በነዳጅ እና በርችት የተሞላ ሳይበርትራክ ላስ ቬጋስ በሚገኘው የትራምፕ ሆቴል ፊት ለፊት ፈነዳ

በላስ ቬጋስ ኔቫዳ በሚገኘው የትራምፕ ሆቴል ደጃፍ በነዳጅ እና በርችት የተሞላ የቴስላ ሳይበርትራክ ከፈነዳ በኋላ ፖሊስ ምርመራ መጀመሩ ተገለጸ።

ፖሊስ ስም ሳይጠቅስ አሽከርካሪው ሲሞት ሰባት ሰዎች ቆስለዋል ብሏል። ሁሉም ጉዳቶች ቀላል መሆናቸውን የመንግሥት ባለስልጣናት ተናግረዋል።

መኪናው ከኮሎራዶ የተከራየ ሲሆን ረቡዕ ረፋዱ ላይ ወደ ከተማዋ ገብቷል። በከተማዋ ሁለት ሰዓት እንኳን ሳይቆይ ፍንዳታው መድረሱን ፖሊስ ተናግሯል። ከሆቴሉ የመስታወት መግቢያ ፊት ለፊት ከቆመ በኋላ ተሽከርካሪው መጨስ ጀምሮ በኋላም ፈንድቷል።

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ምሽት ላይ ባደረጉት ንግግር ዋይት ሃውስ ጉዳዩን እየተከታተለ መሆኑን ገልጸው የህግ አስከባሪ አካላት "በኒው ኦርሊየንስ ከተፈጸመው ጥቃት ጋር ግንኙነት ስለመኖሩ" እየመረመሩ ነው ሲሉ አስረድተዋል። በኒው ኦርሊየንስ በአዲስ ዓመት ቀን በተፈጸመ የመኪና ጥቃት በትንሹ 15 ሰዎች ተገድለዋል።

የፖሊስ መኮንኑ ኬቨን ማክማሂል በጋዜጣዊ መግለጫቸው ፍንዳታውን የሚያሳይ ቪዲዮ እና በኋላ ላይ የደረሰውን ጉዳት በፎቶግራፎች አሳይተዋል። መኪናው ላይ በርካታ የነዳጅ መያዣዎች እና ርችት ተጭነው ነበር።

ሳይበርትራኩ ከሆቴሉ መግቢያ ፊት ለፊት ቆሞ እንደነበር የሚያሳይ ምስልም ታይቷል። መኪናው ከመፈንዳቱ በፊት ለጥቂት ሰኮንዶች ያለሥራ ቆሟል። በፈነዳበት ወቅት ባለብዙ ቀለም የርችት ፍንጣቂዎችም በተለያዩ አቅጣጫዎች ተተኩሰዋል።

በሌላ ቪዲዮ ደግሞ መርማሪዎች እሳቱን ለማጥፋት ሲጥሩ ይታያሉ። የነዳጅ መያዣዎችና ከደርዘን የሚበልጡ የርችት ቅሪቶችም ተገኝተዋል።

ፍንዳታው አንድ ግለሰብ የእስላሚክ ስቴት (አይኤስ) ባንዲራ በያዘ መኪና በኒው ኦርሊየንስ በርካታ ሰዎችን ከገጨ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ የተከሰተ ነው። በጥቃቱ ቢያንስ 15 ሰዎች ሲሞቱ በደርዘን የሚቆጠሩት ደግሞ ቆስለዋል።

የላስ ቬጋስ ፖሊስ ባልደረባ የሆኑት ማክማሂል እንደተናገሩት ክስተቱ ከኒው ኦርሊየንሱ ጋር የተገናኘ ስለመሆኑ እየመረመሩ ነው።

የሆቴሉ ባለቤት ከሆኑት ከተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወይም የቴስላ ባለቤት ከሆነው ኢላን መስክ ጋር የተያያዘ ሊሆን ስለመቻሉም እየመረመሩ መሆናቸውንም አክለው ተናግረዋል።

"የሳይበርትራክ፣ የትራምፕ ሆቴል እና ሌሎች ወደፊት የምንመልሳቸው ብዙ ጥያቄዎች አሉ።"

ኤፍቢአይ ድርጊቱ የሽብር ተግባር ሊሆን ይችላል ወይ የሚለውን እየመረመረ ቢሆንም በተሽከርካሪው ውስጥ የሞተውን የአሽከርካሪ ማንነት ባለስልጣናት እስካሁን አላረጋገጡም ተብሏል። ባለስልጣናት አክለውም ክስተቱ ከአይኤስ ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ ምንም አይነት ማስረጃ እስካሁን እንዳላገኙ ገልፀዋል።

"ሁሉም ሰው 'ይህ የሽብር ጥቃት ነው' ስለማለታችን እየተጠበቀ ነው። እኛም ለማድረግ እየሞከርን ያለነውም ይህንኑ ነው" ሲሉ የኤፍቢአይ ልዩ ተወካይ ዤረሚ ሽዋርት በጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ተናግረዋል።

