ሦስት አስር ዓመት፣ አንድ መሪ - የመከነው የኤርትራውያን ተስፋ

በአንድ ወቅት ከአዲስ የለውጥ አራማጅ የአፍሪካ መሪዎች መካከል ተቆጥረው የተወደሱት ኢሳያስ አፈወርቂ፣ ሥልጣን ከተቆናጠጡ 32 ዓመት ቢያስቆጥሩም የኤርትራውያንን ተስፋ እና ሕልም ሊያሳኩ አልቻሉም።

ኢሳያስ አፈወርቂ አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ከዋና ከተማዋ አሥመራ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ አቧራማ እና ኮረብታ በሆነ ስፍራ ላይ በሚገኘው የገጠር መኖሪያ ቤታቸው ነው።

ካቢኔያቸው ከአውሮፓውያኑ 2018 ጀምሮ ያልተሰበሰበ ሲሆን፣ ማንኛውም የአገሪቱ ጉዳዮች በእርሳቸው በኩል እንዲያልፍ ይደረጋል።

እንደ አንድ የአገር መሪ በርካታ የአገር ውስጥ እና የውጭ አገር ባለሥልጣናትን እየተቀበሉ ያነጋግራሉ።

ኢሳያስ ከገባንበት አረንቋ ያወጣናል ብለው ባዶ ተስፋ ለተሞሉ ኤርትራውያንም የትኩረት ማዕከል ናቸው።

የ79 ዓመቱ አዛውንት በሥልጣን በቆዩባቸው ሦስት አስር ዓመታት ምርጫ አካሂደው አያውቁም።

በቅርብ ጊዜ ውስጥ ለውጥ እንደሚመጣ የሚያሳይ ጭላንጭልም የለም።

ይህ ግን በ1990ዎቹ እጅጉን በጣም የተለየ ነበር።

በአውሮፓውያኑ 1991 የኤርትራ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር (ሻዕቢያ) በትጥቅ ትግል መሪነት የኢትዮጵያ ወታደራዊ መንግሥትን ድል ባደረገበት ወቅት ኢሳያስ የ45 ዓመት ጎልማሳ ነበሩ።

ረዥም እና ማራኪ የሆኑት ኢሳያስ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ በሚገኙ ዘንድ የተስፋን ፈጥረው ነበር።

እንደ አውሮፓውያኑ በ1993 ኤርትራ በይፋ ነፃነቷን ካገኘች በኋላ፣ ኢሳያስ በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የኤርትራ መሪ ሆነው ብቅ አሉ።

በካይሮ በተካሄደው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የመሪዎች ጉባኤ ላይ በተገኙበት ወቅት "ለአስርት ዓመታት በሥልጣን ላይ መቆየት የፈለጉትን" የአፍሪካ መሪዎች ነቀፉ።

ኤርትራ ያን ያረጀ ያፈጀ አካሄድ በፍጹም እንደማትደግመው ቃል ገብተው፣ የሕዝባቸውን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚያረጋግጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንደሚያሰፍኑ ቃል ገብተው ነበር።

ይህ አቋማቸው ከኤርትራውያን እና ከዲፕሎማቶች ዘንድ አድናቆትን አትርፎላቸዋል።

ኢሳያስ በመጀመሪያዎቹ የነፃነት ዓመታት በነበረው የሥልጣናቸው የጫጉላ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሞቅ ያለ አቀባበል ሲደረግላቸው ከምዕራቡ ዓለም ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖራቸው ፈለጉ።

በአውሮፓውያኑ 1995 የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ቢል ኪሊንተን የኤርትራውን መሪ ወደ ዋይት ሐውስ ጋብዘው አገሪቱ በዲሞክራሲ ጎዳና ላይ ለጀመረችው ጠንካራ ጉዞ አድናቆታቸውን ገለፁ።

በወቅቱ ኤርትራ የሕግ የበላይነትን እና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ያሰፍናል ተብሎ የታሰበውን አዲስ ሕገ መንግሥት እያረቀቀች ነበር።

