ፒኤስጂ በሊዮኔል ሜሲ ግብ ታግዞ የፈረንሳይ የሊግ 1 ዋንጫን አነሳ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሊዮኔል ሜሲ ሌላ ክብረ ወሰን የሰበረች ግብ አስቆጥሮ ክለቡ ፒኤስጂ 11ኛ የፈረንሳይ ሊግ 1 ዋንጫ እንዲያነሳ አስችሏል።
በ59ኛው ደቂቃ ሜሲ፤ ኪሊያን ምባፔ ያሻገረለትን ኳስ ከመረብ በማሳረፍ ክለቡን አቻ አድርጓል።
ጨዋታው አንድ አቻ መጠናቀቁን ተከትሎ ፒኤስጂ የዘንድሮው ሊግ 1 ዋንጫ አሸናፊ ሆኗል።
ሜሲ ያስቆጠራት ግብ በአውሮፓ 496ኛው ስትሆን፣ በአንድ ጎል ከክሪስትያኖ ልቆ ክብረ ወሰን ይዟል።
ሜሲ ቅዳሜ ምሽት ያስቆጠራት ግብ ለፒኤስጂ 32ኛዋ እና ምናልባትም በሚመጣው ክረምት ክለቡን የሚለቅ ከሆነ የመጨረሻዋ ትሆናለች።
የጨዋታው የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች አሰልቺ ነበር። ምክንያቱ ደግሞ ፒኤስጂ ዋንጫውን መብላቱን ማወቁ እና ለተጋጣሚው ስትራስቦርግ አቻ ውጤት በቂ መሆኑ ናቸው።
ምንም እንኳ ክለቡ ዋንጫ ቢያነሳም አሠልጣኝ ክሪስቶፈር ጋልቲዬ ከፒኤስጂ ጋር የመቆየታቸው ነገር አጠራጣሪ ሆኗል።
በፈረንጆቹ 2021 ሊል የተሰኘውን ክለብ ለዋንጫ ያበቁት አሠልጣኝ ዘንድሮ ከቻምፒዮንስ ሊግ መሰናበታቸው የክለቡን ኃላፊዎች አስከፍቷል።
ፒኤስጂ፤ ሴይንት-ኢቲየን እና ማርሴ ከዚህ ቀደም የያዙትን የ10 ዋንጫዎች ክብረ ወሰን አልፎት ሄዷል።
ባለፈው ግንቦት ከደጋፊዎች ጋር ቅራኔ ውስጥ ገብቶ የነበረው ሜሲ የፒኤስጂ ምዕራፉን በጎል ያጠናቀቀ ይመስላል።
የሜሲ ዘጋቢ ፊልም
ቢቢሲ ያሰናዳው አዲስ ዘጋቢ ፊልም ታላቁ ሜሲ እንዴት በስተመጨረሻ የዓለም ዋንጫን ሊያነሳ እንደቻለ ይተርካል።
ከአራት ያልተሳኩ ሙከራዎች በኋላ ሜሲ አገሩ አርጀንቲናን እየመራ የካታሩን ዓለም ዋንጫ በድል ተወጥቷል።
አንድ ሰዓት በሚፈጀው ፊልም፤ ኤሚሊያኖ ማርቲኔዝ፣ አሌክሲስ ማክ አሊስተር፣ ጁሊያን አልቫሬዝ እና አሠልጣኙ ሊዮኔል ስካሎኒ ተካተውበታል።
አርጀንቲና ከዓለም ዋንጫው ቀድሞ 36 ጨዋታዎች አለመሸነፏ ለዋንጫው እንድትገመት አድርጓት ነበር።
ነገር ግን በመጀመሪያው ጨዋታ በሳዑዲ አረቢያ መረታቷ የአርጀንቲና ተጫዋቾችን ያስደነገጠ እንደነበር ማርቲኔዝ ለቢቢሲ ይናገራል።
ስካሎኒ ተጫዋቾቹ አገራቸው ያሉ እንዲመስላቸው ብዙ እንደጣረ ዘጋቢ ፊልሙ ያሳያል።
በወቅቱ ተዘግቦ እንደነበረው ስካሎኒ 900 ኪሎ ግራም ሥጋ ከደቡብ አሜሪካ ወደ ኳታር አስመጥቷል።
“ሁሉም ነገር ደስ ይል ነበር። አገራችን ያለን ነበር የሚመስለው። ካርታ እየተጫወተ፤ ትኩስ ነገር እየጠጣን ነበር. . . የአርጀንቲና ሥጋ ሁላ ስንበላ ነበር” ይላል አሌክሲስ ማክ አሊስተር።
ሜሲ ከኔዘርላንድስ ጋር በነበረው ጨዋታው ስላሳየው ጠባይ፤ ከቫን ሃል ጋር ስለነበረው አለመግባባት ስለማርቲኔዝ የፍፁም ቅጣት ምት ስልት፤ በዘጋቢ ፊልሙ ተካተዋል።












