ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ምርጫ 97፡ ከ20 ዓመታት በኋላ ሲታወስ
1997 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የዘመን መቁጥሪያ ላይ ያለ ጊዜ ብቻ አይደለም። ዓመቱ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ዐበይት ሁኔታ ከተከሰተባቸው ዓመታት ተጠቃሹ ነው።
ከ66ቱ አብዮት ከ1983ቱ የመንግሥት ለውጥ ጋር ባይስተካከልም 97 ራሱን የቻለ የታሪክ ዕጥፋት ነው።
ከ20 ዓመታት በፊት በወርሃ ግንቦት 1997 ዓ.ም. በአገሪቱ ታሪክ ያልታየ እንዲሁም ያልተደገመ ጠቅላላ ምርጫ ተካሄደ።
የኢትዯጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ሥልጣን ከያዘ በኋላ የተካሄደው ይህ ሦስተኛው አጠቃላይ አገራዊ ምርጫ ነው።
ምርጫ 97 ቀደም ብለው ከተካሄዱት ምርጫዎች በመራጮች ብዛት የላቀ ነበር። በ1987 እና 1992 በተካሄዱት ምርጫዎች የተመዘገቡት መራጮች ቁጥር ከ21 ሚሊዮን በላይ ሲሆን፣ በ97 የተመዘገቡት ደግሞ 27.3 ሚሊዮን ነበር።
ከ20 ዓመታት በፊት የተካሄደው ምርጫ ከቀድሞዎች የሚለየው ግን በመራጮች ቁጥር ብቻ አይደለም።
"ምርጫ 97 ብዙኃንን ስሜታዊ ያደረገ ብዙ ተስፋ እና ፍራቻ የነገሰበት ነበር" የሚለው ጦማሪው እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ በፍቃዱ ኃይሉ፤ "በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ እና ለመጨረሻ ጊዜ ዴሞክራሲያዊ ፉክክር እና የምርጫ ሂደት ያየነው ያኔ ነው" ሲል የምርጫውን ሂደት ያስታውሳል።
በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የሰብዓዊ መብቶች ፕሮግራም ተባባሪ ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር አባድር ኢብራም በበኩሉ "ምርጫ 97 በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ ውስጥ በጣም ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ነበር" ይላል።
የታሪክ ተመራማሪው ጃን አብኒክ ምርጫ 97ን ሲገልጹት "ምርጫው ምንም እንኳን አወዛጋቢ እና ጉድለት የነበረበት እንዲሁም ለተቃዋሚዎች ትልቅ ስኬት ያስገኘ ቢሆንም፤ አጠቃላይ የዴሞክራሲ ሂደትን ቀውስ ውስጥ ከትቷል" ይላሉ።
ፕሮፌሰር አብኒክ የዲሞክራሲ ሂደቱን "ቀውስ ውስጥ ከቷል" ሲሉ ድኅረ ምርጫ የተስተዋለውን አፈና፣ አመጽ እና የመንግሥትን አምባገነናዊ (authoritarian) አገዛዝን በመጥቀስ ነው።
ፕሮፌሰሩ አክለውም "በ1997 ዓ.ም. የተካሄደው ምርጫ እና ያስከተለው ውጤት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ትልቅ ችግር እንዳለ አሳይቷል" ይላሉ።
"ከአፄ ኃይለሥላሴ እና ከወታደራዊው ሥርዓት በኋላ ማዕከላዊ አምባገነንነት (centralist authoritarianism) አልጠፋም፤ ነገር ግን ምናልባት በአዲስ መልክ እየተፈለሰፈ መሆኑን አሳይቷል" ሲሉ ያክላሉ።
