ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኤርትራ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት "ለጦርነት አጀንዳው ድጋፍ ለማሰባሰብ ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ አጠናክሮብኛል" አለች
ኤርትራ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት "ለጦርነት አጀንዳው ድጋፍ ለማሰባሰብ"፤ የከፈተውን "ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ አጠናክሮብኛል" ስትል ከሰሰች። የኢትዮጵያ መንግሥት "ባለፉት ቀናት" ኤርትራን የሚከስሱ ደብዳቤዎችን ወደ "የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ" እና "የሀገራት መሪዎች ልኳል" በማለትም ወቅሷል።
የኤርትራ መንግሥት ይህንን ክስ በኢትዮጵያ ላይ ያቀረበው ትናንት ሐሙስ ሰኔ 19/2017 ዓ.ም. በማስታወቂያ ሚኒስቴር በኩል ባወጣው መግለጫ ነው። የሀገሪቱ መንግሥት መግለጫ፤ ኢትዮጵያ "ግጭትን በምክንያት ለማላበስ እና ለመቀስቀስ የሐሰት ባንዲራ እያውለበለበች ነው" የሚል ክስን ያቀረበ ነው።
መግለጫው፤ "ባለፉት ጥቂት ቀናት" ውስጥ የኢትዮጵያ መንግሥት "በኤርትራ ላይ የከፈተውን ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ አጠናክሯል" ሲል ከስሷል። የዲፕሎማሲያዊ ዘመቻው "ወደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ እንዲሁም ለበርካታ ለሀገር እና መንግሥት መሪዎች" ደብዳቤዎችን መላክንም ያካተተ እንደሆነ በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።
የተጻፈው ደብዳቤ፤ "ኤርትራን 'በተደጋጋሚ ትንኮሳዎች እንዲሁም በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ጥሰቶች' የሚወነጅል" እንደሆነ የሀገሪቱ መንግሥት መግለጫ አስፍሯል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ይህ ዓይነት ይዘት ያለው ደብዳቤ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስለመጻፉ በይፋ አልገለጸም።
ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸውን አስተያየት ለማግኘት ያደረጋቸው የስልክ ጥሪዎች እና የላከው የጽሁፍ መልዕክት ወዲያውኑ ምላሽ አላገኘም።
ይሁን እንጂ "ሉዓላዊ" የተባለ ለመንግሥት ቅርበት ያለው የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌድዮን ጢሞትዮስ የኤርትራ መንግሥትን በተመለከተ "ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ደብዳቤ ማሠራጨቱን" ዘግቦ ነበር።
ከዘገባው ጋር የተያያዘ ምስል፤ ደብዳቤው ባለፈው ሳምንት አርብ ሰኔ 13/2017 ዓ.ም. እንደተጻፈ የሚያመለክት ሲሆን፣ በኤርትራ መግለጫ የተጠቀሰውን "ተደጋጋሚ ትኮሳዎችን" የመፈጸም እና "የሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ጥሰቶችን" የሚመለከት ዓረፍተ ነገር ያካተተ ነው።
በ2010 ዓ.ም. የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ስምምነት መፈረምን ተከትሎ የመጡ በጎ ለውጦችን የሚያስታውሰው ደብዳቤው፤ በዚህ ወቅት ከአሥመራ በኩል የታየው "የመጀመሪያ ምላሽ አበረታታች" እንደነበር ይገልጻል። ነገር ግን "የሰሜን ኢትዯጵያን ጦርነት ኢትዮጵያን ለማዳከም እንደ ዕድል ተመልክቶት የነበረው" የኤርትራ መንግሥት፤ የፕሪቶሪያው ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ "ከጊዜ ወደ ጊዜ ጠበኛ አቋም መያዝ ጀመረ" ሲል ይከስሳል።
የውጭ ጉዳይ በተጨማሪም፤ የኤርትራ መንግሥት "ከህወሓት አንጃ ጋር ትብብር እና ቅንጅት በመፍጠር እንዲሁም ከሌሎች ታጣቂ ኃይሎች ጋር በመተባበር በመጪው የክረምት ወቅት ከፍተኛ ወታደራዊ ጥቃት ለመፈጸም ተዘጋጅተዋል" በማለት እንደወነጀለ በዘገባው ላይ ተካትቷል።
