ጦርነት እና ግጭት የኢትዮጵያውያንን ማኅበራዊ ትስስር እየበጣጠሱት ይሆን?

የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በቀደም’ለታ እንዲህ አሉ።

“በኢትዮጵያ ነገሩ ሁሉ ከቁጥጥር ውጪ እየወጣ ነው፤ የኢትዮጵያውያን ማኅበራዊ ድራቸው እየተበጣጠሰ ነው።”

የዋና ፀሐፊው ድምዳሜ ያስፈራል። ያስደነግጣል።

የዲፕሎማት ቋንቋም አይመስልም። አልተሽሞነሞነም።

ጉቴሬዝ ምን ቢታያቸው ነው እንዲያ ያሉት?

ሐሳባቸውን ከተፈለቀቀ ሰውዬው እያሉ ያሉት እኮ፤ ‘ኢትዮጵያውያን የሚያስተሳስራቸው ማኅበራዊ ድር እንደ ሹራብ ክር እየተተረተረ ይገኛል ነው።’

የጉቴሬዝ ድምዳሜ እንዴት በዋዛ ታለፈ? ወይስ እኛ ለዘመናት ስንፈራው የነበረን ሐቅ ነው በአንድ ‘ትዊት’ ያፈረጡት?

ለነገሩ የጉቴሬዝ ምልከታ በዋዛ አልታለፈም።

ከአራት ቀናት በኋላ በተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ዲፕሎማት አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ ምላሽ ሰጡ።

የኢትዮጵያውያን የአብሮነት ድር እየተተረተረ ነው የሚለው “ያልተጨበጠ ወሬ ነው” ብለው አጣጣሉ።

“…ትስስራችን በጥብቅ መሠረት ላይ በመሆኑ ነው ከዘንድሮው በከፋ ጊዜ እንኳ ያልተበታተነው። ለምዕተ ዓመታት አብረን የዘለቅነው” ብለው ጻፉ፤ በትዊተር ሰሌዳቸው።

በእርግጥ ኢትዮጵያውያን ቁርኝታችን በጠንካራ መሠረት ላይ ነው? ስፌታችን ስውር ነው? ትስስራችን ጥብቅ ነው? ወይስ በተቃራኒው የላይ ላይታ ቅብ ነው?

እንደ ኢትዮጵያውያን የተጋመደ ሕዝብ በምድር ላይ የለም ከሚሉት ጀምሮ ‘ስናስመስል ነው’ እስከሚሉት ድረስ ለዚህ ጽሑፍ አወያይተናል።

የዲፕሎማቶቹን የዲፕሎማሲ እንካ ሰላንቲያ ለጊዜው ከተንደረደርንበት ይበቃል።

ወደ መሬት ወርደን ነገሩን አንፈትሽም።

“ፖለቲካ የሚፈላባቸው ስታርባክሶች”

ኢብራሒም ባዘዘው (ስሙ እንዲቀየር የጠየቀ) በአሜሪካ ኔቫዳ ግዛት፣ ላስቬጋስ ከተማ ከከተመ እንደ ቀልድ ስምንት ዓመት አለፈው።

እርሱ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ትኩሳት የሚለካባቸው የራሱ ቴርሞሜትሮች አሉት፤ ስታርባክሶች።

“ስታርባክስ ለሐበሻ ካፌ ብቻ አይደለም” ይላል፤ ኢብራሒም።

ማራቶን ሯጭ ውሃ ከጎዳና ቀልቦ ሩጫውን እንደሚቀጥለው፣ ፈረንጆች ቡናቸውን ከባሬስታው እጅ መንትፈው ይሮጣሉ። ወደ ሥራ።

ራሳቸውን ‘ሐበሻ’ በሚል የወል ስም መጥራት የሚመርጡት ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ግን እንዲያ አይደሉም።

“ለኛማ ስታርባክሶች ሁነኛ የፖለቲካ ከባቢዎች (Political space) ናቸው” ይላል፤ ኢብራሒም።

ምን ማለቱ ነው?

