የውጭ አገር ዜጎች በአንድ ጊዜ ከአንድ በላይ መኖሪያ ቤት እንዳይኖራቸው የሚከለክል አዋጅ ጸደቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ አገር ዜጎች በአንድ ጊዜ ሊኖራቸው የሚችለው የመኖሪያ ቤት ከአንድ በላይ እንዳይሆን የሚደነግግ አዋጅን አጸደቀ።
ምክር ቤቱ የውጭ አገር ዜጎች የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሚሆኑበትን አግባብ ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ያጸደቀው ዛሬ ማክሰኞ፣ ሰኔ 24/ 2017 ዓ.ም ነው።
ባለፈው ግንቦት ወር አጋማሽ ላይ ለፓርላማው ቀርቦ የነበረው አዋጅ ዛሬ ሲጸድቅ ከአዋጁ ስያሜ ጀምሮ የተወሰኑ ማሻሻያዎች በቋሚ ኮሚቴዎች ተደርገውበታል።
የቀድሞው ረቂቅ ከመኖሪያ ቤት በተጨማሪ የውጭ ዜጎች የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት የሚሆኑበትንም ድንጋጌዎች የያዘ ነበር።
ሆኖም አዋጁ ለዝርዝር እይታ የተመራላቸው የምክር ቤቱ ከከተማ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች እና ከህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች የአዋጁ ዋና ትኩረት በመኖሪያ ቤት ብቻ ላይ እንዲሆን አድርገው አሻሽለውታል።
ቋሚ ኮሚቴዎች ባቀረቡት የውሳሄ ሃሳብ ላይ የማይንቀሳቀስ ንብረት የሚለዉ ሀረግ ሙሉ በሙሉ እንዲወጣ ተደርጓል።
የውሳኔ ሃሳቡ ይህ የሆነበት ምክንያት "የማይንቀሳቀስ ንብረት የሚለው ሀረግ አሻሚ በመሆኑ አላስፈላጊ ትርጉም ስለሚፈጥር በዚህ መልኩ ማስቀመጥ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ" ስለመሆኑ አብራርቷል።
ከዚህ በተጨማሪም በረቂቅ አዋጁ 'የማይንቀሳቀስ ንብረት'ን የሚመለከተው የትርጓሜ ንዑስ አንቀጽ እንዲሰረዝ ተደርጓል።
በረቂቁ ለማይንቀሳቀስ ንብረት የተሰጠው ትርጓሜ "በውጭ ዜጋ በሊዝ ባለይዞታነት ወይም ባለቤትነት የሚያዝ መሬት ወይም የመኖሪያ ቤት" እንዲሁም "ተያያዥ ግንባታዎች" የሚል ነበር።
የውሳኔ ሃሳቡ በረቂቅ አዋጁ ውስጥ ከማይንቀሳቀስ ንብረት ጋር የተያያዙትን ድንጋጌዎች በሙሉ ትኩረታቸው የመኖሪያ ቤት ላይ ብቻ እንዲሆን አድርጓል።
የውጭ አገር ዜጋ የመኖሪያ ቤት ባለቤት መብትን የሚመለከተው የአዋጁ ድንጋጌ ላይ አዲስ ንዑስ አንቀጽ ተጨምሮበታል።
በዚህ ንዑስ አንቀጽ መሰረት የውጭ አገር ዜጋ የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሚሆነው "በሊዝ በጨረታ ሥርዓት ብቻ ነው"።
የውጭ ሃገር ዜጋ የቤት ግንባታ ማከናወን የሚችለው "በሊዝ ጨረታ በሚሰጥ መሬት እንጂ በምደባ ወይም ተመሳሳይ አሰራር እንዳልሆነ ለመግለፅ" አዲሱ ንዑስ አንቀጽ መካተቱን የውሳኔ ሃሳቡ ያስረዳል።
