ከፍተኛ የገቢ ግብር መጣል የሚጀምርበት የደመወዝ መጠን ወደ 14 ሺህ ብር ከፍ ሊደረግ ነው

የሁለት መቶ ብር ኖቶችን የሚቆጥር ወንድ እጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከሠራተኞች ደመወዝ ላይ የሚሰበሰበው ከፍተኛው 35 በመቶ ታክስ፤ መቆረጥ የሚጀምርበት የደመወዝ እርከን ከ10,900 ብር ወደ 14 ሺህ ብር ከፍ እንዲል የሚያደርግ ረቂቅ ሕግ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ።

ይህ ከፍተኛ ግብር መቆረጥ የሚጀምርበት የደመወዝ እርከን ከዚህ በላይ ከፍ ያልተደረገው "በተለይ በክልል መንግሥታት ገቢ ላይ ከፍተኛ ጫናን ስለሚሳያድር" እንደሆነ ተገልጿል።

በኢትዮጵያ የደመወዝ ገቢ ታክስ ምጣኔ የመጨረሻው ደረጃ የሆነው 35 በመቶ ግብር፤ ከ11 ሺህ ብር ገደማ ጀምሮ መቆረጥ እንዲጀምር የተደረገው በ2008 ዓ.ም. በወጣው የገቢ ግብር አዋጅ ነው።

ከዘጠኝ ዓመት በፊት የወጣውን ይህንን አዋጅ የሚያሻሽል ረቂቅ ሕግ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ባለፈው ሳምንት አርብ ሰኔ 27/2017 ዓ.ም. በተካሄደው ልዩ ስብሰባ ነው።

ይህ ረቂቅ አዋጅ የተዘጋጀው፤ ከግብር እና ቀረጥ የሚገኘው ገቢ ከዓመታዊ ጠቅላላ ምርት ያለውን ዝቅተኛ ድርሻ በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ውስጥ ወደ 11 በመቶ ለማድረስ በፌደራል መንግሥት የተዘጋጀው ስትራቴጂ "አንድ ክፍል" በመሆኑ እንደሆነ በማሻሻያ ማብራሪያ ላይ ተጠቅሷል።

አዋጁ "ሥራ ላይ ከዋለ ከዘጠኝ ዓመታት በላይ ያሳለፈው በመሆኑ ካለንበት የኢኮኖሚ ሁኔታ እና ከንግዱ ውስብስብ ባህሪ አንጻር ሲታይ በርካታ ክፍተቶች" እንዳሉበት ማብራሪያው ያስረዳል።

"ከዲጂታል ኢኮኖሚው ጋር የተጣጣመ ዘመናዊ የታክስ መሠረት" መፍጠርን ዓላማው ያደረገው ረቂቅ አዋጅ፤ "ለታክስ ማጭበርበር በር የሚከፍቱ አሠራሮችን መቀየርንም" ግቡ እንዳደረገ በማብራሪያው ላይ ሰፍሯል።

በረቂቅ ሕጉ ማብራሪያ ላይ በቀዳሚነት የተጠቀሰው "ከመቀጠር፣ ከቤት ኪራይ እና ከግለሰብ ንግድ ሥራ" በሚገኙ ገቢዎች ላይ በሚጣለው ታክስ ላይ የተደረገው ማሻሻያ ነው። በነባሩ አዋጅ ላይ ያለው "የማስከፈያ መጣኔው እና የገቢ ቅንፉ (income bracket) አሁን ካለው የገንዘብ የመግዛት አቅም ጋር የሚሄዱ" እንዳልሆኑ ማብራሪያው ያስረዳል።

አሁን በሥራ ላይ ባለው ሕግ መሠረት በመቀጠር በሚገኝ ገቢ በተለያየ ደረጃ ከ10 እስከ 35 በመቶ ግብር ይጣልበታል። እስከ 600 ብር ያለው ገቢ ከግብር ነጻ ሲሆን፣ ከ601 እስከ 1,650 ብር ያለው የደመወዝ ገቢ ደግሞ 10 በመቶ ግብር ይቆረጥበታል።

ግብር የሚቆረጥበት የደመወዝ እርከን ስድስት ደረጃዎች ያሉት ሲሆን፣ የመጨረሻው የግብር ምጣኔ 35 በመቶ ነው። ይህ የ35 በመቶ ግብር የሚቆረጠው ከ10,900 ብር በላይ ደመወዝ ከሚያገኙ ሠራተኞች ላይ እንደሆነ በሥራ ላይ ባለው አዋጅ ላይ ሰፍሯል።

አሁን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የአዋጅ ማሻሻያ ቀድሞም የነበረው ከ10 እስከ 35 በመቶ የሚደርስ የገቢ ግብር ምጣኔ አስቀጥሏል። ረቂቅ ማሻሻያው ያተኮረው እነዚህ የግብር ምጣኔዎች በሚያርፍባቸው የደመወዝ እርከኖች ላይ መጠነኛ ማስተካከያ ማድረግ ላይ ነው።

