ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አንድ ሙሽሪት፣ ሁለት ባሎች፡ በሕንድ ውዝግብ የፈጠረው ጋብቻ
በሕንድ ሂማሊያ በተሰኘች አነስተኛ መንደር አንድ ሙሽሪት ከሁለት ወንዶች መካከል ተቀምጣለች።
በባህላዊ ልብስ የደመቀችው ሙሽሪት እና ሁለቱ ወንዶች ሙሽሮች በፎቶው ላይ ፈገግ ብለው ይታያሉ።
ይህ የተለመደ የሰርግ ፎቶ አይደለም።
ሱኒታ ሲ ወንድማማቾቹ ካፒል ኤን እና ፕራዲፕ ኤን ጋር የተሞሸረችበት የሰርግ ፎቶ ነው።
በሕንድ ከአንድ በላይ ባል (ፖሊያንድሪ) ወይም ከአንድ በላይ ሚስት (ፖሊጋሚ) በሕግ የተከለከለ ነው።
ከሁለት ወንድማማቾች ጋር በሐምሌ ወር የተደረገው የዚህች ሴት የጋብቻ ፎቶ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት ተጋርቷል።
በርካቶች ቤተሰቡን በስድብ ከመወረፋቸውም በተጨማሪ በአገሪቱ ብሔራዊ ክርክሮች መነሻ መሆኑ አልቀረም።
ሦስቱ ተጋቢዎች ጊሪ እና ቶን በተሰኙ ወንዞች ተፋሰስ በሚገኙ ሂማቻል ፕራዴሽ እና ኡትራካሃንድ የሚኖሩ ቀደምት የሚባሉት የሃቲ ጎሳ አባላት ናቸው።
300 ሺህ የሚጠጋ ሕዝብ ያለው የዚህ ማኅበረሰብ አባላት በክልሉ በሚገኙ 400 መንደሮች ውስጥ ይኖራሉ።
ሃቲ የሚለውን ስያሜያቸውን ያገኙት አትክልት እና ሱፍ "ሃትስ" በተሰኘ ገበያ ለዘመናት ከመገበያየታቸው ጋር የተያያዘ ነው።
ማኅበረሰቡ የሱፍ ሻርፖችን በመሸመን እንዲሁም የብር ጌጣጌጦችን በመሥራት ዕውቅናን አትርፏል።
ሕንድ ከ700 በላይ ለሆኑ ጎሳዎች በይፋ ዕውቅናን የሰጠች ሲሆን፣ እነዚህም የአገሪቱን ሕዝብ 8.6 በመቶ የሚወክሉ ናቸው።
ከሁለት ዓመታት በፊት የሕንድ መንግሥት ለሃቲ ማኅበረሰብ "ውስን በሆነ መልኩ የጎሳነት" እውቅና (scheduled tribe) ሰጥቷቸዋል።
በዚህም ከአገሪቱ የማኅበራዊ ደኅንነት መርሃ ግብሮች እንዲሁም በሥራ እና በትምህርት ተቋማት የተቀመጡ ኮታዎች ተጠቃሚ ሆነዋል።
ማኅበረሰቡ በእምነታቸው ሂንዱዎች ተብለው ቢከፈሉም የጋብቻ ባህላቸው ከሂንዱ ሥነ ሥርዓቶች የሚለይ ነው።
በአካባቢው "ጆዲዳራ" ወይም "ጃጃዳ" በመባል የሚታወቁት እነዚህ የሰርግ ሥነ ሥርዓቶች ሙሽሮች ፊት ለፊት እየተያዩ መሃላ የሚለዋወጡባቸው ናቸው።
በሂንዱ የባህል ጋብቻ ሥነ ሥርዓት ግን የተቀደሰ እሳት በሚባለው ሙሽሮች ሰባት ዙር መሽከርከር ይገባቸዋል።
ሌላኛው የማኅበረሰቡን የሰርግ ሥርዓት ከሂንዱ የሚለየው ሙሽሪት ናት የጋብቻውን ሂደት በመምራት ወደ ሙሽራው ቤት የምታቀናው።
"በጥንት ጊዜ አንደኛው ወንድም ከብቶቹን ለማገድ ለወራት ወደ ሌላ ስፍራ ሲሄድ ሌላኛው ወንድም ከሙሽሪት ጋር ይቆያል። የሄደው ሲመለስም በየተራ አብረዋት መኖር ይጀምራሉ" ይላል ከሃቲ ማኅበረሰብ የተወለደው ሼር ጁንግ ቻውሃን የተሰኘ ጋዜጠኛ።
