የሶማሊያ መንግሥት የኢትዮጵያ ወታደሮች ጦሬ ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል ሲል ወቀሰ

የሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ኃይሎች በሶማሊያ ብሔራዊ ጦር ላይ ጥቃት አድርሰዋል ሲል ወቀሰ።

ሚኒስቴሩ ሰኞ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ዱሎው በተባለችው የጁባላንድ ከተማ "የኢትዮጵያ ኃይሎች ጥቃት ፈፅመዋል" ሲል ወቅሷል።

መግለጫው እንደሚያትተው "ሰኞ ጥዋት 4፡00 አካባቢ የኢትዮጵያ ኃይሎች ዱሎው በሚገኘው የሶማሊያ ብሔራዊ ጦር መቀመጫ ላይ ያለምንም ትንኮሳ እና ያልተጠበቀ ጥቃት ፈፅመዋል" ብሏል።

"ይህ የታቀደበት እና ሆነ ተብሎ የተፈፀመ ጥቃት ሶስት ቁፍል የሶማሊያ ጦር፣ የብሔራዊ ደኅንነት ኤጀንሲ እና የሶማሊያ ፖሊስ ኃይል መቀመጫዎች ላይ የተፈፀመ ነው" ይላል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ "በጥቃቱ የሶማሊያ ኃይሎች ላይ ሞት እና ቁስለት ደርሷል እንዲሁም በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል" ብሏል። ነገር ግን በጥቃቱ ምን ያክል ሰዎች ሰለባ እንደሆነ አሊያም ጉዳት እንደደረሰባቸው አልጠቀሰም።

መግለጫው አክሎ የሶማሊያ መንግሥት "በአንካራ ስምምነት መሠረት የሰላም ሂደቱን ለማጠናከር እየጣረ ባለበት እና ከፍተኛ ልዑክ ወደ አዲስ አበባ ባለከበት ወቅት ነው ይህ ጥቃት የተፈፀመው" ብሏል።

በሌላ በኩል ኤኤፍፒ የዜና ወኪል የጁባላንድ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ "በሥፍራው የሚገኙት የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ጣልቃ የገቡት ባለሥልጣናት ለመጠበቅ ነበር" ማለታቸውን ዘግቧል።

የሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት ከፊል ራስ ገዝ የሆነችው ጁባላንድ ባለፉት ሳምንታት ግጭት ውስጥ መግባታቸው ይታወቃል።

ኤኤፍፒ፤ የጁባላንድ ደኅንነት ሚኒስትር ዩሱፍ ሁሴን ኦስማንን በዱሎው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ "ክስተቱ የተፈጠረው (የፌዴራል) ኃይሎች የጁባላንድ ግዛት ልዑካንን የጫነች አውሮፕላን መትተው እንዲጥሉ ትዕዛዝ መሰጠቱን ተከትሎ ነው" ማለታቸውን አስነብቧል።

ቢቢሲ ከኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

በሶማሊያ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዓሊ ኦማር የሚመራ የልዑካን ቡድን ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ሰኞ ታኅሣሥ 14/ 2017 ዓ. ም. ወደ አዲስ አበባ ማቅናቱ ተገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከሶማሊያ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አሊ ሞሃመድ ኦማር ጋር መወያየታቸውን የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከሶማሊያው አቻቸው አብዱላሂ ሞሐመድ ጋር መወያየታቸውን በማኅበራዊ ሚድያቸው ገልፀዋል።

የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኤክስ ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ፣ ልዑካኑ ወደ አዲስ አበባ ያቀኑት "በአንካራ ስምምነት የተገባውን ቃል ለማጠናከር" ነው ማለቱ ይታወሳል።

ነገር ግን የኢትዮጵያ ኃይሎች ፈፀሙት የተባለው ጥቃት "የአንካራ ስምምነት እንዲሁም የአፍሪካ ሕብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ሕግጋትን አልፎም የሁለቱን ሀገራት ጎረቤታዊ ግንኙነት የሚጥስ ነው" ሲል ወቅሷል።

የሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተፈፀመ ያለውን ጥቃት አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ መሰል ጥቃቶችን "በዝምታ እንደማይመለከት፤ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነቱን እንደሚያስከብር" ገልጿል።

ይህን ወቀሳ አስመልክቶ እስካሁን ከኢትዮጵያ መንግሥት የተሰጠ መግለጫ የለም።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቱርኩ ፕሬዝዳንት አቀራራቢነት አንካራ ላይ በተደረገ ውይይት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል።

ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይብ ኤርዶዋን ስምምነቱን "ታሪካዊ" በማለት በሁለቱ አገራት መካከል "ሰላም እና ትብብር ለማምጣት የመጀመሪያ እርምጃ" እንደሚሆን ተስፋቸውን ገልፀዋል።

በተያያዘ ዜና የግብፅ ወታደሮች በሶማሊያ በሚሰማራው የአፍሪካ ሕብረት የሰላም ሚሽን ልዑካን ውስጥ እንደሚካተቱ የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

"ከሶማሊያ መንግሥት በቀረበ ጥያቄ መሠረት ግብፅ በሰላም አስከባሪ ሚሽን ውስጥ ለመካተት ወስናለች" ሲሉ የውጭ ገዳይ ሚኒስትሩ ባድር አብድላቲ በጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል ይላል የሮይተርስ ዘገባ።

የአፍሪካ ሕብረት ስታቢላይዜሽን ኤንድ ሰፖርት ሚሽን (አውሶም) የተባለው የሰላም አስከባሪ ኃይል በሚመጣው የአውሮፓውያኑ አዲስ ዓመት በሶማሊያ ይሰማራል ተብሎ ይጠበቃል።

ባለፈው ዓመት ታኅሣሥ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የራስ ገዟ ሶማሊላንድ የቀድሞ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሂ የመግባቢያ ሰነድ መፈረማቸው አይዘነጋም። ስምምነቱ ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ ዕውቅና እንደምትሰጥ በምትኩ ሶማሊላንድ ለኢትዮጵያ የባሕር በር እንደምትከፍት ያትታል።

ይህን ሰነድ ተከትሎ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ያለው ውጥረት የከረረ ሆኖ ቆይቷል። የሶማሊያው ፕሬዝደንት ሐሰን ሼኽ ሞሐመድ ከግብፁ አቻቸው አል ሲሲ እና ከኤርትራው መሪ ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ያላቸውን ግንኙነት አጠናክረዋል።

በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ያለው ውጥረት አሳስቦኛል ያለችው ቱርክ ሁለቱን ሀገራት ስታደራድር ቆይታ ታኅሣሥ 2/2017 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና እና የሶማሊያው ፕሬዝደንት ሐሰን ሼኽ ሞሐመድ በተገኙበት የአንካራ ስምምነት ተፈርሟል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በዱሎው ግዛት ፈፀመው ስለተባለው ጥቃት እንዲሁም የሶማሊያ ከፍተኛ ልዑካን ቡድን ወደ አዲስ አበባ ስለማቅናቱ ያለው ነገር የለም።