ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጣልያናዊቷ መነኩሴ የወንጀለኞች ቡድን ከሆነ ማፊያ ጋር አብረው ይሠራሉ በሚል ታሰሩ
የጣልያን ፖሊስ በወንጀለኛ ቡድን ላይ ከሚያደርገው ምርመራ ጋር በተያያዘ 24 ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ያዋለ ሲሆን፣ ከታሰሩት መካከል አንዲት መነኩሴ እንደሚገኙበት ተገለጸ።
በሰሜን ጣልያን ከሚደረገው የወንጀለኛ ቡድን (ማፊያ) ምርመራ ጋር በተያያዘ የታሰሩት መነኩሴ አና ዶኔሊ ይባላሉ።
ንዴራንጌህታ የተባለው የማፊያ ቡድን አባላት ሲታሰሩ ለቡድኑ አባላት መልዕክት የሚያስተላልፉት እኚህ መነኩሴ እንደሆኑ ፖሊስ ያምናል።
ከዚሁ ዘመቻ ጋር በተያያዘ ፖሊስ ሁለት ፖለቲከኞችንም አስሯል። በተጨማሪም በሎምባርዲ፣ በቬኒቶ እና ካላብራ ከተሞች ከ1.8 ሚሊዮን ዩሮ በላይ የሚያወጣ ሃብት ንብረት በቁጥጥር ሥር አውሏል።
ማፊያ የተባለው የወንጀለኛ ቡድኑ በአውሮፓ አደገኛ ከሚባሉ ቡድኖች አንደኛው ሲሆን፣ ፖሊስ ለአራት ዓመታት ምርመራ ሲያደርግ ነበር።
ምርመራውን ያካሄዱት የፖሊስ ባልደረቦች ባወጡት መግለጫ እንዳሉት፣ መነኩሴዋ እስር ቤት በነጻነት የመግባት እና የመውጣት መብታቸውን ተጠቅመው በወንጀለኛ ቡድኑ አባላት መካከል መረጃ ሲያቀባብሉ ነበር።
"ማንም እሷን አይጠረጥርም። በሃይማኖት ምክንያት ወደ እስር ቤቱ በነጻነት መግባት እና መውጣት ትችል ነበር" ሲል መርማሪ ቡድኑ አስታውቋል።
ከምርመራው በኋላ የታሰሩ ፖለቲከኞችን ማንነት እንዲሁም ከወንጀል ቡድኑ ጋር ግንኙት አላቸው በሚል የተመረመሩትን ማንነት ይፋ አላደረገም።
ፖሊስ አሁንም በሰሜን ጣልያን ፍተሻ እያደረገ ይገኛል።
በአነፍናፊ ውሾች በመታገዝ መሣሪያ፣ አደንዛዥ ዕፅ እና ገንዘብ እየተፈለገ ነው።
የወንጀል ቡድኑ ቁርጥራጭ ብረት በመሸጥ ስም ሕገ ወጥ ገንዘብን ወደ ሕጋዊ መስመር ያስገባ እንደነበር ፖሊስ አስታውቋል።
የወንጀል ቡድኑ መነሻ ካላብሪያ ከተማ ስትሆን ከአውሮፓ ባሻገር በዓለም አደገኛ ከሚባሉ ቡድኖች መካከል አንደኛው ነው።
ያለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት ላይ በጣልያን ታሪክ ትልቁ በተባለ በማፊያ የወንጀለኛ ቡድን አባላት ላይ በተካሄደ የፍርድ ሂደት ላይ 200 ሰዎች ከ2,200 ዓመታት በላይ እስር ተፈርዶባቸዋል።