ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እስራኤል ውስጥ በኤርትራውያን መካከል በተፈጠረ አምባጓሮ አንድ ሰው ሲገደል በርካቶች ቆሰሉ
እስራኤል ውስጥ በኤርትራ መንግሥት ደጋፊዎች እና በተቃዋሚዎች መካከል በተፈጠረ አምባጓሮ አንድ ሰው በስለት ሲገደል በርካቶች ቆሰሉ።
ቅዳሜ መስከረም 19/2016 ዓ.ም. በኔታንያ በተለ ስፍራ በተፈጠረው ሁከት አንድ ኤርትራዊ በስለት ተወግቶ መገደሉን የአገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን ፖሊስን ዋቢ አድርገው ዘግበዋል።
የተገደለው ኤርትራዊ የአገሩን መንግሥት የሚቃወም በመሆኑ በአገዛዙ ደጋፊዎች በስለት ሳይወጋ እንዳልቀረ ፖሊስ መጠርጠሩን ታይምስ ኦፍ እስራኤል ዘግቧል።
የኤርትራን መንግሥት በሚደግፉ እና በሚቃወሙ ስደተኞች መካከል ግጭቱ የተነሳው አርብ ምሽት በደቡባዊቷ የቴልአቪቭ ከተማ ክፍል ሃቲክቫቭ በተሰኘች ሰፈር ነው።
ይህም ግጭት ቅዳሜ ማለዳ በኔታንያ የቀጠለ ሲሆን፣ ከሞተው በተጨማሪ በሰላሳዎቹ ዕድሜ የሚገኝ አንድ ኤርትራዊ በከፋ ሁኔታ ተጎድቷል ተብሏል።
በኔታንያ ሄርዝል ጎዳና ላይ በጎራ የተከፋፈሉ ኤርትራውያን ወንበሮች ሲወረውሩ እና ፖሊሶች ሁከተኞቹን ለመበተን ወደ አየር ላይ ጥይት ሲተኩስ የሚያሳዩ ቪዲዮዎች ወጥተዋል።
ፖሊስ ዱላ እና ድንጋይ ይዘው በሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ ጥቃት ለማድረስ አቅደዋል ያላቸውን ከአስር በላይ ሰዎችንም በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል።
አርብ ምሽት በተፈጠረው ሁከት ሁለት ሰዎች በጠና ተጎድተው ሆስፒታል መግባታቸው የተሰማ ሲሆን፣ በዚያው ሳምንት መጀመሪያ ላይ አንድ ኤርትራዊ ስደተኛ በተመሳሳይ ሁኔታ በስለት ተወግቶ ተገድሏል።
ባለፈው ወር በእስራኤል መዲና ቴልአቪቭ በሚገኘው የኤርትራ ኤምባሲ ደጃፍ ላይ በኤርትራ መንግሥት ደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች መካከል በተፈጠረው ከፍተኛ ግጭት ወደ 200 የሚሆኑ ሰዎች ቆስለዋል።
በርካቶች ተጎድተውበታል እንዲሁም ከፍተኛ የንብረት መውደም ተከስቶበታል በተባለው በዚህ ግርግር ተሳትፈዋል የተባሉ ኤርትራውያን ጥገኝነት ጠያቂዎችን በአስቸኳይ ከአገር ማባረርን ጨምሮ ጠንከር ያለ እርምጃም እንደሚወሰድባቸው የእስራኤል መንግሥት አስታውቆ ነበር።
ኤርትራን በፈላጭ ቆራጭነት እየገዙ ባሉት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አገዛዝ ላይ ከዚህ ቀደም በዳያስፖራው ተቃውሞች ቢሰሙም ካለፈው ዓመት ጀምሮ ግን መልኩን እየቀየረ በመንግሥት ደጋፊዎች እና በተቃዋሚዎች መካከል በሚፈጠሩ ግጭቶች ደም መፋሰሶች እየታዩ ነው።
በእስራኤል ውስጥ ወደ 25 ሺህ የሚጠጉ ኤርትራውያን ጥገኝነት ጠያቂዎች እንዳሉ ይገመታል።
በርካቶቹም ከዓመታት በፊት የግብፅን የሲናይ ባሕረ ገብ መሬት አቋርጠው በሕገወጥ መንገድ የገቡ ናቸው። ስደተኞቹ በዓለማችን በጭቆና ከምትታወቀው ኤርትራ አስገዳጅ የሆነውን የብሔራዊ ውትድርና አገለግሎት እና ጭቆናን አምልጠው እንደተሰደዱ ይናገራሉ።
ኤርትራ ከኢትዮጵያ ነጻ የወጣችበትን 30 ዓመት ባከበረችበት ወቅት በተለያዩ አገራት የሚገኙ ዲያስፖራዎች ዕለቱን አክብረዋል።
ነገር ግን በእስራኤል እንደተከሰተው በአውሮፓ እና በሰሜን አሜሪካም በአንዳንድ ስፍራዎች ሁከቶች ተከስተዋል።
በካናዳዋ ቶሮንቶ ለሦስት ቀናት ይቆያል ተብሎ የነበረው የኤርትራውያን የባህል ፌስቲቫል ደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች መጋጨታቸውን ተከትሎ ተሰርዟል።