በአስቆማሪዋ ከተማ ላስቬጋስ የአገር ቤት ፖለቲካ የሚቆመረው በስታርባክስ ነው።

የብሔር ፖለቲካ ተቦክቶ የሚጋገረው፣ ፈልቶ የሚቀዘቅዘው እዚያው ስታርባክስ ነው።

ኢብራሒምም ከጦርነቱ ወዲህ በእነዚህ ስታርባክሶች ውስጥ አንድ አዲስ ነገር አስተዋለ።

ወትሮ የሚያውቃቸውን ካፌዎች ዐይኑን ገልጦ፣ ልቡን ከፍቶ ቢመለከታቸው ጊዜ አዲስ የፖለቲካ አሰላለፍ ፍንትው ብሎ ታየው።

“የሚገርምህ ትሮፒካናና ዲኬተር ላይ የሚገኘው ስታርባክስ ከጦርነቱ በፊት ማንንም ታገኝበት ነበር። ኤርትራዊው፣ ደቡቡ፣ ጎጃሜው፣ ኦሮሞው ሁሉም እየተጫጯኸ ቡና የሚጠጣበት ቦታ ነበር።”

ከጦርነቱ ወዲህ ግን ይህ መልኩን ቀየረ።

“አሁን ሦስቱ ስታርባክሶች ሦስት የፖለቲካ አሰላለፎችን ይዘው ታገኛለህ…” ይላል ኢብራሒም።

“ለምሳሌ ሂድ፣ ዌስት ትሮፒካና 4985 ጎዳና፤ ተጋሩዎች በብዛት ታገኛለህ። ሂድ 4507 ጎዳና፣ ዌስት ፍላሚንጎ፤ ኤርትራውያን በብዛት ታገኛለህ። ሂድ ወደ 4110 ሳውዝ ሬንቦ ጎዳና፤ የተቀረውን ሐበሻ ታገኛለህ።”

ኢብራሒም ይህን ድንገተኛ አዲስ አሰላለፍ ማስተዋል የጀመረው ከሰሜኑ ጦርነት መፋፋም ማግስት ነው።

በሚገርም ፍጥነት ነው ነገሮች የተቀያየሩት ይላል።

“ገባህ? በፊት በቃ በመልክ ሐበሻ ስታይ በዐይን ሰላም ትለዋለህ። ወሬም ልትጀምር ትችላለህ። ማን ነው? ምንድን ነው? ብለህ የብሔር ጥናት ውስጥ አትገባም። አሁን ያ ቀርቷል ወንድሜ….።”

“የትግራይ ተወላጆች ሰላም አይሉንም”

ኢብራሒም በላስቬጋስ ላለፉት ዓመታት መለስ ቀለስ ሲል፣ ‘ሊትል ኢትዮጵያ’ በሚል በሚጠራ ሰፈር ሌላም ነገር አስተውሏል።

ተጋሩዎች እንደ ድሮ አይደሉም። ራሳቸውን እየነጠሉ መጥተዋል።

“በፊት በቃ ጮክ ብለህ አውርተህ ስቀህ ትለያይ ነበር። አሁን ከጦርነቱ ወዲህ አብረውህ ለመታየት እንኳ ምቾት አይሰማቸውም።”

ይህ ከትዊን እስከ ትሮፒካና፣ ከሊንደል እስከ አርቪል የሚዘልቀው ‘ሊትል ኢትዮጵያ’ ዲስትሪክት አንደ ዲሲ ባይሆንም ብዙ ሐበሾች፣ ብዙ የሐበሻ ሱቆችና ምግብ ቤቶች የሚገኙበት ሰፈር ነው።

ለፈረንጅ፣ ‘ሊትል ኢትዮጵያ’ የሚለው ስም የአንድ ጠንካራ ‘ኮሚኒቲ’ን መንፈስ የያዘ ሊመስል ይችላል።

ሃቁ ግን ቀስ በቀስ የመላላት ምልክቶች እዚያም እዚም ይታያሉ፤ በተለይ ከጦርነቱ ወዲህ።

“የሚገርምህ አሁን ሐበሻ ሌላው ቀርቶ ሁካ (ሺሻ) ቤት እንኳ ለይቷል።”

“ጓደኞቼ ልጆቻቸውን በግብፅ ቤተ ክርስቲያን ነው ያስጠመቁት’

የትግራይ ተወላጆች ለምን መነጠልን መረጡ?

