ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የእስራኤል ሴት ወታደሮች ከፍልስጤማዊ እስረኛ ጋር ወሲብ ፈፅመዋል በሚል ክስ ከጠባቂነታቸው ታገዱ
እስራኤላዊ ሴት ወታደሮች ከፍልስጤማዊ እስረኛ ጋር ወሲባዊ ግንኙነት ፈፅመዋል በሚል ክስ ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግለት እስር ቤት ጠባቂ ሆነው እንዳያገለግሉ ታገዱ።
የእስራኤል ሚዲያዎች እንደዘገቡት አንዲት ወታደር በእስራኤል ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት ከፈፀመው ፍልስጤማዊ እስረኛ ጋር አካላዊ ግንኙነት እንዳላቸው አምናለች።
ሌሎች አራት ሴቶችም ከዚሁ ግለሰብ ጋር የቅርብ ግንኙነት እንደነበራችው ተናግራለች።
ግለሰቧ የውትድርና አገልግሎት እየሰጠች እንደነበር ተገልጿል።
ለአብዛኛው እስራኤላውያን ወታደራዊ አገልግሎት መስጠት ግዴታ ነው።
በእስራኤል ሴቶች ቢያንስ ለሁለት ዓመት ወንዶች ደግሞ ለ32 ወራት ወታደራዊ አገልግሎት መስጠት ይጠበቅባቸዋል።
ድርጊቱ መፈጸሙን ያመነችው ወታደር እና የዕድሜ ልክ እስረኛው ስም አልተገለጸም።
ጉዳዩን እየተመለከተ ያለው ፍርድ ቤትም እስር ቤቱ የሚገኝበትን ቦታ ጨምሮ ሌሎች ዝርዝር መረጃዎች ይፋ መውጣት እንደሌለባቸው ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ፍልስጤማዊው እስረኛ ቃሉን እንዲሰጥ ከመጠየቁ በፊት ከነበረበት የእስረኛ ክፍል ወደ ሌላ ክፍል እንደተዛወረም የእስራኤል የእስር ቤት አገልግሎት (አይፒኤስ) ገልጿል።
ዐርብ ዕለት የአይፒኤስ ኃላፊ ካቲይ ፔሪ እና የደኅንነት ሚኒስትሩ ኢታማር ቤን ግቪር፣ ሴት ጠባቂዎች ከዚህ በኋላ ፍልስጤማውያን “ሽብርተኞችን” በያዙና ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግላቸው እስር ቤቶች እንደማያገለግሉ አስታውቀዋል።
የደኅንነት ሚኒስትሩን ኢታማር ቤን ግቪርን ጠቅሶ የእስራኤል ሚዲያ እንደዘገበው በአውሮፓውያኑ 2025 አጋማሽ "አንድም ሴት ወታደር ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግላቸው እስረኞች በሚገኙበት ክንፍ ውስጥ አትቆይም" ብለዋል።
ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግባቸው የእስራኤል እስር ቤቶች የሴት እስራኤላዊ ወታደሮች አገልግሎት እንዲታገድ በተደጋጋሚ ጥሪ ሲቀርብ ቆይቷል።
ሆኖም እነዚህን ሴት ወታደሮች በሚተካቸው የሰው ኃይል እጥረት ምክንያት ጥሪዎቹ ሳይተገበሩ ቆይተዋል።
ባለፈው ዓመት የእስራኤል ሚኒስትሮች ፍልስጤማውያን ፍርደኞች የእስር ቤቱ ጠባቂ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩ ሴት ወታደሮችን ላይ ጥቃት በማድረስና በመድፈር እንዲሁም አንዳንድ የእስር ቤት ከፍተኛ መኮንኖችም ወታደራዊ ግዳጁን "ጥሰዋል" በሚል በአንድ እስር ቤት ውስጥ ምርመራ እንዲካሄድ ትዕዛዝ ሰጥተው እንደነበር ይታወሳል።