ከሩሲያ ሩቅ ምስራቅ አቅጣጫ ከሚገኝ የሙከራ ቦታ ተወንጭፏል።

ሌላኛው ሚሳኤል የተወነጨፈው በባሪንትስ ባህር ከሚገኘው የኒውክሌር ሃይል ከሚንቀሳቀስ ባህር ሰርጓጅ መርከብ መሆኑን መግለጫው አስታውቋል።

ፕሬዝዳንት ፑቲን በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ሩሲያ በኒውክሌር ሃይል የሚንቀሳቀስ የክሩዝ ሚሳኤል “የተሳካ የመጨረሻ ሙከራ አድርጋለች”ብለዋል።

እአአ በ2018 ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ የሆነው መሣሪያ በየትኛው የዓለም ክፍል ያለን ዒላማ መምታት ይችላል ተብሎ ቢወደስም፤ የፕሬዝዳንት ፑቲን ሃሳብ ግን በየትኛውም ወገን አልተረጋገጠም።

የአሁኑ ሙከራዎች ሞስኮ ከዓለም አቀፍ ኒውክለር ስምምነቶች ከመውጣቷ ጋር ተገጣጥሟል።

የአገሪቱ ፓርላማ ረቡዕ ዕለት ሩሲያ ከስምምነቱ የወጣችበትን ህግ አጽድቆ አጠናቋል።

እአአ በ1996 ከስምምነት የተደረሰው ዓለም አቀፍ ህግ በየትኛውም ቦታ የሚደረግን “የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ሙከራ ወይም ሌላ ማንኛውም የኒውክለር ፍንዳታ” ይከለክላል።

ሩሲያ ባለፈው ዓመት ዩክሬንን መውረሯን ተከትሎ የኒውክሌር ጦርነት ስጋት ተፈጥሯል።

ሩሲያ የመጀመሪያውን ታክቲካል የኒውክሌር ጦር መሣሪያ በቤላሩስ አስቀምጣለች። የሩሲያ የግዛት አንድነት ስጋት ላይ ከወደቀ ብቻ ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ፑቲን መናገራቸው ይታወሳል።

ክሬምሊን በኒውክሌር ጦር ዩክሬንን ለማጥቃት ማቀዷን የሚጠቁም ነገር አለመኖሩን የአሜሪካ መንግስት አስታውቋል።