'የሠራተኞችን ኑሮ ያላገናዘበ ነው' የሚል ተቃውሞ የቀረበበት የገቢ ግብር አዋጅ፤ ማሻሻያ ሳይደረግበት ጸደቀ

ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት

የፎቶው ባለመብት, House of Peoples Representatives of FDRE

ከሁለት ሳምንት በፊት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው እና 'ሠራተኞች ላይ ያለውን የኑሮ ውድነት ጫና ያላገናዘበ ነው' በሚል ተቃውሞ ሲቀርብበት የነበረው የገቢ ግብር ረቂቅ አዋጅ፤ ከደመወዝ የሚቆረጠውን ታክስ በተመለከተ ማስተካከያ ሳይደረግበት ጸደቀ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ረቂቅ አዋጁን ያጸደቀው "በ12 ድምጽ ተአቅቦ እና በአምስት ተቃውሞ በአብላጫ ድምፅ" እንደሆነ ተዘግቧል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ ከቅጥር ላይ ከሚገኝ ገቢ ግብር የሚከፈልበት ደረጃ ላይ አነስተኛ ማሻሻያ ያደረገውን አዋጅ ያጸደቀው ዛሬ ሐምሌ 10/2017 ዓ.ም. ባደረገው አስቸኳይ ጉባኤ ነው።

በ2008 ዓ.ም. የወጣውን የገቢ ግብር አዋጅ ያሻሻለው ይህ ረቂቅ፤ ለውጥ ካደረገባቸው ጉዳዮች አንዱ ከቅጥር የሚሰበሰብ ገቢን የሚመለከተው ይገኝበታል።

አዲሱ አዋጅ ከግብር ነጻ የሚሆንን ደመወዝ ከነበረበት 600 ብር ወደ ሁለት ሺህ ብር ከፍ አድርጓል። በሀገሪቱ ከፍተኛ የሆነው 35 በመቶ ግብር መጣል የሚጀምርበትን የደመወዝ መጠን ደግሞ ቀድሞ ከነበረበት 10,900 ብር ወደ 14 ሺህ ብር ከፍ አድርጓል።

ይህ ከዘጠኝ ዓመት በኋላ የተደረገው ማሻሻያ፤ ከግብር ነጻ በሚሆነው እና ከፍተኛ ግብር በሚጣልበት የደመወዝ መጠን ላይ ያደረገው ለውጥ ዝቅተኛ ነው የሚል ቅሬታ ቀርቦበታል።

ይህ ቅሬታ አዋጁ ለምክር ቤቱ ከመቅረቡ በፊት በተደረገ ውይይት ላይም ተነስቶ የነበረ ሲሆን፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኞ ሐምሌ 7 ቀን በረቂቁ ላይ ውይይት ባደረገበት ወቅት በተገኙ ተሳታፊዎችም በከፍተኛ መጠን ተንጸባርቋል።

በዚህ ውይይት ላይ ተቃውሟቸውን ካሰሙት ተሳታፊዎች መካከል የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ይጠቀሳሉ።

ሠራተኞች በአሁኑ ሰዓት ያለውን የኑሮ ውድነት ጫና መቋቋም እንዳልቻሉ የተናገሩት አቶ ካሳሁን፤ "ለፓርላማው የቀረበው ከሠራተኞች የሚቆረጥ የገቢ ግብር ረቂቅ አዋጅ አሁን [ያለውን] ውስብስብ የዋጋ ንረት እና የድህነት መጠንን ያላገናዘበ [ነው]" ሲሉ ተችተዋል።

አሁን ከግብር ነጻ በሚሆን የደመወዝ መጠን ላይ የተደረገው ማሻሻያ ከመንግሥት ዝቅተኛ የደመወዝ ምጣኔ ጭምር የሚያንስ እንደሆነ የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ፤ ይህ የደመወዝ መጠን ሁለት ሺህ ብር የተደረገበት ምክንያትም "ትክክልም አሳማኝም እንዳልሆነ" ተናግረዋል።

"የዛሬ 10 ዓመት 600 ብር ማለት የዚያን ጊዜ ዶላር 20 ብር በነበረበት ሰዓት ነው የተቀመጠው። ዛሬ ዶላር ስንት ብር ነው?" ሲሉም ጠይቀዋል።

ፕሬዝዳንቱ፤ ግብር ሲጣል የሚሰበሰበው ገቢ ብቻ ሳይሆን የሠራተኛው የመክፈል አቅምም መታየት እንዳለበት በመጥቀስ፤ "ቁጥርን ሳይሆን የሰውን ሕወይት እዩ፣ የሰውን ኑሮ እዩ። ስሌቱ ሰውን ማኖር አለበት" ብለዋል።

