ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሊቢያ "ለባርነት ጨረታ" ቀርባ የነበረችው ኢትዮጵያዊት 700 ሺህ ብር ተከፍሎ ነጻ መውጣቷን ተናገረች
ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሊቢያ "ለባርነት ጨረታ ቀርባ" የነበረችው ኢትዮጵያዊቷ ነሒማ ጀማል ለአጋቾቿ 700 ሺህ ብር ተከፍሎ ነጻ መውጣቷን ከቢቢሲ ጋር በስልክ ባደረገችው ቆይታ ተናገረች።
በፎቶዎች እና በቪዲዮዎች ላይ አፏ በጨርቅ ተለጉሞ ስቃይ ሲደርስባት ትታይ የነበረችው ነሒማ በቤተሰቧ አማካይነት ገንዘብ ከኢትዮጵያ ተሰባስቦ ከተላከ በኋላ ከሁለት ቀናት በፊት አጋቾቿ ወደ ከተማ አምጥተው እንደለቀቋቸው ለቢቢሲ አስረድታለች።
ታግታ ከነበረችበት ስፍራ እሷን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ቢኖሩም የተለቀቁት ገንዘብ የተከፈለላቸው "ውስን ሰዎች ነበሩ" ብላለች ከቢቢሲ ጋር በነበራት አጭር ቆይታ።
በአሁኑ ወቅት በሊቢያ የምትገኝ ሲሆን "ድካም እና ህመም ላይ" እንደሆነች የምትናገረው ነሒማ፣ ድምጿም የተረበሸች እንደሆነ የሚያስታውቅ ሲሆን "ከዚህ በኋላ ምን እንደሚፈጠር አላውቅም፤ ስልክ መደወልም ሁሉም ነገር ያስፈራል" ስትል ጭንቀት ላይ እንደሆነች እና ማውራት እንደሚከብዳትም ተናግራለች።
ሬፊዩጂስ ኢን ሊቢያ የተባለው በሊቢያ የሚገኙ ስደተኞችን ጉዳይ የሚከታተለው ተቋም ነሒማ ታግታ በነበረበት ወቅት በኤክስ ገፁ እንዳስታወቀው ነሒማ እና ሌሎች ስደተኞች በታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር በምትገኘው ኩፍራ በምትባል ግዛት ውስጥ እንደነበሩ አስታውቆ ነበር።
አጋቾቹ ነሒማ እንድትለቀቅ ስድስት ሺህ ዶላር እንዲከፈላቸው ጠይቀው ነበር። ለነሒማ ቤተሰብ የተላኩ ቪዲዮዎች ስደተኞቹ በአሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ያሳዩ ነበሩ።
ነሒማም እጅ እና እግሯ ተጠፍሮ፤ አፏ በጨርቅ ታፍኖ ትታያለች። ስቃይ ሲደርስባት እና ደም በደም ሆና የሚያሳዩ ቪዲዮዎች እና ፎቶዎችም አሉ።
ድርጅቱ በለቀቃቸው ቪዲዮዎች እና ፎቶዎች ላይ ነሒማ ብቻ ሳትሆን 50 ገደማ ሌሎች የአጋቾቹ ሰለባዎች ከጀርባዋ ተደርድረው ይታዩ ነበር።
ተማሪ የነበረችው ነሒማ ከኦሮሚያ ክልል ሻሸመኔ፣ በአዲስ አበባ በኩል ወደ በጎንደር በማምራት ከኢትዮጵያ በመውጣት ነበር ወደ ሊቢያ ያቀናችው።
ኢትዮጵያ ውስጥ የምታውቀው ግለሰብ ሥራ አለ ብሏት ነበር ወደ ሊቢያ ያቀናችው። በወቅቱ ለልጁ የከፈለችው ገንዘብ ባይኖርም የተወሰኑ ጓደኞቿን አጥታ ነው ሊቢያ የደረሰችው።
አዲስ አበባ የተዋወቃቻቸው ሁለት ኢትዮጵያውያን ወንዶች በሰሃራ በረሃ በውሃ ጥም ሕይወታቸው አልፏል ብላለች።
ሰውነታቸው ዝሎ እና ደክሞ የሞቱ ጓደኞቻቸውን ለመቅበር "ጉልበት አልነበረንም" የምትለው ነሒማ፤ ከኢትዮጵያ መውጣቷ የሚያስቆጫት ቢሆንም፣ ከዚህ ሁሉ ስቃይ በኋላ ወደ አገር ቤት የመመለስ ዕቅድ ግን የላትም።
"እንደ አምላክ ፈቃድ ሌላ አገር ነው መሄድ የማስበው" ብላለች።
ነገር ግን ለሌሎች ስደትን አማራጭ ለሚያደርጉ "አገራቸው ውስጥ ቢቀመጡ ይሻላቸዋል። መንገድ ላይ በሽታ አለ፣ ሞት አለ። ብዙ ጓደኞቼ መንገድ ላይ ሞተዋል" ብላለች።
የነሒማ ቤተሰቦችን ቢቢሲ ከዚህ ቀደም ባናገራቸው ወቅት ቪዲዮዎች እና ፎቶዎች ተልኮላቸው የማስለቀቂያ ገንዘብ እንዲከፍሉ ማስጠንቀቂያ እንደደረሳቸው ገልጸው ነበር።
የነሒማ እህት ኢፍቱ ጀማል፤ ነሒማ ከስምንት ወራት በፊት ነበር ከሻሸመኔ ከተማ የ11ኛ ክፍል ትምህርቷን አቋርጣ ወደ ሊቢያ የተሰደደችው ስትል ለቢቢሲ ትናገራለች።
"ፎቶዎች እና ቪዲዮዎች ይልኩልናል። ስትሰቃይ ያሳዩናል። የድምፅ መልዕክትም ልከውልናል። እህታችን 'ገንዘብ ላኩላቸው ካልሆነ ይገድሉኛል' ስትል ይሰማል" ብላ ነበር።
ሬፊዩጂስ ኢን ሊቢያ እንደሚለው የ20 ዓመቷ ነሒማ ጀማል ባለፈው ግንቦት ሊቢያ ከገባች ከቀናት በኋላ ነው በታጣቂዎቹ እጅ ውስጥ የገባችው።
በቁጥጥር ሥር ከዋለች በኋላ ስቃይ ሲደርስባት እና ስትደበደብ የሚያሳዩ ፎቶዎች እና ቪዲዮዎች ለቤተሰቦቿ ተልከዋል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በሊቢያ እየተካሄደ ያለውን የባርነት ንግድ ዓለም ረስቶታል ሲሉ ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ይወቅሳሉ።
መብት ተሟጋች ቡድኖች ሊቢያ በተለይ ለጥቁር አፍሪካውያን ስደተኞች መካነ መቃብር ሆናለች ይላሉ። አክለውም መሰል የእገታ ድርጊቶችን የሚፈፅሙ 'ታጣቂዎች ለምንድነው የማይጠየቁት?' ሲሉ ይጠይቃሉ።
በርካታ ኢትዮጵያውያን እና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ስደተኞች ሕይወታቸውን ለመቀየር በሚል ወደ አውሮፓ በሚያደርጉት ጉዞ የሜዲቴራኒያን ባሕርን ከማቋረጣቸው በፊት ሊቢያን ይረግጣሉ።