ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ባሻር አል-አሳድ የት ናቸው? በርካታ አሉባልታ እየተሰራጨ ቢሆንም በይፋ ውድቅ ተደርጓል
በደማስቆ ያለው ግራ የመጋባት እና የፍርሀት ስሜት ይመስላል። የአማጺ አንጃዎች ወደ ከተማዋ ይበልጥ እየተቃረቡ በሄዱበት ወቅት ብዙዎች ምን እየሆነ እንዳለ በትክክል ማወቅ አልቻሉም።
በበርካታ የከተማ አካባቢዎች የአሳድ ሥርወ መንግሥትን የሥልጣን ዘመን የሚያሳዩ የሚመስሉ ምልክቶች ፈርሰዋል ወይም ተቀዳደዋል።
የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በመዲናዋ ዙሪያ በብረት ታጥሯል ብሏል።
በመላ ሀገሪቱ ባሉ በከተሞ እና መንደሮች ውስጥ የመንግሥት ሃይሎች ምንም አይነት መከላከል ሳያደርጉ አማፂ ቡድኖች እጅ ወደቀዋል።
ፕሬዚደንት ባሻር አል-አሳድ ያሉበትን ቦታ በተመለከተ አሉባልታ እየተናፈሰ ሲሆን ሰዎች ወደ ደማስቆ እየገቡ እና እየወጡ ያሉ በረራዎችን በመከታተል እውነታውን ለማወቅ እየሞከሩ ነው።
የፕሬዝዳንቱ ቢሮ አሁንም በደማስቆ በሥራ ላይ እንደሚገኙ በመግለጽ ሁሉንም ዘገባዎች ውድቅ ቢያደርግም ግን እስካሁን አልታዩም።
ለአራት ዓመታት ያህል የቆየው አንጻራዊ መረጋጋት ከሳምንት በፊት ተመልሶ ቢናድም የሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ለዓመታት ያስከተለው ጥልቅ ጠባሳ ካለመሻሩም በላይ አገሪቱ የተከፋፈለች ሆና ቆይታለች።
በአረብ መሪዎች መካከል የአሳድ ፓሪያዊ አቋም አብቅቷል፣ ነገር ግን በሶሪያ ውስጥ ከጦርነት በኋላ ለሕዝቦቿ ተስማሚ የሆነ የወደፊት ሁኔታ ለመገንባት ምንም አይነት እድገት አልተገኘም።
ፕሬዚዳንት አሳድ ለዓመታት በአረብ መሪዎች ዘንድ የነበራቸው መገለል ቢያከትምም ከጦርነቱ በኋላ ለአገሪቱ ሕዝብ ጠብ የሚል መፍትሔ መስጠት አልቻሉም።
ፕሬዝዳንቱ አሁን ከኃላፊነት ከተነሱ ክፍተቱ የሚሞላበት መንገድ ግልጽ አይደለም። ሥልጣንን ለመረከብ የተቀናጀ ተቃዋሚ የለም። የአማጽያኑ የመከፋፈል እና የእርስ በርስ ግጭት ታሪክ አላቸው።
በፕሬዚዳንት አሳድ ላይ የተጀመረውን አዲሱን አመጽ የመራው ቡድን መነሻው በጽንፈኛው አልቃይዳ ውስጥ ነው።
መሪው በሶሪያ ውስጥ ባሉ ሌሎች ማህበረሰቦች ላይ ርዕዮተ ዓለሙን እንደማይጭንባቸው በመንገር ለማረጋጋት ቢሞክሩም ብዙዎች ግን ሊመጣ የሚችለውን ነገር በማሰብ በመፍራት ላይ ናቸው።
የተለያዩ ወገኖች ሥልጣን ለመቆጣጠር እርስ በርስ ስለሚፋለሙ ሶሪያ ወደከፋ ሁኔታ ልትገባ ትችላለች የሚል ጨምሯል።
ቀድሞውንም ያልተረጋጋ እና ተለዋዋጭ በሆነው የዓለም ክፍል ይህ የበለጠ አደገኛ አለመረጋጋት ሊፈጥር ይችላል።
አሁን ግን ቢያንስ በርካታ ሶርያውያን የተሻለ ነገር እመጣል በሚል ተስፋ ሰንቀዋል።