ፑቲን በጎረቤት አገር ቤላሩስ የኒውክሌር የጦር መሳሪያዎች አገራቸው ማስቀመጧን አረጋገጡ

ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በጎረቤት አገር ቤላሩስ የመጀመሪያውን ታክቲካል የኒውክሌር የጦር መሳሪያዎች አገራቸው ማስቀመጧን ተናገሩ።

ፕሬዚዳንቱ በዓለም አቀፉ የኢኮኖሚ ጉባኤ ላይ እንደተናገሩት የኒውክሌር መሳሪያዎቹ ጥቅም ላይ የሚውሉት የሩሲያ ግዛት ላይ አደጋ በሚያስከትሉ ሁኔታዎች ላይ ነው ብለዋል።

አክለውም የሩሲያ መንግሥት ወይም የአገሪቷ ሉዓላዊነት ጉዳት ላይ ከወደቀ መሳሪያዎቹ ጥቅም ላይ እንደሚውሉም ፍንጭ ሰጥተዋል።

የአሜሪካ መንግሥት በበኩሉ ሩሲያ ዩክሬንን ለማጥቃት የኒውክሌር የጦር መሳሪያን ለመጠቀም ማቀዷን የሚጠቁም ነገር እንደሌለ አስታውቋል።

“ሩሲያ የኒውክሌር የጦር መሳሪያ ለመጠቀም እየተዘጋጀች ስለመሆኗ የሚጠቁም ምንም ዓይነት ምልክት አላየንም” ሲሉ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከፑቲን አስተያየት በኋላ ተናግረዋል።

ቤላሩስ ቁልፍ የሩሲያ አጋር ናት።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራን በፈጸመችበት በመጀመሪያው ወቅትም ለጦርነቱ መነሻ ስፍራም በመሆን አገልግላለች።

ፕሬዚዳንት ፑቲን ወደ ቤላሩስ የሚደረገው የኒውክሌር የጦር መሳሪያዎች ማዘዋወርም በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል።

በሴንት ፒተርስበርግ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ጉባኤ ላይ ንግግር ካደረጉ በኋላም ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ፑቲን ምላሽ ሰጥተዋል።

ፕሬዚዳንቱ አገራቸው የኒውክሌር የጦር መሳሪያዎችን ያዘዋወረችው ሁኔታዎችን በጥንቃቄ ለመከታተል ያመቻት ዘንድ ሲሆን “በእኛ ላይ ስልታዊ ሽንፈቶችን ለማምጣት የሚያቅዱትን ለማስታወስ ነው” ብለዋል።

የጉባዔው አወያይ እነዚህን የኒውክሌር የጦር መሳሪያዎች ጥቅም ላይ የሚውሉበት እድል ይኖር ይሆን ወይ? ብለው ፕሬዚዳንቱንም ጠይቀዋቸዋል።

“ለምን መላውን ዓለም እናስፈራራለን? ቀደም ብዬ ተናግሬያለሁ በሩሲያ ግዛት ላይ አደጋ ቢፈጠር እንዲህ ዓይነት ጽንፈኛ እርምጃዎችን ለመውሰድ እንደገደዳለን” ሲሉም ምላሽ ሰጥተዋል።

ዩክሬንና ሩሲያ ጦርነቱን በሰላም ለመቋጨት በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲመጡ የማሸማገል ስራ እየሰሩ ያሉት የአፍሪካ መሪዎች ልዑካን ቡድን ዛሬ በሴንት ፒተርስበርግ ከፑቲን ጋር ይገናኛሉ።

ትናንት ሰኔ 9/ 2010 ዓ.ም ወደ ኪዬቭ አቅንተው የነበረ ሲሆን የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪን ጨምሮ ከፍተኛ የዩክሬን ባለስልጣናት ጋር መክረዋል።