“ሕመምህን የሚጋራልህ ስታጣ፣ በአንተ ጫማ ሆኖ ስቃይህን ለመረዳት የሚፈቅድ ሰው ስታጣ ትነጠላለህ” ይላል ጌታቸው አሰፋ። ጌታቸው በካናዳ አንድ የትምህርት ተቋም ፕሮፌሰር ነው።

ይህን ‘ራስን የመነጠል ስሜት’ ለማስረዳት ለእርሱ የተሻለው መንገድ ካፌዎች አይደሉም፤ ቤተ ክርስቲያን ትቀርበዋለች።

ወደ ፕሮፌሰር ጌታቸው ሐሳብ ከመሻገራችን በፊት እዚህ ኬንያ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በደምሳሳው እንቃኝ።

በናይሮቢ ለኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ሁለት አብያተ ክርስቲያናት አሉ።

አንዱ ኪሊማኒ፣ አርግዊግስ ኮዴክ ጎዳና የሚገኘው መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ነው።

ሁለተኛው በጃምሁሪ፣ ኪንዳሩማ ጎዳና የሚገኘው ኪዳነ ምሕረት ነው።

የመጀመሪያው የኢትዮጵያውያን ነው። ሁለተኛው የኤርትራዊያን።

ይሁንና በርከት ያሉ የትግራይ ተወላጆች የአብያተ ክርስቲያናት ደጅ ላለመርገጥ ያደረጓቸው አጋጣሚዎች ተፈጥረውባቸዋል።

ሰበካው፣ ቅዳሴው ሁሉ “የፖለቲካ ከርቤ ያወደው፤ በፖለቲካ የተለወሰ ነው” ይላሉ።

አልያም በመንፈሳዊው ቤት ፍቅርን ሲሰብኩ የሚያውቋቸው ሰዎች ወደ ደጅ ሲወጡ ጦርነቱን የሚባርኩ፤ ግፋ፣ ስበቅ የሚሉ ሆነው እንዳገኟቸው ይናገራሉ።

በዚህ የተነሳ አንዳንድ የትግራይ ተወላጆች ወደነዚህ ሥፍራዎች ለመሄድ ህሊናቸው ይታገላቸዋል።

አማራጭ ሲያጡ ወደ ግብፅ ቤተ ክርስቲያን ያቀናሉ። ቢያንስ በቀኖና ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር ቀረብ ስለሚል።

ይህ በኬንያ ብቻ የሚታይ አይደለም። ይህ በአንዳንድ የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ብቻ የተስተዋለ ገጠመኝ ብቻም አይደለም።

ለዚህ ዘገባ ያነጋገርናቸው ግለሰቦች እንደሚሉት በተለይ በአገር ቤት መንፈሳዊ ከባቢ ውስጥ ፖለቲካ ሾልኮ ገብቶ ይገኛል።

በአንዳንድ መስጊዶች እና በአንዳንድ የፕሮቴስታንት የስብከት መድረኮችም ፖለቲካ የተጫነው ስብከት ጣል ማድረግ ተለምዷል።

ይህ ምዕመኑን እያሸሸ እንደሆነ የሚያምኑ ጥቂት አይደሉም።

ይህ ስሜት በባሕር ማዶ ካናዳም አንዳንድ ሥፍራዎች እንደተንጸባረቀ ጌታቸው (ፕሮፌሰር) ይናገራል።

“ጓደኞቼ ተመሳሳይ ነገር ገጥሟቸው ልጆቻቸውን ግብፅ ቤተ ክርስቲያን ለማስጠመቅ ተገደዋል” ይላል።

“ይህ የሚሆነው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ‘የኔ የምትለው ጥግ’ ስታጣ ነው።”

ጌታቸው ለዚህ ግሩም የሆነ ተምሳሌታዊ ማብራሪያ ሲሰጥ የኖህ መርከብን ታሪክ በማውሳት ነው።

ቤተ ክርስትያን በኖህ መርከብ ትመሰላለች፤ በመርከቢቱ እባብን እርግብም ገብተዋል። ሁሉም የገቡት ግን ከለላን በመሻት ነበር። ከጥፋት ውሃ ለመዳን።

“ልብ አድርግ፣ እርግቡና እባቡ አንዱ ሌላውን አምኖ አይደለም የገባው። ያመኑት የመርከቡን ባለቤት ነው።”

ቤተ ክርስቲያንም የኖህ መርከብ መሆን ይገባት ነበር።

“አንዳንዶች ያን ሰላምና ከለላ እዚያ አላገኙትም፤ በአጭሩ ለነርሱ የሚሆን ጥግ አላገኙም።”

ስለዚህ ምዕመናኑ ሌላ አማራጭ ማየት ጀመሩ።

“ይገርምሃል! ይህ የምልህ ጓደኛዬ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን ጥርሱን ነቅሎ ያደገ ነው፤ ዲያቆን ነው፤ ግራ ሲገባው ልጁን ለማስጠመቅ ግብፅ ቤተክርስቲያን ሄደ።”