ፕሮፌሰር አብኒክ ከኢህአዴግ ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ ከተካሄዱት ምርጫዎች ውስጥ የ97ቱ ምርጫ "እጅግ ወሳኝ እና ውጤታማ ምርጫ ነበር ማለት ይቻላል" ይላሉ።
"ሰዎች ለውጥ ሊኖር እንደሚችል ተሰምቷቸው ለብዙ ሰዓታት [በምርጫ ጣቢያዎች]ተሰልፈው ለመምረጥ ተዘጋጅተዋል" የሚሉት ፕሮፌሰሩ፤ "ይህ በራሱ ለአገሪቱ ዴሞክራሲ ትልቅ ትርፍ ነበር" ሲሉ ምርጫውን ይገልጹታል።
መጨረሻው በእንከኖች የተሞላ፣ የሰው ሕይወት የበላ እና የአገሪቱን የዴሞክራሲ ሂደት ወደ ኋላ የመለሰ ቢሆንም ምርጫ 97 ኢትዮጵያ እስካሁን መድገም ያልቻለችው ትልቅ ክስተት ነው።
የዴሞክራሲ ግንባታ ድክ ድክ፡ የምርጫ 97 መባቻ
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እና ጓዶቻቸው "ዴሞክራሲ በአንድ ጀምበር አይመጣም" የሚሉት ብሂል ነበራቸው። ከትግራይ በረሃዎች ተነስተው አራት ኪሎ ከገቡ በኋላ የማርክሲስት ካባቸውን አውልቀው አብዮታዊ ዴሞክራት ሆኑት እነ መለስ እውነት አላቸው።
ሥልጣን ከያዙ በኋላ የተካሄዱት ምርጫዎች ዴሞክራሲያዊም ፍትሃዊም ናቸው ለማለት ያስቸግራል።
ፕሮፌሰር አብኒክም በ1987 እና በ1992 በተካሄዱት ሁለት ምርጫዎች "ነጻ እና ፍትሃዊ' ምርጫ ሙሉ በሙሉ እውን ሊሆን አልቻለም" ይላል።
ነገር ግን ኢህአዴግ በ1997 ምርጫ መባቻ ለዴምክራሲያዊ የምርጫ ፉክክር መደላድሎችን መፍጠሩ አከራካሪ አይደለም።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ በፍቃዱ ኃይሉ "ከምርጫው በፊት በነበሩት አስር ዓመታት ገደማ የዴሞክራሲ ምኅዳሩ አንጻራዊ ስፋት እያሳየ የመጣበት ጊዜ ነበር" ሲል ከ1997 በፊት ያሉትን አስር ዓመታት ይገልጻቸዋል።
በእነዚህ አስር ዓመታት "ሚዲያዎች እያበቡ፤ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችም በነጻነት እየሠሩ ነበር" የሚለው በፍቃዱ "በርካታ ነጻ ጋዜጦች የተለያዩ ትችቶችን በነጻነት ያቀርቡ ነበር" ይላል።
ፕሮፌሰር አብኒክ "ከ1983 ዓ.ም. በኋላ ኢትዮጵያ ጉልህ የሆነ የፖለቲካ ተቋም ግንባታ እንደታየ እና ሕዝባዊ የዲሞክራሲ ሥርዓት መውጣቱ ምንም ጥርጥር የለውም" ይላሉ።
ከመገናኛ ብዙኃን እና ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች መነቃቃት በተጨማሪ ምርጫው ሲቃርብ "የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችም የተለያዩ ንቅናቄዎችን ለመመሥረት እየሞከሩ ነበር" ይላል በፍቃዱ።
ከ1997 በፊት በነበሩት ሁለት ምርጫዎች በጣም በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደነበሩ የሚያስታውሰው በፍቃዱ፤ የፓርቲዎች መብዛት "ተቃዋሚዎቹን የሚደግፉ ሰዎችን ድምጽ ስለሚከፋፍሉ ለገዢው [ፓርቲ] advantage ይሰጣሉ" ይላል።
