ፓርላማው የአንድ የምክር ቤት አባልን ያለመከሰስ መብት ሊያነሳ ነው

የፎቶው ባለመብት, HOPR
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአንድ ምክር ቤት አባልን ያለመከሰስ መብት ሊያነሳ እንደሆነ አስታወቀ።
ፓርላማው ስማቸው ያልተገለጹ የምክር ቤት አባልን ያለመከሰስ መብት ዛሬ መጋቢት 25፣ 2015 ዓ.ም እንደሚያነሳ ይጠበቃልም ሲልም በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስማቸውን ያልገለጻቸው ግለሰብ በምን ምክንያት ያለመከሰስ መብታቸው ሊነሳ እንደሚችልም የሰጠው መረጃ የለም።
በዚህ 13ኛ መደበኛ ጉባኤው ከሁለት ሳምንታት በፊት በፍቃዳቸው ስራቸውን ለቀዋል የተባሉት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትላቸውን ተተኪ ሹመት ያጸድቃል።
የፌደራል ከፍተኛ ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ብርኃነ መስቀል ዋጋሪ እንዲሁም ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ተናኘ ጥላሁን በዚህ የኃላፊነት ቦታ ለባለፉት ሶስት ዓመት አገልግለዋል።
በዛሬው የምክር ቤቱ ውሎም የሁለቱን የኃላፊነት ቦታዎች የሚተኩ ዕጩዎችን ሹመት መርምሮ እንደሚያጸድቅም ይጠበቃል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለት ምክትል ፕሬዚዳንቶች ያሉት ሲሆን ሌላኛው በምክትልነት እያገለገሉ ያሉት አቶ ተኅሊት ይመስል ናቸው።
በተመሳሳይ መልኩ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት እና ምክትላቸው ከስራ መልቀቃቸውን ተከትሎ ከሁለት ወር በፊት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ ተተኪዎችን መሾሙ ይታወሳል።
ላለፉት አራት ዓመታት ያህል የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው ያገለገሉት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊንም በመተካት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግ ትምህርት ረዳት ፕሮፌሰር በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ተሹመዋል።
ምክር ቤቱ በጥር መደበኛ ስብሰባው በምክትልነት ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ሰለሞን አረዳንም እንዲተኩ ወይዘሮ እምቢአለን መሾሙ ይታወሳል።