ጌታቸው (ፕሮፌሰር) ከዚህ የከፋ አጋጣሚም ያውቃል።

በምርጫ ማጣት ነገሩን እያሰላሰሉ ልጆቻቸውን ሳያስጠምቁ 2 እና 3 ዓመት የሆናቸው ወላጆች አጋጥመውታል።

“አንዳንዴ የሚያጽናናህ ቃል ፈልገህ ሄደህ፣ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ላይ የምትሰማውን የጦርነት ቅስቀሳ የሚመስል ነገር ትሰማለህ። አንዳንዱ ምዕመን ታግሶ ይቀመጣል፤ አንዳንዱ ደግሞ ሁለተኛ ድርሽ አይልም፤ ጥጉን ይፈልጋል።”

የኡበር ፖለቲካ

ለላስቬጋስ ነዋሪው ኢብራሒም ከስታርባክሶች ሌላ የዲያስፖራ ፖለቲካን እጥፋት የሚለካው በታክሲዎች ነው።

“እዚህ ላስቬጋስ ገምት ካልከኝ ከ4 ሺህ እስከ 5 ሺህ የሚሆን ታክሲ አለ። 65 በመቶ የታክሲ ሥራውን የተቆጣጠሩት ደግሞ ‘ሐበሾች’ ናቸው” ይላል።

በተለይ የላስቬጋስ ‘ሃሪ ሬይድ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ’ ደጅ ላይ በጣም ብዙ ታክሲ የሚሠሩ ሐበሾች ተራ ሲጠብቁ ይታያሉ።

በነዚህ ቦታዎች ደንበኛ እስኪመጣ ሐበሻ ተሰብስቦ ፖለቲካን ነበር እንደ ሞተር የሚያሞቀው።

“በፊት ሁሉንም ሰብሰብ ብለው ታያቸው ነበር።”

ከጦርነቱ ወዲህ ግን ሁሉም የሚመስለውን ብቻ ተጠግቶ ክብ ሠርቶ ሲያወራ ነው የምታየው።

በፊት ትልቅ ክብ ነበር። አሁን ግን ትንንሽ ክቦች።

ቀስ በቀስ ወደ ትንንሽ ክቦች እየተከፋፈልን ይሆን?

“ኢትዮጵያ ነዳጅ የላትም፤ ብቸኛ ሃብቷ ጥብቅ ማኅበራዊ ትስስር ነው”

አቶ ገለታው ዘለቀ ፖለቲከኛ ናቸው።

ከዚህ ካነሳነው ጉዳይ ብዙም ባልራቁ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ጥናት አድርገዋል።

ከጦርነቱ ወዲህ ባሉ ጊዜያት በተለይ የሕዝብ መተማመን በአግድሞሽም በቁመትም መሸርሸሩን አይክዱም።

“ለዚህ መሠረት የጣለው የፖለቲካ አስተምህሮው ብሔር ላይ መቸከሉ ነው” ይላሉ።

አንድ ሰው አጠገቡ ያለውን ዜጋ ዝም ብሎ እንዲጠረጥር በሚያስችል ከባቢ ውስጥ ነው ያለነው። “ማኅበራዊ ሃብታችን እየላላ የሄደውም በዋናነት ለዚያ ነው።”

አቶ ገለታውን እንሞግታቸው።

የኢትዮጵያ ማኅበራዊ ሃብት ግን መጀመሪያውኑ ጥብቅ ነበር? ወይስ በእሳት ያልተፈተሸ ወርቅ ሆኖ ነው የቆየው?

በእርግጥስ ትስስራችን ጥብቅ ነበር ወይስ ቅብ የሚለው ጥያቄ ለአቶ ገለታው አነሳን።

“ልል እና ቅብ ነበር” የሚለው ነገር በፍጹም አይስማማቸውም። ጥብቅ በመሆኑ ላይ ጥርጣሬ ገብቷቸው አያውቅም።

“እንዲያውም (እኛ መሆናችን ነው እንጂ) አሁን የደረሰው መአት በሌላ አገር ላይ ደርሶ ቢሆን፣ ያ አገር አይቀጥልም ነበር” እስከ ማለት ይደርሳሉ።