ከዚህ በተጨማሪም የውጭ አገር ዜጎች ሊኖራቸው የሚችለው የመኖሪያ ቤት ቁጥር ላይ ገደብ ተቀምጧል። ከአንድ ወር ገደማ በፊት ለፓርላማ በቀረበው ረቂቅ አዋጅ፤ የውጭ አገር ዜጋ "በአንድ ጊዜ የሚኖረው ከፍተኛ የማይንቀሳቀስ ንብረት ቁጥር በመመሪያ እንዲወሰን የተተወ ነበር።
ነገር ግን ቋሚ ኮሚቴዎቹ ያቀረቡት የውሳኔ ሃሳብ "ማንኛውም የውጭ ሃገር ዜጋ በማናቸውም በአንድ ጊዜ የሚኖረው የመኖሪያ ቤት ቁጥር አንድ" ነው የሚል ገደብ አስቀምጧል።
ነገር ግን የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር "ከሃገር ጥቅም አንፃር አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው" ቁጥሩን በመመሪያ የማሻሻል ሥልጣን ተሰጥቶታል።
የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለመሆን መሟላት የሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ላይም አዲስ መስፈርት ተካትቶበታል።
አንድ የውጭ አገር ዜጋ የቤት ባለቤት ለመሆን "ከሃገር ሰላም፣ ደኅንነት፣ ጸጥታ እና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር የሚያያዝ የክልከላ ገደብ የሌለበት መሆን" እንደሚገባው አዋጁ ያትታል።
ከዚህ በተጨማሪ የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሆኑ የውጭ አገር ዜጎች መብቶችን የሚመለከተው የአዋጁ ክፍል ላይ፤ የውጭ አገር ዜጎች መኖሪያ ቤታቸውን የማከራየት መብት ቢኖራቸውም፤ "መኖሪያ ቤቱን ለንግድ ዓላማ ማዋል" እንደማይችሉ ግልጽ ድንጋጌ ተቀምጧል።
ከዚህ በተጨማሪም የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለመሆን በሊዝ መሬት የሚያገኙ የውጭ አገር ዜጎች "አጠቃላይ የሊዝ ዋጋውን በአንድ ጊዜ የመክፈል" ግዴታ አለባቸው።
ይህ ግዴታ የተጣለባቸው "ክልሎች ወይም ከተሞች የሊዝ ክፍያውን ባንድ ጊዜ የሚያገኙበትን እድል መፍጠር ስለሚያስችል" እንደሆነ የውሳኔ ሀሳቡ ላይ ሰፍሯል።
በረቂቅ አዋጁ የውጭ አገር ዜጎች የሊዝ፣ የቤት ግዢ፣ የግንባታ ፈቃድ እንዲሁም ተያያዥ የመንግሥታዊ አገልግሎት ክፍያዎችን በውጭ ምንዛሪ ብቻ ነበር መክፈል ያለባቸው።
በውሳኔ ሃሳቡ መሰረት ዜጎች የሊዝ፣ የቤት ግዢ፣ የግንባታ ፈቃድ ክፍያዎች እንዳሉ ሆነው በውጭ ምንዛሪ መክፈል የሚጠበቅባቸው መንግሥታዊ አገልግሎት ግን "የመጀመሪያው ዓመት" አግልግሎትን ብቻ እንዲሆን ተደርጓል።
አዋጁ በረቂቂ ውስጥ ያልነበረ እና ለክልሎች ሥልጣን እና ኃላፊነት የሚሰጥ አዲስ አንቀጽ አካትቷል።
በዚህ መሰረት ክልሎች አዋጁን ድንጋጌዎች በክልላቸው እና በከተሞቻቸው የማስፈጸም፣ ለተግባራዊነቱ "ተገቢ ክትትልና ድጋፍ" የማድረግ የውጭ ሃገር ዜጎች ንብረት ይዞታን በተመለከተ "በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊ አሰራር" የመመስረት ኃላፊነት አለባቸው።















