ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዩክሬን በፕሬዝዳንት ፑቲን መኖሪያ ላይ የድሮን ጥቃት ፈጽማለች መባሉን አስተባበለች
ፕሬዝዳንት ቭሎድሚር ዜሌንስኪ፤ ዩክሬን በፕሬዘዳንት ፑቲን መኖሪያ ቤት ላይ የድሮን ጥቃት ከፍታለች በሚል ከሩሲያ የቀረበውን ክስ አስተባበሉ። ሞስኮ ይህንን እንደ ምክንያት በመጠቀም የሰላም ንግግሩን ለማጓተት እየሞከረች ነው ሲሉም በምላሹ ከስሰዋል።
ዩክሬን በሰሜን ምስራቃዊ ሩሲያ፤ ኖቭጎሮድ ግዛት በሚገኘው የፑቲን ፕሬዝዳንታዊ መኖሪያ ላይ ጥቃት ከፍታለች የሚለውን ክስ ያሰሙት አገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ናቸው። እንደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ኪዬቭ ምሽት ላይ ረጅም ርቀት የሚጓዙ 91 ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በመጠቀም በፑቲን መኖሪያ ላይ ጥቃት ሰንዝራለች።
ተሰነዘረ የተባለው ጥቃት በተፈጸመበት ወቅት ፕሬዝዳንቱ ፑቲን የት እንደነበሩ በግልጽ አልታወቀም። በጥቃቱ ምክንያት ሩሲያ የሰላም ድርድሩ ላይ ያላትን አቋም መልሳ እንደምትፈትሽ አስታውቃለች።
ይህንን ክስ "የተለመደ የሩሲያ ውሸት" በማለት ያጣጣሉት ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ በበኩላቸው፤ ሞስኮ ጥቃት ተፈጽሟል እያለች ያለችው በዩክሬን ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት የምታስቀጥልበት ምክንያት በመፈለግ ነው ብለዋል።
ሩሲያ ከዚህ ቀደም በኪዬቭ የሚገኙ የመንግሥት መስሪያ ቤቶችን ዒላማ ያደረገ ጥቃት መፈጸሟን ተናግረዋል። ዜሌንስኪኦ አክለውም፤ "በዚህ ሰዓት ዓለም ዝምታን አለመምረጡ እጅግ ወሳኝ ነው። ሩሲያ ዘላቂ ሰላምን ለማሳካት የሚደረገውን ጥረት እንድታደናቅፍ መፍቀድ አንችልም" ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል።
የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰኞ ዕለት ቴሌግራም ላይ ባወጡት መግለጫ፤ ወደ ፑቲን መኖሪያ ተወንጭፈዋል የተባሉት ሁሉም 91 ድሮኖች በሩሲያ የአየር መከላከያ ስርዓት መጠለፋቸውን እና መውደማቸውን ገልጸዋል።
በጥቃቱ ምክንያት ሪፖርት የተደረገ ጉዳትም ሆነ ውድመት አለመኖሩንም አክለዋል። "ወንጀለኛው የኪየቭ አገዛዝ ወደ መንግስታዊ ሽብርተኝነት ፖሊሲ በመሸጋገሩ እና በመጨረሻ ደረጃ በመበላሸቱ ምክንያት የሩሲያ የድርድር አቋም እንደገና ይከለሳል" ብለዋል።
ይሁን እንጂ ሩሲያ ከአሜሪካ ጋር ከተጀመረው የድርድር ሂደት የመውጣት እቅድ እንደሌላት መናገራቸውን የሩሲያ የዜና ወኪል የሆነው 'ታስ' ዘግቧል።
ሞስኪ ይህንን ክስ ያቀረበችው አሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ዜሌንስኩ እሁድ ዕለት በፍሎሪዳ ተገናኝተው ማሻሻያ በተደረገበት የጦርነት መቋጫ እቅድ ላይ ከተነጋገሩ በኋላ ነው።
ከውይይቱ በኋላ ከፎክስ ኒውስ ጋር ቆይታ ያደረጉት ዜሌንስኪ፤ በ2026 "ይህንን ጦርነት የመቋጨት እድል አለ" ብለዋል።
"የፕሬዝዳንት ትራምፕ ማዕቀቦች እና የኢኮኖሚ እርምጃዎች፤ እጅግ ጠንካራ ለሆኑ እርምጃዎች ዝግጁ እንደሆኑ ያሳያል" ሲሉም ተናግረዋል። "በዚህ ሁኔታ ውስጥ አሜሪካ ሁኔታውን በፍጥነት ወደ ሰላም ልታደርሰው ትችላለች" ሲሉም ተደምጠዋል።
አሜሪካ ለ15 ዓመታት የሚቆይ የደህንነት ዋስታን ለዩክሬን ማቅረቧን ዜሌንስኪ ገልጸዋል። ትራምፕ በበኩላቸው በዚህ ጉዳይ ላይ "95 በመቶ ገደማ" ስምምነት ላይ መደረሱን ጠቅሰዋል።
ዜሌንስኪ፤ የግዛት ጉዳዮች እና በሩሲያ ቁጥጥር ስር ያለውን የዛፖሪዝዝያ የኒውክሌር ጣቢያ ነገር መቋጫ ያላገኙ ጉዳዮች እንደሆኑ ገልጸዋል።
ሩሲያ ሙሉ በሙሉ ልትቆጣጠረው በምትፈልገው አወዛጋቢው የዶንባስ ግዛት መጻኢ እድል ላይ የታየው መሻሻልም በጣም አነስተኛ እንደሆነ አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት ሞስኮ የዶኔትስክን ክልል 75 በመቶ ገደማ እንዲሁም አጎራባች ከሆነውን የሉሃንስክን ግዛት 99 በመቶ ያህልን ተቆጣጥራለች። እነዚህ ሁለት ክልሎች በጥቅሉ ዶንባስ በመባል ይታወቃሉ።