እርሳቸው “የፖለቲካችን መናጆዎች” የሚሏቸው ብዙዎቹ ከፖለቲካችን ጋር የሚግተለተሉት የጥላቻ ንግግሮች፣ የኔ-ወ-ያንተ ትርክቶች ከባቢውን ሞልተውታል።

በዚህ ሁሉ ምስቅልቅል መቀጠላችን በራሱ ተአምር ነው ለአቶ ገለታው።

ለዚህም ነው አቶ ገለታው የማኅበራዊ ድራችን ጥንካሬ ተፈትኖ አያውቅም በሚለው የማይስማሙት።

ተፈትነን አልፈናል ነው የሚሉት። “አስረጂ አምጣ” ሲባሉ የኤርትራውያንን ሽኝት ያስታውሳሉ።

ለምሳሌ አቶ መለስ “የዐይናችሁ ቀለም ካላማረን….” ብለው ኤርትራውያንን ከኢትዮጵያ ሲያሰናብቱ ምን ሆነ?

“ትዝ የሚለኝ ብዙ ጎረቤቶች ለኤርትራዊያኑ ማልቀሳቸው ነው፤ ሲደብቋቸው ነበር፤ ንብረታቸውን ለ20 ዓመታት ጠብቀው አቆይተውላቸዋል። ይህ ስለ ማኅበረሰቡ ምንድነው የሚነግርህ ታዲያ?”

አቶ ገለታው፣ ስላለፈው ይህን ይበሉ እንጂ ስለወደፊቱ እርግጠኛ አይደሉም። በትንሹ ሐሳብ ይገባቸዋል።

“ድልድይና ፎቅ ቢፈርስ እንገነባዋለን። ማኅበራዊ ትስስር ግን እንደ ጡብ የምትደረድረው ነገር አይደለም። ከፈረሰ ፈረሰ ነው።”

ለርሳቸው መፍትሄው ታዲያ የዘር ፖለቲካን ማስወገድ ነው፤ ሁለተኛው ደግሞ በሚያለያዩን ሳይሆን በሚያስማሙን ነገሮች ላይ አብዝቶ መሥራት።

“ሰርቢያ እና ክሮአቶች ማለት እኮ ጎጃምና ጎንደር እንደማለት ናቸው”

አቶ ባይሳ ዋቅወያ ከዓለም የዘር ፍጅቶች አንዱ የሆነውን የክሮአቶች እና የሰርቢያን መጫረስአይተዋል። በወሬ ሳይሆን በአካል።

በፈረንጆች 1992 በክሮሺያ እና በቦስኒያ በኩል ሳራዬቮ ገቡ። ለሦስት ዓመታት እልቂቱ ሲቀጥል እዚያው ነበሩ።

ያን ጊዜ በተባበሩት መንግሥታት የሕግ ባለሙያ ሆነው ይሠሩ ነበር።

ኢትዮጵያን ከዩጎዝላቪያ ማመሳሰል መልካም ስሜት ባይሰጣቸውም አሁን እየሆነ ያለውን ነገር ሲመለከቱ ያ መጥፎ ትዝታ ፈንቅሎ እየወጣ የሚያስቸግራቸው ይመስላል።

ስለ ኢትዮጵያውያን ‘ጥብቅ’ ማኅበራዊ ትስስር በጠየቅናቸው ጊዜ ነገሩን በክሮአቶች እና በቦስኒያዎች በኩል ማስረዳትን መረጡ።

“ሰርብ እና ክሮአት ማለት እኮ የጎጃምና ጎንደር ወይ የወሎና ጎጃም ያህል ናቸው። በቃ አንድ ሕዝብ። አንዱ ለአንዱ ሚዜ ሆኖ፣ ተጋብቶ ተጋምዶ ነው የኖረው።”

ውስጥ ውስጡን ግን ጥላቻ ተዘርቶ ነበር።

ሆኖም ክሮአቶች ሰርቦችን ጥላቻ ካቶሊክ ሆነዋል። ሰርቦች ደግሞ ኦርቶዶክሶች ናቸው በብዛት።

በ2ኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ ክሮአቶች የሒትለር ደጋፊ ሆነው ብዙ ጥፋት ሰርቦች ላይ አደረሱ።