ፕሬዚደንት ኢሳያስ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እስኪመሠረት ድረስ "የሽግግር ፕሬዚደንት" እንዲሆኑ ነበር የታሰበው። አዲሱ ሕገ መንግሥት እአአ በግንቦት 1997 በሕዝብ ተወካዮች ሸንጎ በኩል ጸድቋል።

ነገር ግን በ1998 ኤርትራዊያን እና ዓለም አገራዊ ምርጫ ይካሄዳል ብለው ሲጠብቁ በኤርትራ እና በጎረቤት አገር ኢትዮጵያ መካከል በተፈጠረው አጨቃጫቂ ድንበር ምክንያት ጦርነት ተቀሰቀሰ።

ኢሳያስ ምርጫውን ላልተወሰነ ጊዜ ለማራዘም ጦርነቱን እንደ ምክንያት ተጠቅመዋል ተብለው ይከሰሳሉ።

የመድበለ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመፍጠር ቃል የገቡት ፕሬዚደንቱ፣ እአአ በ2000 የሰላም ስምምነት ከተደረሰ በኋላ ቁርጠኝነታቸው ተፈትሿል።

የቀድሞ የቅርብ ጓደኞቻቸው እና የትግል አጋሮቻቸውን ጨምሮ በርካታ ሚኒስትሮቻቸው በመንግሥታቸው ላይ ተሃድሶ እንዲደረግ ጥሪ ማቅረብ ጀመሩ።

እነዚህ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች በመጋቢት 2001 በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ፣ በኋላ ላይ ቡድኑ ጂ 15 ተብሎ መጠራት ጀምሯል፣ ፕሬዚደንቱን ሥልጣናቸውን አላግባብ ተጠቅመዋል እና ከጊዜ ወደ ጊዜ ፈላጭ ቆራጭ እየሆኑ መጥተዋል ሲሉ ቅሬታቸውን ገለፁ።

ሕገ መንግሥቱ እንዲተገበር እና አገር አቀፍ ምርጫ እንዲደረግም ጠየቁ።

እአአ ከ1990ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ብቅ ብቅ ያሉት ጋዜጦች በወቅቱ ህዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲ እና ለፍትህ (ህግዴፍ) ተብሎ ከተሰየመው ፓርቲ አባላት ጀምሮ የሌሎቹንም ጠንካራ አስተያየቶች ይዘው ይወጡ ስለነበር ኤርትራውያን ጥቂት ነጻነትን ማጣጣም ጀመሩ።

የሽግግር ብሔራዊ ሸንጎ ምርጫ መቼ እንደሚካሄድ ወስኖ፣ የምርጫ ኮሚሽን እየተቋቋመ እና የቀረቡ የፖለቲካ ፓርቲ ሕጎች ክርክር እየተካሄደባቸው ነበር።

አገሪቷ ቀስ በቀስ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መንገድ እየተጓዘች መሰለች።

ነገር ግን ይህ አዝጋሚ ጉዞ በመስከረም 2001 የዓለም ትኩረት በአሜሪካ ላይ ከተሰነዘረው የሽብር ጥቃት በኋላ በድንገት ተዘጋ።

የአገሪቱ መንግሥት አንድ ቀን ጠዋት፣ ጠንካራ ትችት በማቅረብ የሚታወቁትን ነጻ ጋዜጦች በሙሉ ዘጋ። በርካታ የጋዜጦቹ አዘጋጆች እና ጋዜጠኞች ታሰሩ እና ከዚያ በኋላም የነጻ ፕሬስ ወሬ አልተሰማም።

በተመሳሳይ ሁኔታ መንግሥት ጂ15 [ቡድን 15] ተብለው ከሚታወቁት ውስጥ 11ዱን በቁጥጥር ስር ያዋለ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም እና በርካታ የብሔራዊ ምክር ቤት አባላት ይገኙበታል።

ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እነዚህ ግለሰቦች ስላሉበት ሁኔታ የተሰማም የታየም ነገር የለም።

ከዚያ ጊዜ አንስቶ የበርካታ ኤርትራዊያን ተስፋ እንደ ጉም በኖ ጠፋ።

ነገር ግን ኢሳያስ ቀድሞውንም ቢሆን ዴሞክራሲያዊ ለውጦችን ከማስተዋወቅ በብዙ መንገድ ርቀው ነበር።

በአውሮፓውያኑ ሚያዝያ 2001 ፕሬዝዳንቱ "በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የመሳተፍ ፍላጎት ኖሮኝ አያውቅም" ሲሉ ተናግረዋል።

