ዛምቢያ በዘረኛ ቪደዮዎች የተጠረጠረውን ቻይናዊ አሳልፋ ሰጠች

የቢቢሲ የምርመራ ጋዜጠኝነት ቡድን 'አፍሪካ አይ' በቻይና የማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚሰራጩ ዘረኛ ቪዲዮችን በማዘጋጀት ያጋለጠውን ቻይናዊ የዛምቢያ መንግሥት ድርጊቱን ፈጽሞበታል ለተባለባት ማላዊ አሳልፎ ሰጠ።

እነዚህ ዘረኛ ቪዲዮዎች በቻይና እስከ 70 ዶላር የሚሸጡ ሲሆን በተለይም በአፍሪካዊያን ሕጻናት የሚሰሩት ቪዲዮች በርካታ ተመልካች አላቸው።

ሉ ኬ የተባለው ተጠርጣሪ አፍሪካውያን ሕጻናት በማይረዱት ቋንቋ የገንዘብ ማባባያ በመስጠት በሚያዋርድ ሁኔታ በቀረጻቸው ቪዲዮዎች በቢቢሲ 'አፍሪካ አይ' የምርመራ ዘገባ ሲጋለጥ ነዋሪነቱ በማላዊ ነበር።

በምርመራ ዘገባው እንደተጋለጠው፣ ቻይናዊው ዘረኛ ይዘት ያላቸውና ለግል የተሰናዱ የሰላምታ ቪዲዮዎችን ሲቀርጽ በአካባቢው ያሉ ክፉ ደጉን የማይለዩ ሕጻናትን ተጠቅሟል።

ግለሰቡ እነዚህን አጸያፊ ቪዲዮዎች አልሰራሁም በሎ የካደ ሲሆን ቪዲዮዎቹን የሰራውም የቻይናን ባህል ለማስፋፋት በማሰብ እንደሆነ ተናግሯል።

ባለፈው ሳምንት በዛምቢያ በቁጥጥር ስር የዋለው ቻይናዊው ወደ አገሪቱ በሕገ-ወጥ መንገድ በመግባቱ የገንዘብ ቅጣት ተጥሎበታል።

የማላዊ ዋና ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሆኑት ታአቦ ቻካካ ግለሰቡ ተላልፎ መሰጠቱን ብሎም በሕጉ መሰረት ሰኞ ወደ ችሎት እንደሚቀርብ አረጋግጠዋል።

ይህንን ምርመራ ተከትሎም ኢትዮጵያን ጨምሮ የበርካታ የአፍሪካ አገራት ዜጎች በቻይና ባሉ ማኅበራዊ ሚዲዎች በተመሳሳይ የዜጎቻቸውን ሰብአዊ ክብርን በሚያዋርዱ ብሎም ዘረኛ ይዘቶች ባላቸው ቪዲዮዎች ውስጥ መመልከታቸውን ሲገልጹ ነበር።

ኢትዮጵያዊያን ሴቶችን የሚያዋርዱ ዘረኛ ቪዲዮዎችም በተመሳሳይ ቢቢሲ በሰራው ተከታይ ምርመራ ላይ ማጋለጥ ችሏል።

ኢትዮጵያውያኑ ሴቶች በማየውቁት ቋንቋ ክብር የሚነኩ ቃላትን በማናገርም ቪዲዮዎቹን በመቅረጽ በቻይና የማኅበራዊ ሚዲየዎች ላይ ተሰራጭተዋል።

የአፍሪካ አይን ዘገባ ተከትሎ የቻይና መንግሥት ከፍተኛ ዲፕሎማት በሰጡት ምላሽም አገራቸው እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት ትቃወማለች ብለዋል።

“ቻይና ባለፉት ዓመታት በእንዲህ አይነት መስመር ያለፉ ሕገ ወጥ ድርጊቶች ላይ እርምጃ ስትወስድ ቆይታለች” ሲሉም በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

“ወደፊትም እንደዚህ ዓይነት ዘረኝነትን የሚያንጸባርቁ ቪዲዮዎችን ለማስቆም መስራታችንን እንቀጥላለን” ሲሉም ዲፕሎማቱ አክለዋል።