"ልጆች በየትኛው አባት ይጠራል የሚሉ ውሳኔ አሁንም የሚወሰነው በቤተሰቡ መካከል በሚደረግ ስምምነት ነው" ሲልም አክሏል።
በከፋ የከባቢ ሁኔታ የተቀረጸው ባህል
ሃቲዎች የሂንዱይዝምን እምነት፤ እንስሳት፣ ዕጽዋት፣ ወንዞች ወይም ማንኛውም ተፈጥሯዊ ነገሮች መንፈሳዊ ማንነት አላቸው ከሚለው ከአኒሚዝም ጋር አዋሂደው ይከተላሉ።
አማልክቶችም በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ውስጥ ማዕከላዊ ሚና ይጫወታሉ።
በተረቶቻቸውም የማኅበረሰባቸውን አመጣጥ ከትውልድ ወደ ትውልድ ያስቀጥላሉ።
በእጅ የተሸመነ የሱፍ ባህላዊ ልብሳቸው ለማንነታቸው ድምቀትን ያላብሳል።
በጋራ የቤተሰብ ምሥረታ አንድነትን እንዲሁም ሃብት መጋራትን ያጠናክራል ይላሉ።
ወንድማማቾች የመሬት ይዞታቸው እንዳይከፋፈል አንድ ሚስት በጋራ እንዲያገቡ ይበረታታሉ።
በስፍራው ያለው ለም መሬት በጣም አናሳ ነው።
በተጨማሪም ውርስ በወንድሞች መካከል መከፋፈል የቤተሰቡን ሃብት ሊቀንሰው ይችላል ይላሉ።
የሕንድ ሕገ መንግሥት በተለየ መንገድ በመንግሥት ካልተከለከለ በስተቀር እንደ ሃቲ ያሉ ጎሳዎች ልምድና ባህላቸውን እንዲያስጠብቁ ይፈቅዳል።
የሂማቻል ፕራዴሽ የመጀመሪያ አስተዳዳሪ እንዲሁም ምሁር የሆኑት ያሽዋንት ሲንግ ፓርማር "ሴቶች ከአንድ በላይ ባል የማግባት ባህል የመጣው በተራራማው ስፍራ ካለው የከፋ የከባቢ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ውስን የሆነውን የመሬት ሃብት ለመጠበቅ ነው" ሲሉ 'ፖሊያንድሪ ኢን ዘ ሂማሊያስ' በተሰኘ መጽሐፋቸው አስፍረዋል።
ነገር ግን እንደነዚህ ዓይነት ጋብቻዎች በዘመናችን እየቀሩ መጥተዋል።
በአካባቢው ከትምህርት መስፋፋት፣ ከኢኮኖሚ ልማት እና ከዘመናዊነት ተጽእኖ ጋር ተያይዞ ከአንድ በላይ ባል ማግባት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
በአካባቢው ነዋሪ የሆነው ካፒል ቻውሃን በክልሉ ውስጥ ባሉ እያንዳንዱ መንደሮች ቢያንስ ከአራት እስከ ስድስት የሚሆኑ ቤተሰቦች ፖሊያንድሪን ተግባራዊ ያደርጋሉ ይላል።
"የማንነታችን መገለጫ እንዲሁም ኩራታችን ነው። ከአንድ በላይ ባል ያገቡ ቤተሰቦች እስከ ተስማማቸው ድረስ ለሌላው ሰው ችግር ሊሆንበት አይገባም" ሲል ለቢቢሲ ያስረዳል።
የአካባቢው የማኅበራዊ ተሟጋች የሆኑት ራሜሽ ሲንግታ በበኩላቸው "በአሁኑ ወቅት እንዲህ አይነት ትዳሮች ሰው ሳይሰማ በዝምታ ነው የሚፈጸሙት" ይላሉ።
ምርጫ ወይስ ብዝበዛ?
