ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የዋስትና መብት ታገደ
የፍትሕ መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር የሆነው የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የዋስትና መብት በፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ታገደ።
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ሰኞ ሰኔ 27/ 2014 ዓ.ም. በ100 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲለቀቅ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወስኖ ነበር።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ይህን ውሳኔ ከሰጠ በኋላ የጋዜጠኛው ቤተሰቦች የተጠየቀውን የዋስትና ገንዘብ ቢያስይዙም ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከእስር ሳይለቀቅ ለአራት ቀናት ቆይቷል።
የጋዜጠኛው ጠበቃ ሄኖክ አክሊሉ ዐቃቤ ሕግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በዋስትና ሊፈታ አይገባም በሚል አቤቱታ ካቀረበ በኋላ የፈዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠው የዋስትና መብት መታገዱን ለቢቢሲ አስረድተዋል።
ዛሬ ሐሙስ ሰኔ 30/2014 ዓ.ም. ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ለምን ከእስር እንዳልተለቀቀ ለማስረዳት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተገኝቶ እንደነበረ ጠበቃ ሄኖክ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንም ጋዜጠኛው በዋስ ያልተለቀቀው ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዋስትና መብቱን በማገዱ እንደሆነ ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማስረዳቱን ጠበቃው ጨምረው አስረድተዋል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዐቃቤ ሕግ የይግባኝ መከራከሪያዎችን ለማድመጥ ለሐምሌ 07/2014 ዓ.ም. ቀጠሮ መስጠቱን ጠበቃ ሄኖክ ተናግረዋል።
ዐቃቤ ሕግ፤ በእስር ላይ በሚገኘው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ ወታደራዊ ምስጢሮችን ለሕዝብ ይፋ በማድረግ፣ ሐሰተኛ የሆኑ ወታደራዊ መረጃዎችን በማውጣት፣ ለአመጽ ሕዝብን በማነሳሳት የሚሉ ክሶችን አቅርቦበታል።
በሦስቱም ክሶች ላይ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በሚሰራበት ሚዲያ ላይ በመጻፍ እነዚህን የወንጀል ተግባሮች ፈፅሟል የሚልም ወደ ሰባት የሚሆኑ የፍትሕ መፅሔት ዕትሞች በማስረጃነት መቅረባቸውን ጠበቃው ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ግንቦት 18/2014 ዓ.ም. ከሥራ ቦታው በፀጥታ ኃይሎች ተይዞ ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መወሰዱ ይታወሳል።
ተመስገን በጋዜጣና በመፅሔት ባለቤትነትና ዋና አዘጋጅነት በቆየባቸው ጊዜያት መንግሥትን በሚተቹ ጽሁፎቹ ይታወቃል።
በተደጋጋሚ ጊዜያትም የህትመት ሥራዎቹ እንዲቋረጡ ከመደረጋቸው በተጨማሪ፣ ለበርካታ ጊዜያት ለእስር መዳረጉ ይታወሳል።
ተመስገን ደሳለኝ ከአራት ዓመት በፊት ለረጅም ጊዜ በአስር ላይ ቆይቶ ከተፈታ በኋላ፣ ተቋርጣ የነበረችውን ፍትሕ መጽሔትን መልሶ በመጀመር በየሳምንቱ ለንባብ እየበቃች ትገኛለች።