"አሁን በፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ የመሳተፍ ፍላጎት የለኝም፤ ወደፊትም ቢሆን በፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ የመሳተፍ ፍላጎት የለኝም።"

ዴሞክራሲያዊ ሒደቱን "ውዥንብር" ሲሉ የጠሩት ሲሆን፣ ህግዴፍ "ፓርቲ አይደለም፣ አገር ነው" ሲሉም የፓርቲያቸውን አይነኬነት አብራርተዋል።

ለብዙዎች ፕሬዚዳንቱ የዴሞክራሲ ማሻሻያዎችን ለማድረግ እንደማይፈቅዱ ግልጽ ሆነ።

የተቃውሞ ድምጾችን ማፈናቸው እና ምርጫ አለማካሄዳቸው እርሳቸውንም ሆነ አገሪቱን እንድትገለል አድርጓል።

ሆኖም ደጋፊዎቹ በምዕራባውያን አገራት ኢፍትሃዊ በሆነ መልኩ መገለል እንደ ደረሰባቸው በመግለጽ፣ ኢሳያስን የብሔራዊ ነጻነት ምልክት በማድረግ ያሞካሽዋቸዋል።

ፕሬዚደንት ኢሳያስ እአአ በ2002 የሽግግር ምክር ቤቱ ይፋዊ ባልሆነ መንገድ አፍርሰዋል፤ በ 2018 ካቢኔው ላይ ተመሳሳይ እርምጃ ወስደዋል።

አንዳንድ በዕድሜ የገፉ እና ምንም እውነተኛ ሥልጣን የሌላቸው ሚኒስትሮች አሁን ደካማ የመንግሥት ቢሮዎችን ይመራሉ።

እና በርካታ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣ መከላከያን ጨምሮ ያለ ሚኒስትር ይመራሉ።

ብዙዎች የነፃነት ጀግና የነበሩት ግለሰብ ለምን እንዲህ ዓይነት አፋኝ የሆነ እርምጃን እንደወሰዱ ይጠይቃሉ።

የቀድሞው የክልል አስተዳዳሪ እና ከፍተኛ አምባሳደር አብደላ አደም ኢሳያስ በዴሞክራሲ ፈጽሞ እንደማያምኑ እናም ሁልጊዜም የሥልጣን ጥማት እንደነበራቸው ይናገራሉ።

አሁን በለንደን በስደት የሚኖሩት አብደላ እንደሚሉት ከሆነ ኢሳያስ ከነጻነት በፊትም ቢሆን ሻዕቢያን በጠንካራ መዳፎቹ ስር በማድረግ ይመሩ ነበር።

"ሥልጣኑን ሊገዳደሩ የሚችሉ ሕዝባዊ ቅቡልነት እና የትግል ብቃት ያላቸውን መሪዎች በስልታዊ መልኩ አዳክሞ ከሥልጣን አስወግዷል" ይላሉ።

ፕሬዚደንት ኢሳያስ በግንቦት 2014 (እአአ) አዲስ ሕገ መንግሥት የማዘጋጀት ዕቅድ እንዳላቸው ያስታወቁ ሲሆን፣ በኋላም በ1997 የፀደቀው ሕገ መንግሥት "አክትሞለታል" ሲሉ ተናግረዋል።

ነገር ግን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አልታየም።

አዲስ ሕገ መንግሥት የማርቀቅ ሃሳብ የመጣው እአአ በ2013 በከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ምክንያት ሊሆን ይችላል።

ወታደራዊ መኮንኖቹ ታንኮችን በዋና መዲናዋ አሥመራ እየነዱ ለበርካታ ሰዓታት የብሔራዊ ቴሌቪዥን እና የሬዲዮ ጣቢያዎችን ተቆጣጥረው ቆይተዋል።