በመንደሪቷ አንዲት ሴት ሁለት ባሎች ማግባቷ በሕንድ ውስጥ በሰፊው የማኅበራዊ ሚዲያ ክርክር አስነስቷል።
ምንም እንኳን በርካቶች ከመፈቃቀድ እና ከግል ምርጫ ጋር የተያያዘ ነው ቢሉም አንዶች ግን የሴቶችን መብት የሚጋፋ ነው ብለው ይከራከራሉ።
ደጋፊዎች የመሬት እና የቤተሰብን አንድነት በማስተሳሰር ባህላዊ ሁኔታዎችን በማስቀጠል አሞካሽተዋል።
ይህንን የሚተቹ ደግሞ ባህሉ በዘመኑ ያለውን ጠቀሜታ፣ ሕጋዊ ሁኔታ እንዲሁም የሥርዓተ ፆታን ከግምት ውስጥ ያላስገባ ያረጀ ያፈጀ ነው ይላሉ።
ሌሎች ደግሞ የአንዲት ሴትን ከአንድ በላይ ባል ማግባት (ፖሊያንድሪን) ተቀብሎ ከአንድ በላይ ሚስት (ፖሊጋሚን) መኮነን ግብዝነት ነው ይላሉ።
ቤተሰቡ በበኩሉ ምርጫቸውን ደግፈው ደስታን የሚሰጣቸው እና ባህላቸው መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
የአካባቢው ፖለቲከኛ እና የኢንዱስትሪዎች ሚኒስትር ሃርሽዋርድ ቻውሃን "ይህንን ልምድ በማስቀጠል ፕራዲፕ እና ካፒል ባህላችንን አክብረዋል" ሲሉ ተናግረዋል።
አንዳንዶች በበኩላቸው ሴቷ በቤት ውስጥ የሚኖርባትን ጫና በመጥቀስ ሁኔታውን የከፋ ሊያደርገው ይችላል ሲሉ ይከራከራሉ።
"ይህ ባህል የሴቶችን ብዝበዛ የሚያበረታታ እና መሠረታዊ መብቶቻቸውን የሚጥሰ ነው" ሲሉ የመላው ሕንድ ዲሞክራቲክ ሴቶች ማኅበር ዋና ፀሐፊ ማርያም ድዋሌ ያስረዳሉ።
ሁለት ባሎች ማግባት ማለት ሴቷ በርካታ ልጆች እንድትወልድ ተጨማሪ ጫና ሊፈጥርባት እንደሚችል ማርያም ይናገራሉ።
ሆኖም አሻ ዴቪ በዚህ "ጆዲዳራ" በተሰኘው ከአንድ በላይ ባል ያገባች ሴት ባህሉ የሴትን ነጻነት እንደማይጋፋ ትናገራለች።
"ከሚታሰበው የተሳሳቱ አመለካከቶች በተቃራኒ ሴቶች እንዲህ ዓይነት ጋብቻን አለመቀበልም ሆነ ትተው የመውጣት መብት አላቸው። ሴቶችም ሆኑ ወንዶች በዚህ ጋብቻ አይገደዱም" ስትል አሻ ታስረዳለች።
ከሰሞኑ የተጋቡት ሦስቱ ጥንዶች ሙሉ ለሙሉ ባህላዊ ሕይወትን አይመሩም።
ሙሽራዋ ሱኒታ በኢንዱስትሪ ማሠልጠኛ ተቋም ትምህርቷን የተከታታለች ቴክኒሻን ናት። አንደኛው ባሏ ፕራዲፕ የመንግሥት ሠራተኛ ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ በመስተንግዶ ዘርፍ የተሰማራ ነው።
ሙሽራዋ ሱኒታ ወደዚህ ጋብቻ የገባችው በፍቃዷ መሆኗን ለጋዜጠኞች ተናግራለች።
"የራሴ ውሳኔ ነው። ዘመናትን ያስቆጠረውን የጥንት ወግ ተቀብያለሁ" ብላለች።
ባሎቿም እንደሷ ተመሳሳይ አስተያየት አላቸው።
"ያለን ግንኙነት በባህል ላይ ያለንን እምነት እንዲሁም እርሰ በርስ ለመተሳሳብ የጣልነውን የጋራ ኃላፊነት የሚያሳይ ነው" ሲል ፕራዲፕ ለሕንድ መገናኛ ብዙኃን ተናግሯል።
ሦስቱም በፍቅር ለመኖር እና ኅብረታቸውን ለማጠናከር ቃል ገብተዋል።
ፖሊያንድሪ በሌሎች ባህሎች
አንዲት ሴት ከአንድ በላይ ባል ማግባት ወይም ፖሊያንድሪ ብዙም ያልተለመደ ቢሆንም፤ በሂማልያ የሚኖሩት እንደ ኪናኡሪስ እንዲሁም በደቡብ ሕንድ ቶዳስ በተሰኙት ጎሳዎች አሁንም ተግባራዊ ይደረጋል።
በሌሎችም እንዲህ ዓይነት ተመሳሳይ ባህሎች ያሉ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ በቻይና ሞሱአ ማኅበረሰብ የሚደረገው "ዋኪንግ ሜሪጅ" አንዱ ነው። በዚህም ወንዶች በምሽት ሴቶችን የሚጎበኙበት እና በቀን ደግሞ ከሌላኛዋ የትዳር አጋራቸው ጋር የሚኖሩበት ነው።
በቲቤት፣ በናይጄሪያ ኢሪግዌ ማኅበረሰብ እና በአማዞን ጎሳ ቦሮሮ በተመሳሳይ መልኩ ሴቶች ከአንድ በላይ ባል የማግባት ባህል አላቸው።
በተጨማሪም በምሥራቅ አፍሪካ በማሳይ ማኅበረሰብ ዘንድ ተመሳሳይ ባህል እንዳለ የተመዘገበ ቢሆንም ይህ ባህል ግን በሕግ ተከልክሏል ወይም በዘመናት ሂደት እየጠፋ ነው።