እንደ ዘገባው ከሆነ መንግሥት የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፤ "በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እንዲረጋገጥ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እንዲያከብር በኤርትራ መንግሥት ላይ ግፊት እንዲያደርግ" ጥሪ አቅርቧል።
የኤርትራ መንግሥት በበኩሉ ትናንት ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግሥት የጻፈውን ደብዳቤ "የተለመደ ማደናገሪያ" ሲል ጠርቶታል። "[የዲፕሎማሲ ዘመቻው] ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ማታለል እና በዚህም ረጅም ጊዜ ሲብላላ ለቆየው የጦርነት አጀንዳው ድጋፍ ማሰባሰብን" ዓላማ ያደረገ ነው በማለት ከስሷል።
መግለጫው፤ "እውነታው ግን የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ ብልፅግና፤ የኤርትራ ወደቦችን 'በተቻለ መጠን በሕጋዊ መንገድ፣ አስፈላጊ ከሆነም በወታደራዊ መንገድ' ለመውሰድ በሚል ላለፉት ሁለት ዓመታት በግዴለሽት አላስፈላጊ መግለጫዎች እና ተንኳሽ ጦር ሰበቃ ውስጥ እየገባ ነው" ብሏል። የኢትዮጵያ መንግሥት "የጦር መሣሪያዎች ግዢ" ላይ ተሰማርቷል ሲልም አክሏል።
ይህ የኤርትራ መንግሥት መግለጫ የወጣው በአዲስ አበባ እና አሥመራ ባለሥልጣናት አንዳቸው ሌላኛቸውን ዒላማ የያደረጉ ንግግሮችን እያሰሙ ባሉበት በዚህ ወቅት ነው።
የኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ባለፈው ግንቦት በተከበረው የሀገሪቱ 34ተኛ የነጻነት በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያ መንግሥት እና በገዢው ብልፅግና ፓርቲን ላይ በግልጽ ውንጀላዎችን አቅርበው ነበር።
ኢሳያስ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት "የውሃ ጉዳይ፣ አባይ እና ቀይ ባሕር፣ የባሕር በር ማግኘት፣ የኦሮሞ ሕዝብን የማይወክል የኦሮሙማ አስተሳሰብ፣ የኩሽ እና የሴም ግጭት፣ የአፋር ሕዝብ እና መሬትን ለዚህ አጀንዳ መጠቀም" የጦርነት ቅስቀሳ እያደረገ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
ፕሬዝዳንቱ በዚህ ንግግራቸው በተለይም "የኦሮሙማ አስተሳሰብ" በሚል ያነሱት ውንጀላ በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ የኦሮሞ ምሁራንን ጨምሮ ከተለያዩ አካላት ጠንካራ ምላሽ አስከትሎ ነበር።
በዚያው ሰሞን ከመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ጋር ቃለ መጠይቅ ያደረጉት የመከላከያ ሚኒስትሯ አይሻ መሐመድ፤ "በዚህ ልክ ስለ ኢትዮጵያ ለመናገር [ሙከራ] ማድረጋቸው የተለመደ የእነርሱ ባህሪ እንደሆነ እናውቃለን" ብለዋል።
በግንቦት መጨረሻ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው የነበሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌድዮን፤ ኢትዮጵያ መንግሥት ከኤርትራ መንግሥት ጋር "የቃላት ጦርነት ውስጥ አልገባም" ሲሉ ተደምጠዋል።
"ትንኮሳ ቢኖርም አንዳንዴ ሆደ ሰፊነት፣ አንዳንዴ ሰምቶ እንዳልሰማ፣ አንዳንዱን ደግሞ በራሱ በዲፕሎማቲክ ቻናል ለመመለስ ጥረት እናደርጋለን እንጂ የቃላት ጦርነት ውስጥ አልገባንም፤ የምንገባም አይመስለኝም" በማለት ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መንግሥት መካከል ያለው ውጥረት እየተባባሰ ቢመጣም፤ ከ2010ሩ ስምምነት በኋላ ተከፍተው በድጋሚ የተዘጉ በትግራይ ክልል በኩል ያሉት የዛላምበሳ እና የራማ ድንበር መስመሮች ባለፉት ሳምንታት ተከፍተዋል።
ድንበሮቹ የተከፈቱት "ከሁለቱም መንግሥታት ይፋዊ ድጋፍ ሳይደረግ በአካባቢው የማኅበራዊ አንቂዎች እና የማኅበረሰብ ተወካዮች አነሳሽነት" ነው የተባለ ሲሆን፣ "የትግራይ ክልል መንግሥት እና የኤርትራ ባለሥልጣናትንም" ይሁንታ እንደሰጡ ተገልጿል።
የእነዚህን የድንበር መስመሮች መከፈት በተመለከተ እስካሁን ድረስ ከፌደራል መንግሥት በኩል የተሰጠ ይፋዊ አስተያየት የለም።