ሙከራው መክሸፉን የተረዱት ወታደራዊ መኮንኖች፣ በመገናኛ ብዙኃኑ የ1997ቱ ሕገ መንግሥት ተግባራዊ እንዲደረግ እና የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ጥሪ ለማቅረብ ሞክረዋል። ነገር ግን የፀጥታ ኃይሎች ሥርጭቱ እየተላለፈ እያለ አቋርጠውታል።

የማዕድን ሚኒስትሩን ጨምሮ በርካታ ባለሥልጣናት፣ አስተዳዳሪዎች፣ ዲፕሎማቶች እና ጄነራሎች ታስረዋል። የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ በቁጥጥር ስር ከመዋላቸው በፊት ራሳቸውን አጥፍተዋል።

በናይጄሪያ ዲፕሎማት የነበሩት ዘርዓ ሥላሴ ሺከር ሥራቸውን ትተው በዩናይትድ ኪንግደም ጥገኝነት ጠየቁ።

በነጻነት ትግሉ ውስጥ የተሳተፉት እና በናይጄሪያ የኤርትራ አምባሳደር የነበሩት አሊ ኦሜሩ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ የበላቸው ጅብ አልጮኽም።

አሁን በዩናይትድ ኪንግደም ሊድስ ዩኒቨርሲቲ የፒኤችዲ ተማሪ የሆኑት ዘርዓ ሥላሴ እንደ ኢሳያስ አፈወርቂ ሰዎችን የሚያስሩ መንግሥታት "እውነተኛ የፖለቲካ እና ማኅበራዊ ተቋማትን ወይም የሕግ የበላይነትን አይፈቅዱም" ይላሉ።

አክለውም "የኤርትራ ሕገ መንግሥት ላልተወሰነ ጊዜ መታገዱ እና የመንግሥት ተቋማት ለፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ተጠሪ መሆናቸው ከዚህ አንፃር መታየት አለበት" ብለዋል።

ከዓለም አቀፍ መድረክ የተነጠሉት ኢሳያስ ራሳቸውን ከዓለም አቀፍ መድረክ አግልለዋል።

እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ እና የአፍሪካ ኅብረት ያሉ ስብሰባዎች ላይ መሳተፍ ካቆሙ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል።

የዓለም ባንክ ባለፈው ዓመት ባደረገው ግምገማ የአገሪቱ ኢኮኖሚ "ፈተና ውስጥ ነው" ብሏል።

የዓለም ባንክ ባለሙያዎች "የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ባልዳበረ መሠረተ ልማት የተነሳ፣ በመንግሥት የበላይ ተቆጣጣሪነት በሚካሄድ ውሱን ውድድር እና የገቢ እቃዎች ጥብቅ ቁጥጥር ታንቋል" ካሉ በኋላ የፋይናንስ ዘርፉ ለረጅም ጊዜ "ደካማ" ሆኖ ቆይቷል ብለዋል።

ፕሬዚደንት ኢሳያስ ባለፈው ታኅሣሥ ላይ ከመንግሥት ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ችግሮቹን አምነዋል።

"ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኢኮኖሚ የትም አያደርሰንም። በአሁኑ ወቅት በዚህ ረገድ ከበርካታ የአፍሪካ አገራት የተሻለ ደረጃ ላይ አይደለንም" ብለዋል።

በተጨማሪም ኢሳያስ የሰብዓዊ እርዳታን "ራስን መቻል" የሚለውን መርኅን የሚያናጋ ጥገኝነትን ያመጣል በሚል ፍራቻ አይቀበሉም።

ለብዙ ኤርትራውያን፣ በተለይም ማብቂያ በሌለው ብሔራዊ አገልግሎት ውስጥ ገብተው መላወሻ ላጡ ወጣቶች፣ የዕለት ተዕለት ኑሮው በጣም ከባድ ነው።

በአፋኝ አገዛዝ ውስጥ መጻዒ ጊዜያቸውን ብዙም ተስፋና ነፃነት ሳይኖራቸው ይገፋሉ።

በፖለቲካዊ ዕድገት እጦት ግራ የተጋቡ፣ በግዳጅ ውትድርና እና በመንግሥት የኃይል እርምጃ የተሰላቹ በርካታ ኤርትራውያን ነፃነት ፍለጋ ሕይወታቸውን ለአደጋ ያጋልጣሉ።

ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን አገራቸውን ጥለው በበረሃዎች ውስጥ በማቋረጥ አስተማማኝ መሸሸጊያ ፍለጋ ተሰድደዋል።

ዩናይትድ ኪንግደም ስደተኛ አድርጋ ከተቀበለቻቸው የውጭ አገር ዜጎች መካከል ኤርትራውያን በሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ኢሳያስ ባለፈው ወር በነጻነት ቀን ላይ ባደረጉት ንግግር ብዙ ኤርትራውያን ለማየት ተስፋ ስለሚያደርጉት ለውጥ ምንም ፍንጭ አልሰጡም። ስለ ሕገ መንግሥት፣ ብሔራዊ ምርጫ ወይም የፖለቲካ እስረኞች መፈታት ያሉት ነገር የለም።

በተመሳሳይም እየሞተ የሚገኘውን የአገሪቱን ምጣኔ ሀበት እንዲያንሰራራ ለማድረግ የሚያስችል ተጨባጭ ዕቅድ አልታየም።

ፕሬዚደንት ኢሳያስ በአገር ውስጥ ትችት ቢሰነዘርባቸውም በተወሰኑ አካላት በተለይም በወታደሩ፣ በገዥው ፓርቲ የቅርብ ሰዎች እና እርሳቸውን የብሔራዊ ነፃነት ምልክት እና የውጭ ጣልቃ ገብነትን የተቋቋሙ አድርገው በሚመለከቱት ወገኖች ዘንድ ድጋፍ አላቸው።

ፕሬዚደንቱ ምዕራባውያን ኃይሎች ኤርትራ በትግል ያገኘችውን ነጻነት ለማናጋት እያሴሩ ናቸው ብለው በሚያምኑ ዲያስፖራዎች ዘንድም ጠንካራ ድጋፍ አላቸው።

ኤርትራ ውስጥ ተስፋ መቁረጥ እየጨመረ ሲመጣ፣ ፕሬዚደንት ኢሳያስ እአአ ከ2014 ጀምሮ ግንባታውን በቅርበት በሚከታተሉት አዲ ሀሎ ግድብ አቅራቢያ ወደ ሚገኘው አና ከአሥመራ ወጣ ብሎ በሚገኘው መኖርያ ቤታቸው ከትመዋል።

ኢሳያስ ዕድሜያቸው ወደ 80 ሲጠጋ ብዙዎች ቀጥሎ ምን ሊፈጠር ይችላል ብለው ይሰጋሉ።

የበኩር ልጃቸውን ተኪያቸው አድርገው ለማምጣት ያደረጉት ሙከራ እአአ በ2018 ለመጨረሻ ጊዜ በተደረገው የካቢኔ ስብሰባ ላይ ውድቅ ተደርጓል።

ነገር ግን አሁን ያለውን አገዛዝ ሊተካ የሚችል ግልጽ የሆነ የመተካካት ዕቅድም ሆነ ተዓማኒ የሆነ ተቃዋሚ በአገሪቱ ስለሌለ ለብዙዎች ከፕሬዚደንት ኢሳያስ ውጪ የአገሪቱን የወደፊት ዕጣ ፈንታ መገመት አዳጋች ሆኖባቸዋል።

ዘርዓ ሥላሴ "አገሪቱን ከውድቀት የታደጋት የፕሬዚዳንቱ ጽህፈት ቤት ነው" ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።

በዘንድሮው የትንሳኤ በዓል በአሥመራ በሚገኝ አንድ ቤተ ክርስቲያን በነበረ ክብረ በዓል ላይ ኢሳያስ መስቀል ሲሳለሙ ታይተዋል።

አንዳንዶች ፕሬዚደንቱ መንፈሳዊ ድህነትን እንደሚፈልጉ ሲናገሩ ሌሎች ደግሞ የፖለቲካ እስረኞችን ይፈቱ ይሆናል ሲሉ ተስፋ ያደርጋሉ።

አሁንም ኤርትራ በኢሳያስ ጠንካራ መዳፎቹ ስር በመሆኗ ኤርትራዊያን ለረዥም ጊዜ በጉጉት እና በጭንቀት የሚጠብቁትን ለውጥ መጠበቅ ይቀጥላሉ።