በፍቃዱ አክሎም "ያኔ ግን በድንገት የተፈጠረው ቅንጅት ለአንድነት እና ለዴሞክራሲ እንዲሁም ደግሞ ሌላኛው አማራጭ የነበረው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ሕብረት ከኢህአዴግ አንጻር ቆሙ" ሲል ያስታውሳል።
ቅዳሜ ኢህአዴግ፣ እሁድ ቅንጅት... የምርጫ ዋዜማ
ሚያዝያ 29/1997 ዓ.ም. መስቀል አደባባይ ገዢው ፓርቲ የምርጫ መለያ የሆነው የንብ ምሥል የታተመበት ቲሸርት በለሰበሱ ሰልፈኞች ተሞልቷል።
የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ "ማዕበል" ሲሉ የጠሩት ሰልፍ የተካሄደው ለገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ድጋፍ ለማሳየት ነበር።
በማግስቱ ይህን የቅዳሜውን ሰልፍ የሚያስንቅ ሰልፍ በዚያው በመስቀል አደባባይ ተካሄደ። እሁድ ሚያዝያ 30/1997 ዓ.ም. የተካሄደውን ሰልፍ የጠራው ተቃዋሚው ቅንጅት ለአንድነት እና ለዴሞክራሲ ነበር።
ተቃዋሚው ፓርቲ የተደረገው የሚያዝያ 30ው ሰልፍ ላለፉት 20 ዓመታት አልተደገመም።
ኢህአዴግ እና ተቀዋሚዎች በተለይ ቅንጅት የሕዝቡን ልብ ለማሸነፍ ተፎካከሩት ግን በአደባባይ ብቻ አልነበረም። በቴሌቪዥን በተላለፉ የምርጫ ክርክሮች ጭምርም ነበር።
ፕሮፌሰር አብኒክ "በአንፃራዊነት ነፃ እና ግልጽ የሆነ ሕዝባዊ ውይይት በገዢው ፓርቲ እና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል እንዲሁም በገጠር ሰፊ ቅስቀሳ በማድረግ እስከዚያ ድረስ ታይቶ የማይታወቅ ተስፋ ተፈጥሯል" ይላሉ።
ገዢው ኢህአዴግ "ነጻ የሆነ ምርጫ አካሂጄ አሸንፋለሁ የሚል ስሜት ስለነበረው መድረኩን ክፍት አድርጎታል" የሚለው በፍቃዱ በበኩሉ "ተቃዋሚዎቹ በዚህ አጋጣሚ ተጠቅመው ብዙኃንን በተለይ የከተማ ነዋሪዎችን በከፍተኛ ሁኔታ አንቀሳቅሰዋል" ይህም ውጤት እንዳስገኘ ይናገራል።
በተጨማሪም "በቴሌቪዥን የሚደረጉ ክርክሮች የነበረው ዓውድ አጠቃላይ ዴሞክራሲን ተግባራዊ (exercise) እያደረግን ነበር ብለን እንድናምን የሚያደርጉ በርካታ ነገሮች ነበሩ" ሲል ያክላል።
ዶ/ር አባድር በበኩላቸው በምርጫ 97 ወቅት ኢህአዴግ "ዴሞክራታይዝ የማድረግ ፍላጎት ነበረው ወይም ሳይፈልግም ወደዚያ እየሄደ ነበር" ይላሉ። ይህ በበኩሉ ዴሞክራሲያዊ ወደሆነ የምርጫ ፉክክር አምርቷል።
ጅማሮው ላይ ዴሞክራሲያዊ የመሰለው ምርጫ 97 ግን አጨራረሱ አላማረም።
ፕ/ር አብኒክ ነጻ እና ግልጽ ሆኖ ጀመረ ያሉት ምርጫ "በድኅረ-ምርጫ ምዕራፍ ከፍተኛ አለመግባባት፣ ውዝግብ እና ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ላይ ከፍተኛ አፈና ተስተውሏል" ይላሉ።
"ቃዋሚ ፓርቲዎች አሸንፈናል ቢሉም ድል የተነፈጋቸው በማጭበርበር ነው" የሚሉት ፕ/ሩ በአከራካሪ የምርጫ ክልሎች አዲስ ምርጫ እንዲደረግ ያቀረቡት ጥያቄ ውድቅ ሲደረግ ሰላማዊ ሰልፍ ጠርተዋል ሲሉ ያስታውሳሉ።
ኢህአዴግ 371 ወንበሮች (ወይም 67.8 በመቶ ድምጽ)፣ ቅንጅት 109፤ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ሕብረት ደግሞ 52 በማሸነፍ ተቃዋሚዎች በድምሩ 174 የፓርላማ ወንበሮችን አግኝተው ነበር።