ጦርነቱ ሲያበቃ ደግሞ ሰርቦች የበላይነት አገኙና ተበቀሉ።

ክሮአቶችን ከነነፍሳቸው ቀበሯቸው። አቃጠሏቸው። የተረፉት ወደ ጀርመን፣ ካናዳ፣ አውስትራሊያ ጠፉ።

ክሮአቶች 70 ዓመት ቂም ይዘው ጠበቁና ዩጎዝላቪያ ስትፈርስ ዳግም ተላለቁ።

አቶ ባይሳ ይህን የታሪክ ትምህርት ያመጡት ያለ ምክንያት አይደለም።

ክሮአቶች እና ሰርቦች ማኅበራዊ ትስስራቸው ልክ እንደ ኢትዮጵያ አስደናቂ የሚባልለት ስለነበረ ነው።

በኋላ ላይ ጥላቻ ዘለቀና ቦረቦረው። ሲገዳደሉ ታዲያ የክርስትና አባት የክርስትና ልጁን አልማረም። ሙሽራ ለሚዜው ርሕራሄን አላሳየም።

‘ምን መሰለህ፤ ጦርነት ውስጥ አንዴ አንድ ሰው ትገድላለህ። ከዚያ በኋላ ሰው አይደለም የሚታይህ። አውሬ የመግደል ያህል ሆኖ ነው የሚሰማህ። ‘

አሁን የርሳቸው ትልቁ ፍርሃት ይህ የትስስር መላላት በኢትዮጵያም መታየት መጀመሩ ነው።

የኛ ማኅበራዊ ትስስር ድሮም የሚያመረቃ ነበር ብለው አያስቡም። ስለ ኢትዮጵያ ስናወራ በተግባር ስለ ሦሰት ብሔር ነው እንጂ የምናወራው ሌላውን እንደምንዘነጋ ይሰማቸዋል።

ለምንድነው ማኅበራዊ ትስስራችን በዘመን ውስጥ ያልጎለበተው ለሚለው ጥያቄ ግን ቅልብጭ ያለ መልስ ይሰጣሉ።

‘ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ‘ብሔረ-አገር’ እንጂ ‘አገረ-ብሔር’ የለም። ብሔረ አገር ምሥረታው አልተሳካም። በዘመናት መንግሥታት ኢትዮጵያን መሩ እንጂ ኢትዮጵያዊያንን አልፈጠሩም። ‘ ይላሉ።

በዚህ የተነሳ ግንኙነቱ ልል ሆኖ ቆየ።

 በታሪካችን ሁሉ ልል እንደሆነ በቆየው ማኅበራዊ ትስስር ላይ ጦርነትና ጥላቻ ተዘርቶበት አሁን ደግሞ ብሶበታል ይላሉ አቶ ባይሳ።

ስለዚህ ነገ ያስፈራቸዋል።

‘በቀላሉ ከዚህ አዘቅት የምንወጣ አይመስለኝም።' የሚሉትም ለዚሁ ነው።

ፖለቲከኞች ዞር ቢሉ፥ ገበሬው በብሔር ይጫረሳል?

አሁን የምናየው ልል ማኅበራዊ መስተጋብር፣ ክፍፍል፣ ሽኩቻ፣ጥላቻና መመራረዝ ምናልባት የበይነ መረቡ ዓለም አጋኖ እያሳየን ይሆን?

ከዛሬ ነገ የምንፈርስ የሚመስለን መነጽራችን በጥላቻ የደፈረሰው ማኅበራዊ ሚዲያ አደምኖት ይሆን?

በሌላ አነጋገር ገበሬው ዘንድ ብንሄድ የምንፈራው ሁሉ የለ ይሆን?

ፖለቲከኛ ዞር ቢልለት ቡና እየተጠራራ፣ ሐዘን ለቅሶ እየደረሰ በፍቅር መኖሩን ይቀጥላል?

ፕሮፌሰር ጌታቸው ይህን ለመመለስ ማኅበረሰብን በአራት እርከኖች ያስቀምጣል።

ቤተ መንግሥት፣ ቤተ ክህነት፣ ቤተ ልሂቅና ቤተ ሕዝብ።

በኢትዮጵያ ታሪክ ቤተ መንግሥትና ቤተ ክህነት እጅና ጓንት ሆነው ኖረዋል። ሕዝብ ላይ ጭቆና በማድረስም ተቃርነው አያውቁም።

በዚህ ዘመን ደግሞ ቤተ ልሂቅ ተደምሯል።

ሦስቱ ገለል ቢሉለት ቤተ ሕዝብ አብሮ ለመኖር የሚያበቃ በቂ ማኅበራዊ ትስስርን አዳብሯል ብሎ ያምናል ፕሮፌሰር ጌታቸው።

ምናባዊ ጥያቄያችንን እንድገመው።

ለምሳሌ አማራና ትግራይ ድንበር ላይ ሄደን ፖለቲከኛን ገለል አድርገን ብንቆይ ገበሬዎች መሀል ምን ይፈጠራል?