14 ሺህ ብር ደመወዝ በሚያገኙ ሠራተኞች ላይ እንዲጣል የቀረበውን 35 በመቶ ግብር በማንሳት እነዚህ ሠራተኞች በሚገዙት እቃ ውስጥ የሚከፍሉት 15 በመቶ የተጨማሪ እሴት ታክስ (ቫት)፣ እና ለጡረታ የሚከፍሉት ሰባት በመቶ መዋጮ ሲቆረጥ በአጠቃላይ ከደመወዛቸው ውስጥ 57 በመቶው ግብር ላይ እንደሚውል አስረድተዋል።

የሁለት መቶ ብር ኖቶችን የሚቆጥር ወንድ እጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"15 ሺህ ብር ደመወዝ የሚያገኝ ሰው አሁን ከደመወዙ ላይ 57 ፐርሰንት [ግብር] ይቆረጣል። 57 ፐርሰንት ተቆርጦ፤ በ43 ፐርሰንት ቤት ኪራይ ከፍሎ፣ ልጆች አስተምሮ ይኖራል ወይ? ሌላውን ትተን ለምግብ ብቻ ይበቃል ወይ?" ሲሉ በአጽንኦት አንስተዋል።

"የኢትዮጵያ ሠራተኞች አልቻሉም። ማታ ከሥራ ወጥተው ቋሚ ኮሚቴው ፈቃደኛ ከሆነ [ሠራተኞች] ከሥራ ሲወጡ ቆመን፣ አብረን ማየት እንችላለን። አንዳንድ ሠራተኞች ከሥራ ወጥተው ፌስታል ይዘው ሆቴል አካባቢ ይለምናሉ" ሲሉም ተደምጠዋል።

"የድህነት ወለልን መነሻ በማድረግ" ግብር መጣል የሚጀምርበት የደመወዝ መጠን "ከ8,334 ብር" ጀምሮ እንዲሆን የጠየቁት አቶ ካሳሁን፤ በተጨማሪም ሠራተኞች ከድርጅቶች እኩል 35 በመቶ ታክስ እንዳይከፍሉ እንዳይደረግ ምክረ ሃሳባቸውን አቅርበዋል።

አቶ ካሳሁን፤ ረቂቁ ለፓርላማ ከመቅረቡ በፊት በተደረጉ ውይይቶች የቀረቡ ምክረ ሃሳቦች ተሰምተው ማሻሻያ እንዳልተደረገባቸው አስታውሰው፤ "[ያሉንን] ሰምተን መጣን እንጂ ያልናቸውን አልሰሙንም። ሕዝብ ተወያይቷል ይባላል። ስንወያይ እኮ ለውጥ መኖር አለበት" ሲሉም ተችተዋል።

በኢሠማኮ ፕሬዝዳንት እና ሌሎች ተሳታፊዎች ተመሳሳይ ተቃውሞ ከቀረበበት ውይይት ሦስት ቀናት በኋላ በተካሄደው የፓርላማ ስብሰባ ረቂቁ እንዲጸድቅ የቀረበው፤ የሠራተኞች ደመወዝ ላይ የሚጣለውን ግብር በተመለከተ ማሻሻያ ሳይደረግ ነው።

የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አዋጁ እንዲጸድቅ ፓርላማው ባቀረበው የውሳኔ ሀሳብ እንደሚያመለክተው፤ ሌሎች ጉዳዮችን በሚመለከቱ የረቂቁ ክፍሎች ላይ ማስተካከያዎች ተደርገዋል። በመቀጠር በሚገኝ ገቢ ላይ ተፈጻሚ የሚሆን ግብር ምጣኔን የሚመለከተውን የአዋጁን አንቀጽ 11 በተመለከተ በውሳኔ ሃሳቡ ላይ የተጠቀሰ ማስተካከያ የለም።

አዲሱ አዋጅ "የታክስ መሠረትን በማስፋት፣ የመንግሥት ገቢ አሰባሰብን በማሻሻል እና የታክስ ፍትሐዊነትን በማረጋገጥ የመንግሥትን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የሚያስችሉ ድንጋጌዎች በውስጡ" እንደያዘ በውሳኔ ሃሳቡ ላይ ተጠቅሷል።

"ስለሆነም ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ምቹ እና ቀላል የታክስ ሥርዓትን በመዘርጋት ለሀገራችን የተሻለ ኢኮኖሚ ለመፍጠር የሚሞክር መሆኑ በቋሚ ኮሚቴው ታምኖበታል" ያለው ቋሚ ኮሚቴው፤ "ረቂቅ አዋጁን ከቀረበው ማስተካከያ ጋር በሙሉ ድምፅ" እንደተቀበለው አስታውቋል።

ይህ የፕላን ፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የውሳኔ ሃሳብ የቀረበለት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም የገቢ ግብር ማሻሻያ አዋጁን "በ12 ድምጽ ተአቅቦ እና በ5 ተቃውሞ በአብላጫ ድምፅ" እንዳጸደቀው ብሔራዊው ቴሌቪዥን ዘግቧል።