ጉዞ ወደ አምባገነናዊ አገዛዝ? የምርጫ ማግስት
የድምጽ ቆጠራው መደረግ ሲጀመር ተቃዋሚዎች ጥሩ አፈጻጸም የነበራቸው ይመስላል፣ ምርጫውን ያለጊዜው አሸንፈናል ማለታቸው ገዥው ፓርቲ ሁኔታውን ለማረጋጋት እና እንደገና ለመቆጣጠር እርምጃዎችን ወስዷል።
ይህን ተከትሎ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ላይ ወጥታ የነበረችው የዴሞክራሲ ጀምበር ለማዘቅዘቅ ወራት አልፈጀባትም። ፕሪፌሰር አብኒክ "የፖለቲካ ውዝግብ ተከተለ እና ተስፋ መቁረጥ በሕዝቡ አእምሮ ውስጥ ነገሰ" ይላሉ።
ከግንቦት 7 በኋላ ለአንድ ወር ያህል ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፎችን ማድረግ ታገደ። ተቃዋሚዎችን በክህደት የሚወንጅሉ የሚዲያ ዘመቻዎች ተጀመሩ። ጋዜጠኞች ታሰሩ።
የቅጣት ዘመቻ በሚመስል መልኩ በገጠር የገዥው ፓርቲ ፖለቲከኞች፣ ካድሬዎች እና ፖሊሶች ተቃዋሚ የሚሏቸውን ፖለቲከኞች ማዋከብ የጀመሩ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ታሰሩ።
"ግልፅ ባልሆነ ሁኔታ ቢያንስ አንድ የፓርላማ አባል ሆነው የተመረጡ ዕጩ በጥይት ተመተው መገደላቸውን" ፕ/ር አብኒክ አስፍረዋል።
ሰላማዊ ሰልፍ ማድርግ መከልከሉን ተከትሎ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በግቢ ውስጥ በመቀመጥ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
በአዲስ አበባ የሚገኙ የታክሲ አሽከርካሪዎች የሥራ ማቆም አድማ የጀመሩ ሲሆን በባሕር ዳር፣ በአዋሳ እና በአምቦ ከተሞችም የሚገኙ ተማሪዎችም ተቃውሞውን ተቀላቅለዋል።
ረቡዕ ሰኔ 1 ቀን 1997 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ የተካሄደው ሰልፍ እና መንግሥት የወሰደው እርምጃ በዴሞክራሲያዊ ክርክር የተጀመረውን ምርጫ በደም የቋጨ ነበር።
በከተማዋ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች እና ወጣቶች የጀመሩትን ሰልፍ መንግሥት "በማንኛውም መንገድ እንዲቆጣጠሩት" ትዕዛዝ መስጠቱን ተከትሎ የተቃውሞው ሰልፍ ወደ ቀውስ ተቀየረ።
የመንግሥት ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ በርካታ ሰዎች ሲገደሉ በመቶዎች የሚቀጠሩ ደግሞ ለእስር ተዳርገዋል።
ምርጫው "በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ እጅግ ፉክክር የታየበት ነገር ግን ውጥረት የበዛበት ወቅት ነበር" የሚሉት የሕግ ምሁሩ ዶ/ር አደም ካሴ፤ "በርዕዮተ ዓለምም ሆነ በሥልጣን ደረጃ የዜሮ ድምር ስሜት የተሰማበት ወቅትም ነበር" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ኢህዴግም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች "ፈረጃ ውስጥ ገቡ እንዲሁም ምርጫውን ሁሉንም ማሸነፍ ፈለጉ" ሲሉ ያክላሉ።