ይተላለቃሉ ወይስ ይኗኗራሉ?

‘የኢህአዴግ ቁልቁለት ጉዞ’ የሚለው ብዙ ያነጋገረ መጽሐፍ ደራሲ ብርሃነ ጽጋብ ይህን ጥያቄ የሚመለስ አጋጣሚን በመጽሐፋቸው ሰንደዋል።

ደራሲው ከገጽ 296-313 የሚያወሱት የትግራይና የአማራ ገበሬዎች አቶ ገዱና አቶ አባይ ወልዱ በተገኙበት መድረክ ያደረጉትን አስገራሚ ስብሰባ ነው።

ጉዳዩ የግጨው የወሰን ጉዳይ ነበር።

ቅራቅር በምትባል በአማራ ክልል የጠገዴ ወረዳ፣ በትግራይ ደግሞ ጸገዴ ወረዳ መካከል የምትገኝ ትንሽ መንደር በተደረገ ልዩ ስብሰባ የትግራይና የአማራ ገበሬዎች ለኢህአዴግ አመራሮች የተናገሩትን ደራሲው ለታሪክ ዘግበውት ይገኛል።

‘እኛ ዘመዳሞች ነን፣ አንገዳደልም። የተጣላችሁት እናንተ ፖለቲከኞች ናችው። …ነገሩ ተበላሽቶ እንኳ ወደ ጦርነት ካስገባችሁን በሚል ያ ከመጣ ወደ ሰማይ እንተኩሳለን ተባብለን ተስማምተን ነበር። ‘

ፕሮፌሰር ጌታቸው፣ አማካዩ ኢትዮጵያዊ የዘረኝነት ችግር አለበት ብዬ አላምንም የሚለውም ለዚህ ነው።

‘ቤተ እምነቱ፣ ቤተ መንግሥቱና ቤተ ልሂቁ ግን ትስስራቸው ያስፈራኛል። ምክንያቱም ቤተ ሕዝብን ሊበክሉ ይችላሉ።‘

በጥቅሉ የፕሮፌሰር ጌታቸው እምነት ይህ ይሁን እንጂ፣ ይህን እምነቱን የሚሸረሽር ጥቂት አጋጣሚዎች አልተፈጠሩም ማለት አይደለም። በተለይ በከተሞች አካባቢ።

‘አንድ ዘበኛ ሌላውን ዘበኛ፣ አንድ የኔ ቢጤ ሌላውን የኔ ቢጤ በማንነቱ ምክንያት አሳልፎ ሲሰጠው ታይቷል። የማንም ተጽእኖ ሳይኖር ነው ታዲያ።'

ይሁንና ፕሮፌሰር ጌታቸው እንዲህ ዓይነቱን ነገር ቢኖር እንኳ አለ ብሎ ማመን የሚፈልግ አይመስልም።

“ማመን የምፈልገው በቃ እነዚያ የኔ ቢጤዎች ያን ያደረጉት ተገደው ነው ብዬ ነው” ይላል። ለምን? ሲባል

‘ጤንነቴ እንዳይቃወስ።' ሲል ፈጥኖ ይመልሳል።

በማኅበራዊ ትስስራችን መላላት ጉዳይ ጨርሶ ተስፋ ለመቁረጥ የፈቀደ አይመስልም።

ጥላቻው ወደ ትውልድ ያልፋል?

የላስ ቬጋሱ ኢብራሒም ከሁሉ የሚያሳስበው በልጆቹ ትምህርት ቤት ደጅ ላይ የሚያስተውለው ነገር ነው።

‘ምን መሰለህ፣ በፊት ልጆቻችንን ከትምህርት ቤት ስናወጣ መኪና ማቆምያ ቦታ ላይ ሰላም-ሰላም እንባባል ነበር፤ ስለ ልጆቻችን እናወራም ነበር።

‘ከጦርነቱ ወዲህ ግን በተለይ ተጋሩዎች ሰላም አይሉንም፤ ወይም ደግሞ ሰላም ላለማለት አይናቸውን ሲያሸሹ ታያለህ። ብቻ ያለው ነገር ደስ አይልም።' ይላል።

