የአሜሪካ የባሕር ኃይል የቻይና የስለላ ፊኛ ስብርባሪ ምስሎችን ለቀቀ

የፊኛው ስብርባሪ

የፎቶው ባለመብት, US FLEET FORCES COMMAND

የአሜሪካ የባሕር ኃይል ቅዳሜ ዕለት የተመታውንና የስለላ እንደሆነ የተጠረጠረውን የቻይና ፊኛ ስብርባሪዎችን ምስሎች ለቀቀ።

የአሜሪካ አየር ኃይል ኮማንድ የፊኛውን ስብርባሪዎች የሚያሳይ በርካታ ፎቶዎችን በፌስቡክ ገጹ ያጋራ ሲሆን፤ የፊኛውን ትላልቅ ስብርባሪዎች ወደ ጀልባ ሲጎትቱ አሳይተዋል።

በፌስቡክ ገጹ ፎቶዎችን ባጋራበት ጽሑፉም እሁድ ዕለት የፊኛውን ስብርባሪ ያወጡት መርከበኞች የባሕር ኃይል ልዩ የፈንጂ ባለሙያዎች ቡድን አካል መሆናቸውን ገልጿል።

ፊኛው የስለላ መሣሪያ መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥም ስብርባሪዎቹ ላይ ምርመራ እንደሚደረግ ተገልጿል።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት እንዳሉት ፊኛው ወደ 200 ጫማ ( 60 ሜትር) ቁመት ፣ የመጫኛው ክፍሉ በመጠን ከአነስተኛ አውሮፕላን ጋር የሚስተካከል ሲሆን በመቶዎች ምን አልባትም በሺዎች የሚቆጠር ፓውንድ ክብደት አለው።

ቻይና "የአየር መርከብ" ስትል የገለጸችው ፊኛ የስለላ እንዳልሆነ እና የአየር ንብረት ጥናት የሚሰራ፣ ነገር ግን ባጋጠው መጥፎ የአየር ጠባይ በድንገት ወደ አሜሪካ ክልል የገባ መሆኑን በተደጋጋሚ አስታውቃለች።

ማክሰኞ ዕለት የአሜሪካ ባለሥልጣናት እንዳሉት ፊኛው ተመትቶ እንዲወድቅ ከተደረገ በኋላ የአሜሪካ መከላከያ መሥሪያ ቤት ( ፔንታገን) በመከላከያ ሚኒስትር ሊሎይድ ኦስቲን እና በቻይናው አቻቸው መካከል በስልክ ውይይት ለማድረግ ታቅዶ የነበረ ሲሆን ቻይና ግን ፈቃደኛ ሳትሆን ቀርታለች።

የመከላከያ ዋና ጸሐፊ ብርጋዲየር ጄነራል ፓትሪክ ራይደር “በእንዲህ ዓይነት ወቅት መስመሮችን አለማለፍ አስፈላጊ ነው፤ ነገር ግን በሚያሳዝን ሁኔታ የቻይና መንግሥትም ያቀረብነውን ጥያቄ አልተቀበለም” ብለዋል።

የቻይና ፊኛው በአሜሪካ የአየር ክልል መገኘት ዲፕሎማሲያዊ ቀውስ ያስከተለ ሲሆን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ለስብሰባ ወደ ቻይና ሊያደርጉት የነበረውን ጉዞ ሰርዘዋል።

ስብሰባው በአሜሪካ እና በቻይና መካከል “ኃላፊነት በጎደላቸው እርምጃዎች” ዙሪያ ለመነጋገር በዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ይካሄዳል የተባለ ከፍተኛ ስብስባ ነበር።

የፊኛው ስብርባሪ

የፎቶው ባለመብት, US FLEET FORCES COMMAND

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አሜሪካ መትታ የጣለችው ፊኛ ስብርባሪ ከአንድ ቀን በኋላ በደቡብ ካሮላይና ግዛት ማይርትል የባሕር ዳርቻ ላይ ተገኝቷል።

የባሕር ኃይሉ እንዳለው ከአትላንቲክ ውቅያኖስ 11 ኪሎ ሜትር ቦታ እና በሁለት የባሕር ኃይለ መርከቦች ላይ የወደቀ ሲሆን አንደኛው መርከብም ለመነሳት ከባድ ክሬን አስፈልጎታል።

ይሁን እንጂ የወጡት ምስሎች እንደሚያሳዩት የፊኛውን ስብርባሪዎች በእጅ ተጎትተው የሚወጡም ናቸው።

የአሜሪካ ጦር የቀረ የፊኛውን ስብርባሪ ለመፈለግም ሰው አልባ የውሃ ውስጥ ተሽከርካሪዎችን አሰማርታለች።

ባለሙያዎች የፊኛው ስብርባሪዎች ፊኛው ምን እንደሚያደርግ እና መረጃዎችን እንዴት ማስተላለፍ እንደሚችል ለመረዳት እና የቻይና የስለላ ቴክኖሎጂንና ዘዴዎችን ለማወቅ ለአሜሪካ ጠቃሚ ሃሳብ ይሰጣል ብለዋል።

የፊኛውን መሣሪያዎች ለማግኘት የተደረገው ጥረት፣ የአሜሪካ ሠራተኞች እንደ ፈንጂ ወይም የባትሪ አካላት ካሉ አደገኛ ነገሮች እንዲጠበቁ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ ውስብስብ ሆኖ ቆይቷል።

የአሜሪካ መከላከያ ባለሥልጣናት ሐሙስ ዕለት ፊኛውን እየተከታተሉ መሆኑን አስታውቀው፣ፊኛው ተመትቶ በውሃው ላይ በሰላም እስኪወድቅ ድረስ ጠብቀዋል።

በአሜሪካ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ማሰራጫዎች የተላለፉ ምስሎች ፊኛው ከትንሽ ፍንዳታ በኋላ ሲወድቅ አሳይተዋል።

አርብ ዕለት ፔንታገን የቻይና ሁለተኛው የስለላ ፊኛ በላቲን አሜሪካ ኮስታሪካ እና ቬንዙዌላ የአየር ክልል ውስጥ መታየቱን አሳውቋል።

የኮሎምቢያ የአየር ኃይል ፊኛ እንደሆነ የታመነውንና የታየው ግዑዝ አካል ከአምስት ቀናት በፊት በአገሪቷ የአየር ክልል በ55 ሺህ ጫማ ከፍታ ላይ ታይቷል ብሏል።

ግዑዝ አካሉ የአየር ክልሉን ለቆ እስከሚወጣ ድረስ መከታተሉን ገልጾ፣ ለአገሪቷ የደኅንት ስጋት እንደማይሆን ገልጿል።