"ስለዚህ የማሸነፍ ወይም የመሸነፍ ዕድሉ ከፍተኛ ነበር። ይህም ከምርጫው ቀን በኋላ ለተፈጠረው ሁከት መነሻ ፈጥሯል" ሲሉ ውዝግቡን ተከትሎ የመጣውን ቀውስ ያብራራሉ።
ጦማሪው በፍቃዱ ኃይሉ በበኩሉ ድኅረ ምርጫን ተከትሎ የመጣው ሁከት እና ቀውስ፤ "የኢህአዴግ ድንጋጤ ውጤት ነው" ይላል። ኢህአዴግ ከምርጫው በኋላ ያሳየው ባህሪ "ፀረ ዴሞክራሲያዊ" መሆኑንም ያክላል።
"ከዚያ በኋላ በተቃዋሚዎች ላይ ያደረጉትን አፈና የሚያስተባብሉት ለሰላም ሲባል የተደረገ ነው ብለው ነው። ምንም ማስተባበያ ቢሰጡ እና ከዚያ በኋላ ሕዝቡን መቆጣጠር ቢችሉም በወቅቱ የተፈጠረባቸው ድንጋጤ እና ከሥልጣን ሊያወርዱን ነበር የሚለው እምነት በጣም አስደንግጧቸው ጭቆና ውስጥ ገቡ" ሲል ያብራራል።
ለዚህም በማሳያነት የሚጠቅሰው ከምርጫው ሦስት ዓመታት በኋላ በፓርላማው የወጡትን ሕጎች ነው።
"የፀረ ሽብር አዋጅ፣ ከውጭ ፈንድ እንዳይቀበሉ የሚያግደው እና ብዙ የአሠራር ማነቆዎችን ያደረገው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጀቶች አዋጅ እና የሚዲያ ሕጎች የሲቪክ ምኅዳሩን ፍጹም እየጠበበ አድርገውታል" ይላል።
ይሀን ተከትሎ "መጀመሪያ ያንን ምኅዳር እንዲሰፋ እና ለበሰለ የምርጫ ፉክክር ብቁ እንዲሆን ያደረጉትን ነገሮች በሙሉ ሚዲያው፣ ሲቪል ማኅበረሰቦች እንደሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች ራሱ ከዚያ በኋላ ተዳከሙ" ሲል ያክላል።
በፍቃዱ እንደሚለው "ከምርጫ 97 በኋላ ያሉት አመጾች ባይኖሩ ኖሩ መንግሥት እነዚያን ሕጎች ለማውጣት ሰበብ አያገኝም ነበር።" እንዲሁም "ከኢህአዴግ ድንጋጤ" በተጨማሪ ተቀዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የራሳቸው ድርሻ ነበራቸው።
"ተቃዋሚዎች በታሪክ ተገኝቶ የማይታወቅ ብዙ ድምጽ ቢያገኙም፤ በወቅቱ አሸንፈዋል የሚል እምነት የለኝም"፤ የሚለው በፍቃዱ "ሁሉንም ጠቅልሎ የመውሰድ አባዜ አለ እንጂ ሰጥቶ መቀብል የሚለው መርኅ የለም" ሲል ይተቻል።
ተቃዋሚዎችም "ይሄንን የሚያህል ትልቅ ወንበር ካገኘን በቂ ነው፤ ስለዚህ ከተቻለ አመጽ አልባ የሆኑ ትግሎችን መታገል ካልተቻል ግን ያለውን ወስደው ለሚቀጥለው ደግሞ አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት ከመሞከር [ይልቅ] እነሱ አደገኛ የሆነ መንገድ መርጠዋል" ይላል።
ፓርላማ መግባት የለብንም የሚለው የተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ውሳኔ "በጣም አደገኛ እና መዘዝ ያስከተለ" እንደነበርም ያስታውሳል።
እንደ ስለት ልጅ ያልተደገመው የምርጫ ሂደት
ዶ/ር አባድር ከ1997 በኋላ ኢህአዴግ "ፍጹም ወደሆነ አምባገነናዊ ሥርዓት ነው የገባው" ይላል። ለዚህ ማሳያ የሚሆኑት ከ1997 ተካሄዱት ምርጫዎች ናቸው።
ኢህአዴግ በ2002 የተካሄደውን ምርጨ 99.6 በመቶ ማሸነፉን በጊዜው አስታውቋል። ከዚያም በኋላ የተካሄደውን የ2007 ምርጫን ያሸነፈው ደግሞ 82.4 በመቶ ነበር።