በኒው ኦርሊየንስም ሆነ በላስ ቬጋስ የደረሱት ጥቃቶችን የተፈፀሙባቸው መኪናዎች ከተመሳሳይ መተግበሪያ የተከራዩ ሳይሆኑ አልቀሩም እየተባለ ነው።

ቱሮ የተባለው መተግበሪያ ቃል አቀባይ በሰጡት መግለጫ ኩባንያው በላስ ቬጋስ እና በኒው ኦርሊየንስ ከሚገኙ ባለስልጣናት ጋር በምርመራው ላይ እገዛ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል። ቃል አቀባዩ አክለውም ሁለቱም መኪና ተከራዮች "እንደደህንነት ስጋት" የሚያስቆጥራቸው የወንጀል ታሪክ የሌላቸው እንደሚመስሉ ተናግረዋል።

"በኒው ኦርሊየንስ እና በላስቬጋስ በተፈጸመው ጥቃት ልባችን ተሰብሯል። ጸሎታችን ለተጎጂዎች እና ለቤተሰቦችቻቸው ይድረስ" ብለዋል በመግለጫቸው።

ባለሥልጣናት ተሽከርካሪውን የተከራየውን ሰው ስም እንደሚያውቁ ቢናገሩም መኪናውን ያሽከረከረው እራሱ ስለመሆኑን በይፋ አላረጋገጡም።

"በታዋቂው የላስ ቬጋስ ቡሌቫርድ ላይ በደረሰው ፍንዳታ ምክንያት የህብረተሰባችንን ደህንነት ለመጠበቅ ማድረግ ያለብንን ጥንቃቄዎች ሁሉ እያከናወንን ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

አሁን ለላስ ቬጋስ ማህበረሰብ ስጋት የሚሆን ነገር የለም ሲሉ ማክማሂል ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንት ባይደን በኒው ኦርሊየንስ ስለደረሰው ጥቃት እና ስለ ላስ ቬጋስ ፍንዳታ ገለጻ ተሰጥቷቸዋል።

ፕሬዚዳንቱ በምሽቱ ንግግራቸው "በላስ ቬጋስ ከትራምፕ ሆቴል ፊት ለፊት ስለደረሰው የሳይበርትራክ ፍንዳታ እየተከታተልን ነው" ብለዋል።

"ህግ አስከባሪ አካላት እና የስለላ ተቋማት በኒው ኦርሊየንስ ከተፈጸመው ጥቃት ጋር ግንኙነት መኖሩን ጨምሮ ምርመራ እያደረጉ ነው።"

የእሳት አደጋ መከላከያ ኃላፊዎች የድንገተኛ ጊዜ ሠራተኞች የተሽከርካሪውን ቃጠሎ ለማጥፋት በፍጥነትመንቀሳቀሳቸውን ገልጸዋል።

ህዝቡ ከአካባቢው መራቅ እንዳለበትም አክለዋል። አብዛኞቹ የሆቴሉ እንግዶች ወደ ሌላ ቦታ ተዘዋውረዋል።

ሆቴሉ በከፊል በተመራጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኩባንያ ባለቤትነት የተያዘ ነው። የትራምፕ ልጅ ኤሪክ ትራምፕ በኤክስ ላይ በለጠፈው ጽሁፍ "በትራምፕ የላስቬጋስ ሆቴል ፊት ለፊት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቃጠሎ ተከስቷል" ብሏል።

"የእንግዶቻችን እና የሠራተኞቻችን ደህንነት ቀዳሚ ትኩረታችን ነው። የላስ ቬጋስ የእሳት አደጋ መከላከያ እና የአካባቢው ህግ አስከባሪ አካላት ለሰጡት ፈጣን እና ሙያዊ ምላሽ ምስጋናችን ይድረሳቸው" ብሏል።

ስቴፈን ፌርላንዶ ክስተቱን በትራምፕ ታወር 53ኛ ፎቅ በሚገኘው የሆቴል ክፍሉ ሆኖ መመልከቱን ለዋሽንግተን ፖስት ተናግሯል። "በእርግጠኝነት ፍንዳታ" እንደነበር እና መስኮቶቹ መንቀጥቀጥ መጀመራቸውን ገልጿል።

ትራምፕ ሆቴል 64 ፎቆች ያሉት ሲሆን ወደ 1 ሺህ 300 የሚጠጉ ክፍሎች እንዳሉት በድረ ገጹ ላይ ተገልጿል።

በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ትራምፕ እና መስክ የፈጠሩትን ቅርበት ተከትሎ ተመራጩ ፕሬዝዳንት የመንግስትን ብቃት የሚገመግምን መስሪያ ቤት በኃላፊነት እንዲመራ ቢሊየነሩን ሾመውታል።