በዚህም መሠረት ከግብር ነጻ የሚሆነውን በመቀጠር የሚገኝ ዝቅተኛ ደመወዝ ከነበረበት 600 ብር ወደ 2,000 ብር አሳድጓል።

ከፍተኛው የግብር ምጣኔ የሆነው 35 በመቶ የሚጀምርበት የ10,900 ብር ገቢ ላይ ደግሞ የ3,100 ብር ጭማሪ ተደርጓል። ማብራሪያው፤ "ከፍተኛው የማስከፈያ መጣኔ የሆነው 35 በመቶ የሚያርፍበት ከመቀጠር የሚገኝ ገቢ ደግሞ ወደ ብር 14,000 ከፍ እንዲል ሆኗል" ሲል የተደረገውን ማሻሻያ ያስረዳል።

ዋሌት ውስጥ የተቀመጡ የ200፣ 100፣ 50 እና 10 ብር ኖቶች

የፎቶው ባለመብት, AFP

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ማብራሪያው እንደሚያመለክተው፤ ይህንን ረቂቅ አዋጅ በተመለከተ በተካሄደ "የሕዝብ አስተያያት መስጫ መድረክ" ላይ "ከግብር ነጻ የሚሆነው ከመቀጠር የሚገኝ ገቢ በከፍተኛ መጠን እንዲያድግ" ሀሳብ ቀርቦ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ሀሳብ ተቀባይነት እንዳላገኘ ማብራሪያው ይገልጻል።

"[ይህ ሀሳብ] በዚህ ምክንያት የሚታጣውን የመንግሥት ገቢ ከግምት ውስጥ ያላስገባ እና በሌላ ገቢ ሊካካስ በማይችልበት ደረጃ ገቢን የሚቀንስ በመሆኑ ለመቀበል አልተቻለም" ሲልም ምክንያቱን ያስረዳል።

አሁን በሥራ ላይ ያለው የገቢ እና ታክስ ምጣኔ ከነባራዊው "የገንዘብ የመግዛት አቅም ጋር የሚሄድ" እንዳልሆነ የሚጠቅሰው ማብራሪያው፤ ይሁን እንጂ አሁን በረቂቅ ከተቀመጠው መጠን በላይ ማሻሻያ ማድረግ በመንግሥት ገቢ ላይ ያስከትላል ያለውን ጉዳት ያብራራል።

ማብራሪያው፤ "መንግሥት በተለይም የክልል መንግሥታት" ከሚሰበስቡት ገቢ ውስጥ ከደመወዝ ላይ ከሚቆረጥ ግብር "የሚሰበሰበው ትልቅ ድርሻ" እንዳለው ያነሳል። "በመሆኑ መጣኔውን መቀነስ ወይም የገቢ ቅንፉን ማሳደግ በመንግሥት በተለይም በክልል መንግሥታት ገቢ ላይ ከፍተኛ ጫናን እንደሚያሳድር" አመልክቷል።

በዚህም ምክንያት ይህንን በተመለከተ የሚደረግ ማሻሻያ "በጥንቃቄ መታየት አለበት" የሚለው ማብራሪያው፤ ይህ ማሻሻያ የተደረገው ሁለት ጉዳዮችን ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነ ይጠቅሳል።

"በመሆኑም ተቀጣሪው በኑሮ ውድነት ምክንያት ያለበትን ጫና በአንድ በኩል፤ የመንግሥት ገቢ በከፍተኛ ደረጃ መሸርሸር፣ በመንግሥት አገልግሎቶች ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ በሌላ በኩል ከግምት ውስጥ በማስገባት ሰንጠረዦቹ ላይ ሚዛኑን የጠበቀ ማስተካከያ ተደርጓል" ሲል የተደገውን አነስተኛ ማሻሻያ አመክንዮ ያስረዳል።

ከዚህም በተጨማሪ ከኪራይ እና ከግለሰብ ንግድ በሚገኝ ዓመታዊ ገቢ ላይ ተመሳሳይ ማሻሻያ መደረጉን ማብራሪያው ገልጿል። እነዚህ ማሻሻያዎች "ምክንያት መንግስት የሚያጣው ገቢ ከአገራዊ ጠቅላላ ምርት 0.21 በመቶ" ያህል እንደሚሆን ተጠቅሷል።

ማብራሪያው፤ "ከዚህ በላይ ማስተካከያ ይደረግ ቢባል በመንግስት አገልግሎቶች ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ውጤትን የሚያስከትል ይሆናል" ይላል። አሁን በተደረገው ማሻሻያ "ምክንያት የሚታጣውን ገቢ የግብር መሰረትን ለማስፋት በአዋጁ በተወሰዱ ማስተካከያዎች እና የታክስ አስተዳደሩን ውጤታማ በማድረግ ማካካስ እንደሚቻል" እምነት እንደተያዘም ተገልጿል።

በአርብ ዕለቱ ልዩ ስብሰባ ይህ ረቂቅ የቀረበለት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ ህጉን ለዝርዝር እይታ ለፕላን በጀትና ፋይናንስ ቋሚ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል። ፓርላማው ዛሬ ሰኞ ሰኔ 30/2017 ዓ.ም. የስራ ጊዜ የሚጠናቀቅ በመሆኑ ረቂቅ አዋጁ መታየት የሚጀምረው ምክር ቤቱ በሚቀጥለው ዓመት መስከረም ወር ወደ ስራ ሲመለስ እንደሆነ ይጠበቃል።