ለበፍቃዱ ኃይሉ ኢህአዴግ በ2002 እና 2007 የተካሄዱትን ምርጫዎች በሰፊ ልዩነት ከማሸነፉ በላይ አስገራሚው ነገር ፓርቲው ያገኘው የመራጮች ድምጽም ብዙ መሆኑ ነው።
"የፓርላማ መቀመጫዎችን ማሸነፉ ብቻ አይደለም የሚያስደንቀው፤ ድምጹን ራሱ ቢቆጠር ከ90 ወይም 85 በመቶ በላይ ነው ኢህአዴግ እያገኘ የነበረው" ይላል።
"በማንኛውም ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የማይቻል ነው። አንድ ፓርቲ ከ80 በመቶ በላይ ድምጽ ሊያገኝ አይችልም" የሚለው በፍቃዱ፤ "51 በመቶ ድምጽ አግኝቶ ሁሉንም [የምክር ቤት] ወንበር ሊያሸንፍ ይችላል፤ በየምርጫ ጣቢያው በአንድም በሁለትም ድምጽ እየበለጠ ማለት ነው ግን ይሄ ድምጹ ራሱ ሰፊ ልዩነት ነው ያለው" ሲል ያስረዳል።
ይህ ሊሆን የቻለበት ምክንያት ሲያብራራም "ይህ የሚያሳየው ምንድን ነው፤ የተሳተፈውም የመረጠውም የገዢው ፓርቲ ደጋፊ ነው፤ አለበለዚያ ሌላው ተጨቁኗል አማራጭ እንዳይኖር ተደርጓል። ከዚያ ደግሞ መራጮች በብዙ መልኩ ተገዝተዋል" ይላል።
ከዚህ በተጨማሪም በእነዚህ ምርጫዎች "በዚያ ጊዜ እንዳየነው የተቃዋሚ ፓርቲዎች አሁን እንደምናየው ትንኮሳ ሳይደርስባቸው ደጋፊዎቻቸውን ማነቃነቅ አልቻሉም" ሲል ያክላል።
ከምርጫ 97 በፊት ኢህአዴግ "ዴሞክራታይዝ የማድረግ ፍላጎት ነበረው ወይም ሳይፈልግም ወደዚያ እየሄደ ነበር" የሚለው ዶ/ር አባድር ኢብራሂም፤ "ከ97 በኋላ ግን ዴሞክራሲ እንደማይሆነው ግልጽ የሆነ ውሳኔ ላይ ደርሷል" ሲል ከምርጫው በኋላ የተከሰተውን ዐበይት ለውጥ ያስታውሳል።
"ከዚያ በፊት ዴሞክራታይዝ እናደርጋለን፣ ከዚያ ምርጫ እናሸንፋለን ዓይነት ስሌት ነበር የነበራቸው። ከ97 በኋላ ግን ዴሞክራታይዝ የማድረግ ፍላጎት ጭራሽኑ አልነበራቸውም። ከ97 በኋላ ዴሞክራሲ አማራጭ አልነበረም" ሲልም ያክላል።
"[ኢህአዴግ] 99 በመቶ ያሸነፈው ድባቡ ስለተቀየረ ወይም ተቃዋሚዎች ስላልተሳተፉ አይደለም። 99 በመቶ ማሸነፍ ስለሚፈልግ ነበር። አንድም ፐርሰንት ለመልቀቅ ፍላጎት አልነበረውም። ልማታዊ የሆነ ግን ደግሞ ፈላጭ ቆራጭ የሆነ መንግሥት መገንባት ነበር ከ97 በኋላ ፍላጎታቸው" ሲል ድኅረ 97 የነበረውን የአገሪቱን ሥርዓተ መንግሥት እና ፖለቲካ ያስረዳል።
ዶ/ር አባድር ከ97 በኋላ ነበሩት ምርጫዎች ዴሞክራሲያዊ አለመሆናቸውን ያነሳል።
ለዚህ በአስረጂነት የሚጠቅሰው የምርጫው ሂደት ምን ያህል አሳታፊ እና ፉክክር የታየበት ነው የሚለውን በማንሳት ነው።
በ1997 የምርጫ ሂደት የታየው የተሳትፎ መጠን እንዲሁም የፉክክር ደረጃ ይህም ማለት ገዥው ፓርቲ ከተቃዋሚዎች ጋር ሲነጻጸር ያገኘው ድምጽም ለሂደቱ ዴሞክራሲያዊነት ማሳያ ይሆናል።
ከዚያ በኋላ በተካሄዱት ምርጫዎች ገዢው ፓርቲ የፉክክር ልኬቱ እና አሳታፊነት እጅግ አናሳ እንደነበር ዶ/ር አባድር ይገልጻል።
ባለፉት 20 ዓመታት ሊደገም ያልቻል የምርጫ ሂደት በመጪዎቹ ዓመታትም የመደገም ዕድሉ አጠራጣሪ ነው።
በፍቃዱ ኃይሉ "ቅድመ 97 የነበሩት የሲቪክ ምኅዳሩ እና የሚዲያ ምኅዳር በጥቅሉ አሁን የሉም፤ ስለዚህ በሚቀጥለው ምርጫ የ97ን የሚመስል ነገር እናያለን የሚል ተስፋ ጭራሽኑ የለኝም" ይላል።