ኤርትራ ሠራዊቷን እያጠናከረች፣ ኢትዮጵያ እንዳትረጋጋ እያደረገች ነው - ሪፖርት

ኤርትራ ተጥሎባት የነበረው የጦር መሳሪያ ማዕቀብ መነሳቱን ተከትሎ ሠራዊቷን መልሳ በማጠናከር በአካባቢው በተለይም በኢትዮጵያ መረጋጋት እንዳይኖር እያደረገች ነው ሲል አንድ የአሜሪካ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ሪፖርት አመለከተ።

ኤርትራ ግን የቀረበባት ክስ የፈጠራ እና ማሳበቢያ ነው በማለት በአካባቢው ለተፈጠረው ውጥረት ተጠያቂያዋ ኢትዮጵያ ናት ስትል ከስሳለች።

'ዘ ሴንትሪ' የተባለው የአሜሪካ የመብቶች ተከታታይ መንግሥታዊ ያልሆነው ድርጅት ሰኞ ዕለት ባወጣው ሪፖርት ኤርትራ ተጥሎባት የነበረው የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ከሰባት ዓመት በፊት ከተነሳ በኋላ ሠራዊቷን መልሳ በመገንባት እና በማጠናከር "በጎረቤቶቿ በተለይም በኢትዮጵያ ውስጥ አለመረጋጋት እየፈጠረች ነው" ብሏል።

ከደም አፋሳሽ የድንበር ጦርነት በኋላ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በፍጥጫ ውስጥ የቆዩት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በ2010 ዓ.ም. የሰላም ስምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ በተባባሩት መንግሥታት ተጥሎባት የነበረው የጦር መሳሪያ ማዕቀብ እንደተነሳላት ይታወሳል።

"የተጣለባት ማዕቀብ በተነሳበት በአሁኑ ወቅት ኤርትራ ጦር ሠራዊቷን መልሳ እያገነባች፣ የመከላከያ ኃይሏን እያጠናከረች እና ጎረቤቶቿ እንዳይረጋጉ ማድረጓን ቀጥላለች" ሲል የአሜሪካው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት 'ዘ ሴንትሪ' ያወጣው ሪፖርት ላይ አመልክቷል።

ሪፖርቱ አክሎም "ያለው ሁኔታ ሳይቀየር ባለበት የሚቀጥል ከሆነ [ኤርትራም] እያደረገች ባለው ትቀጥላለች ተብሎ ይጠበቃል" ሲል አስጠንቅቋል።

'ዘ ሴንትሪ' ባወጣው ሪፖርት በኤርትራ ላይ የቀረበውን ክስ በተመለከተ በፈረንሳይ ዜና ወኪል፣ ኤኤፍፒ የተጠየቁት የማስታወቂያ ሚኒስትሩ የማነ ገብረመስቀል "የፈጠራ ትርክት" በማለት ሪፖርቱ የሌሎችን ድርጊት በኤርትራ ላይ "የሚያላክክ" ነው በማለት አጣጥለውታል።

ሚኒስትሩ አክለውም "በቀጣናው ለተፈጠረው አዲስ ውጥረት ምክንያቱ ኢትዮጵያ ከሕግ ውጪ በይፋ ወደብ እና የባሕር ጠረፍ የማግኘት ፍላጎት እንዳላት ማሳወቋ" መሆኑን በመጥቀስ ኢትዮጵያን ተጠያቂ አድርገዋል።

ባለፈው በዚህ ዓመት አጋማሽ ላይ የኤርትራ መንግሥት የቀድሞ የሠራዊት አባላት ወደ የክፍሎቻቸው ለዳግም ሥልጠና እንዲመለሱ እና ሌሎች ዜጎቹ ከአገር ለመውጣት የሚጠበቅባቸውን መስፈርቶች ማጥበቁን ቢቢሲ መዘገቡ ይታወሳል።

በዚህም ከ60 ዓመት በታች የሆኑ በኤርትራ ሠራዊት ውስጥ ያገለገሉ ዜጎች ተመዝግብው ወደ ማሠልጠኛ እንዲገቡ፤ እንዲሁም ከ50 ዓመት በታች የሆኑ ሰዎች ደግሞ ተገቢውን ፈቃድ ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ሳያገኙ ከአገር እንዳይወጡ ዕገዳ መጣሉን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በትግራይ ጦርነት አንድ ላይ ቆመው የትግራይ ኃይሎችን የወጉት የኤርትራ እና የኢትዮጵያ መንግሥታት ወዳጅነታቸው መቀዛቀዝ የጀመረው ጦርነቱን ያበቃው የፕሪቶሪያ ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ነው።

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ የኅልውና ጉዳይ መሆኑን በይፋ ካሳወቁ በኋላ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ወደ ውዝግብ እና መካሰስ ተሸጋግሯል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ኤርትራ በውስጥ ጉዳያቸው ጣልቃ እየገባች ታጣቂዎችን እየደገፈች ነው የሚል ተደጋጋሚ ክስ ሲያቀርቡ የቆዩ ሲሆን፣ በቅርቡም የኤርትራ ኃይሎች ከያዟቸው የኢትዮጵያ ግዛቶች እንዲወጡ ተጠይቋል።

ከሁለቱም አገራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና መገናኛ ብዙኃን በተደጋጋሚ የሚሰማው ንግግር ዳግም ጦርነት ሊፈነዳ ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።

ኤርትራ ወታደራዊ ዝግጅት እያደረገች መሆኑን ያመለከተውን ሪፖርት ያወጣው 'ዘ ሴንትሪ' የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ዋነኛ ትኩረት የሚያደርገው ጦርነቶችን የሚደግፉ ስውር የገንዘብ ዝውውሮችን መከታተል ላይ ሲሆን፣ በአውሮፓውያኑ 2009 በኤርትራ ላይ የጦር መሳሪያ ማዕቀብ የተጣለባት ለሶማሊያ ጂሃዲስት ቡድኖች ድጋፍ ትደርጋለች በሚል ክስ መሆኑን ጠቅሷል።

ድርጅቱ በዚህ ሪፖርቱ ላይ ከሁለት ዓመት በፊት ባበቃው በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ በተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት ወቅት የተፈጸሙ ሰቆቃዎችንም ጠቅሷል።

በትግራይ ኃይሎች እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል በተካሄደው ጦርነት ወቅት የኤርትራ ሠራዊት የኢትዮጵያ መንግሥትን ደግፎ ተሳታፊ የነበረ ሲሆን፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን የአፍሪካ ኅብረት መረጃ ማመልከቱን ኤኤፍፒ ጠቅሷል።

የ'ዘ ሴንትሪ' ሪፖርት በጦርነቱ የተሳተፉ ሁሉም አካላት የጦር ወንጀሎችን መፈጸማቸውን በመጥቀስ፣ በተለይ በኤርትራ ሠራዊት የተፈጸሙት ግን "የታቀዱ እና የሚነጻጸሩ ይደሉም" ሲል ከስሷል።