በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የትንሹ ስታድየም ባለቤት የሚሆነው ሉተን ታውን ወደ ሊጉ አደገ

የፎቶው ባለመብት, Rex Features
ሉተን ታውን የተሰኘው ክለብ ከታችኛው ምድብ የእግር ኳስ ውድድር ተነስቶ ወደ እንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የገባ የመጀመሪያው ቡድን ሆነ።
ሉተን ታውን ቅዳሜ ምሽት ኮቨንትሪን በፍፁም ቅጣት ምት 6 ለ 5 በመርታት ታሪክ ፅፏል።
ጆርዳን ክላርክ በመጀመሪያው አጋማሽ አክርሮ የመታት ኳስ ሉተን ታውንን መሪ ብታደርግም፣ ጉስታቮ ሃመር ኮቨንትሪን አቻ ማድረግ ችሎ ነበር።
ጨዋታው ለ120 ደቂቃ አንድ አቻ በመዝለቁ ለሁለቱ ክለቦች ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ሊያመሩ ግድ ሆኗል።
በፍፁም ቅጣት መለያው የኮቨንትሪው ፋንካቲ ዳቦ በግራ እግሩ ኳሷን ወደ ሰማይ በመስቀሉ ሉተን ታውን ባለድል ሆኗል።
ሉተን ታውን ለመጨረሻ ጊዜ በፕሪሚዬር ሊጉ የተጫወተው ሊጉ በተቋቋመበት ዓመት [1992 በፈረንጆቹ] ነበር።
ከ31 ዓመታት በኋላ ወደ ሊጉ የተመለሱት ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ‘ነን-ሊግ’ በሚባለው ውድድር ውስጥ ቆይተው ነው።
አሠልጣኝ ሮብ ኤድዋርድስ ባለፈው ዓመት ፎረስት ግሪን የተሰኘውን ክለብ ወደ ሊግ 2 ማሳደጉ ይታወሳል።
አሁን ደግሞ ሉተን ታውንን ይዞ ወደ ተወዳጁ እንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ መጥቷል።
ኤድዋርድስ ፎረስት ግሪንን ከለቀቀ በኋላ የሉተን ታውን ዋነኛ ተቀናቃኝ የሆነው ዋትፈርድ አሠልጣኝ ሆኖ ተቀጥሮ ባለፈው መስከረም ነው የተባረረው።
የቤድፈርሻየር ክለብ የሆነው ሉተን ታውን ስታድየም የፕሪሚዬር ሊግ ደረጃን የሚመጥን ስላለሆነ መታደስ አለበት።
ይህን የዕደሳ ሥራ ለመሥራት ክለቡ 10 ሚሊዮን ፓውንድ ወጪ ማድረግ አለበት።
ሉተን ታውን ሚሊዮኖች ወጪ አድርገው መቀመጫቸው ሊጉን እንዲመጥን ማድረግ ቢችሉ እንኳ ስታድየሙ በፕሪሚዬር ሊጉ ትንሹ ከመሆን አይድንም።
የሉተን ታውን ስታድየም አሁን ማስተናገድ የሚችለው ከ10 ሺህ ትንሽ ከፍ ያለ የተመልካች ቁጥርን ነው።
ፔሊ-ሩዶክ ምፓንዙ
የሉተን ታውን አማካይ ፔሊ-ሩዶክ ምፓንዙ ‘ከነን ሊግ’ እስከ ፕሪሚዬር ሊግ ከአንድ ክለብ ጋር የመጣ የመጀመሪያው ተጫዋች ሆኗል።
በ2013 ክለቡን ሲቀላቀል 19 ዓመቱ ነበር። በወቅቱ ሉተን ከእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ አምስት ደረጃ ዝቅ ብሎ ነበር የሚገኘው።
እነሆ አሁን ከ10 ዓመታት በኋላ የ29 ዓመቱ አማካይ ከእናት ክለቡ ጋር ወደ ትልቁ ሊግ ተሸጋግሯል።
ሉተን ታውን ከኮቨንትሪ ከመጫወቱ በፊት በትዊተር ገጹ ላይ “ይህ ሰው ታሪክ ሊሠራ 90 ደቂቃ ይቀሩታል” ብለው ለጥፈው ነበር።
ተጨዋቹ በክለቡ ደጋፊዎች ዘንድ እንደ ክለቡ የጀርባ አጥንት እና ባለውለታ ነው የሚታየው።
ሉተን ታውኖች ወደ በ2024 አሊያም 25 ወደ አዲሱ ስታድየማቸው ከማቅናታቸው በፊት እንደ ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ሲቲ እና አርሰናል ወደ ትንሿ ስታድየም መጥተው የምፓንዙን ክለብ መግጠም ይኖርባቸዋል።












