ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ካናዳ፣ሜክሲኮ እና ቻይና ከዛሬ ጀምሮ ታሪፍ እንደሚጣልባቸው ዋይት ሃውስ አስታወቀ
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሜክሲኮ እና በካናዳ 25 በመቶ እንዲሁም በቻይና 10 በመቶ ታሪፍ ቅዳሜ፣ ጥር 24/ 2017 ዓ.ም እንደሚጥሉ ዋይት ሐውስ አስታወቀ።
ነገር ግን ትራምፕ አርብ ዕለት አገሪቱ ከካናዳ በሚገባው ዘይት ላይ የምትጥለው ታሪፍ 10 በመቶ እንደሚሆንና ይህም ከሁለት ሳምንታት በኋላ ተግባራዊ እንደሚሆን ተናግረዋል።
ትራምፕ አሜሪካን በጥሩ መልኩ አላስተናገዳትም ባሉት የአውሮፓ ኅብረት ላይም ታሪፍ ለመጣል ማቀዳቸውን ገልጸዋል።
በካናዳ እና በሜክሲኮ ላይ የሚጣለውን ታሪፍ አስመልክቶ የተናገሩት የዋይት ሐውስ የፕሬስ ሴክሬታሪ ካሮሊን ሌቪት "እርምጃው በአስር ሚሊዮን የሚቆጠሩ አሜሪካውያንን ሕይወት የቀጠፈውን ሕገወጥ ፌንታኒል ምንጭ በመሆናቸው እንዲሁም በአገራችን በማከፋፈላቸው የተሰጠ ምላሽ ነው።" ብለዋል።
ትራምፕ በበኩላቸው የታሪፍ መጣል እርምጃቸው ድንበሮቻቸውን አቋርጠው የመጡ ከፍተኛ መጠን ያላቸው ሰነድ አልባ ስደተኞችን ምክንያት ያደረገ እንዲሁም ከጎረቤት አገሮች አገር ያለውን የንግድ ሚዛን ጉድለት ለማመጣጠን ነው ሲሉ በተደጋጋሚ ተሰምተዋል።
የፕሬስ ሴክሬታሪዋ አርብ ዕለት በዋይት ሐውስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ "እነዚህ በፕሬዚዳንቱ ቃል የተገቡ እንዲሁም ቃል በገቡት መሰረት የተፈጸሙ ናቸው" ብለዋል።
ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ቻይና ሰራሽ ምርቶች ላይ እስከ 60 በመቶ የሚደርስ ታሪፍ እንደሚጥሉ ዝተው ነበር።
ነገር ግን ወደ ዋይት ሐውስ በተመለሱ በመጀመሪያ ቀናቸው ምንም አይነት አፋጣኝ እርምጃ ከመውሰድ ተቆጥበው አስተዳደራቸው ጉዳዩን እንዲያጠና መመሪያ ሰጥተዋል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት አንድ የቻይና ከፍተኛ ባለሥልጣን አገራት ምርቶቻችን ለመጠበቅ ነው በሚል የሚጥሉትን ታሪፍ አስመልክቶ ማስጠንቂያ ሰጥተዋል።ባለስልጣኑ አሜሪካን በስም ባይጠቅሷትም የትራምፕ ወደ ሥልጣን መመለስ በዓለም ሁለት ታላላቅ ምጣኔ ኃብቶች መካከል የንግድ ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ስጋት መደቀኑ እየተነገረ ነው።
የቻይናው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ዲንግ ዙዢያንግ በበኩላቸው አገራቸው የንግድ ውጥረቶችን ለማርገብ "ሁሉም አሸናፊ" ሆነው የሚወጡበት መፍትሄ እየፈለገች እንደሆነ ተናግረዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ ቻይና ከውጭ የምታስገባቸውን ምርቶች ማስፋት እንደምትፈልግ በስዊዘርላንድ ዳቮስ በተካሄደው የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ተናግረዋል።
ቻይና፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ የአሜሪካ ቀዳሚዎቹ የንግድ አጋሮች ሲሆኑ ባለፈው አመት አገሪቷ ካስገባቻቸው ምርቶች 40 በመቶውን ይሸፍናሉ።
ትራምፕ የሚጥሉት ታሪፍ የንግድ ጦርነት ሊቀሰቅስ እንዲሁም በአሜሪካ ውስጥ ከፍተኛ የዋጋ ንረት ሊያስከትል ይችላል የሚል የበርካቶች ስጋት እየጨመረ ነው።