ኢብራሒም የትግራይ ተወላጆች በብዙ ተቀይረው ተመልክቷል።

ለምሳሌ ልጆቻቸውን ከሚያለብሷቸው አልባሳት ጀምሮ፣ መኪናቸውን እስከሚያጋጌጡበት ቁሳቁስ ድረስ የፖለቲካ አስተሳሰባቸውን የሚንጸባረቅበት እየሆነ ነው።

ያ በራሱ እምብዛምም ችግር ሆኖ አይታየውም ለኢብራሒም።

መቃቃሩ ቀስ በቀስ ወደ ልጆች እንዳይወርድ ግን ያሳስበዋል።

‘የኛ ሰላም አለመባባል በልጆቻችን አእምሮ ላይ ጥያቄ መፍጠሩ አይቀርም፤ ደግሞም ልጆች ዝም አይሉም፤ ይጠይቁሃል። እንዴት ታስረዳቸዋለህ? ምን ብለህ?’

‘አንዳንዴ ለልጆቻችን ጥላቻን እያወረስናቸው ይሆን? አውቀንም ሆነ ሳናውቀው? አልላሁ። '

በመቼው እዚህ ተደረሰ?

ያለፉት ሁለት ዓመታት በእርግጥ ሁለት ዓመታት ብቻ ነበሩ?

የአባትን ገዳይ በስልክ ይዞ መዞር

አቶ ባይሳ የውጭ ወረራን እና የእርስ በእርስ ጦርነትን ለየቅል መልኮች ሲያስቀምጡ፣ የውጭ ወረራን ‘ቅዱስ’ ያስመስሉታል።

‘ዚያድባሬ መጣ፤ ሄደ። ጣሊያን መጣ ሄደ። ብዙ ጥፋት አድርሰዋል። ነገር ግን በነሱ ላይ ቂም የያዘ አንድም ኢትዮጵያዊ አታገኝም’ ይላሉ።

የእርስ በእርስ ጦርነት ግን ክፉ ነው። በዳይና ተበዳይ ጎረቤት ሆነው እንዲኖሩ ያስገድዳል።

ይህ ዘመን ደግሞ ነገሩን የበለጠ ክፉ ሳያደርገው አልቀረም።ዕድሜ ለማኅበራዊ ሚዲያ።

ተጎጂዎች ቁስላቸው በየደቂቃው ያመረቅዛል። ጉዳቱ ሲደርስ መታመም አለ፤ በጉዳቱ ላይ ሌላው ሲያፌዝ ደግሞ ሌላ ሕመም አለ።

 ቴክኖሎጂ ሌላ ቁስል ነው። ጦርነትን እንደ ሰርግ ቀርጾ ያስቀራል።

አንዳንዶች የእናታቸውን ደፋሪ፣ የአባታቸውን ገዳይ በስልካቸው ጭምር ይዘውት ነው የሚዞሩት።

ድሮ የጦር ሜዳ ውሎ ከዘመቻ በሚመለስ ወታደር ነበር በገደምዳሜ የሚሰማው።

ዛሬ ግን ሞልቶ የፈሰሰ ግፍ በካሜራ ተቀርጾ ይቀመጣል። እንደ ኳስ በቀጥታ በዩትዩብ ይተላለፋል። ገዳይ ከሬሳ ጋር ‘ሰልፊ’ ይነሳል።

ይህ ደግሞ ይቅር መባባልን ዳገት ያደርገዋል።

ለፕሮፌሰር ጌታቸው የአንድ ማኅበረሰብ ማኅበራዊ ትስስር (Social fabric) መለኪያ በተበዳይ ጫማ ውስጥ መሆን ነው። ሌላው ሁሉ ትርፍ ነው።

አሁን ያለው ስሜት ግን ያ አይደለም፤ እንዲያውም በተቃራኒው ይመስላል።

አይዞን የሚል የለም። ችግሩ ደግሞ ገዳይም ይፈራረቃል። ተበዳይም ይፈራረቃል። አዙሪት። ክብ ልፋት።

‘ብዙ ተጎዳድተናል፤ ከሁለቱም ወገን ስንት ሰው በረሃ ውስጥ እንደተቀበረ አናውቅም። ‘ ይላሉ አቶ ባይሳ።

‘የሚያምር ጦርነት ባይኖርም የኛ በጣም አስቀያሚው ይመስለኛል።‘ ይላሉ ብዙ እልቂት በዓለም ዙርያ የተመለከቱት አቶ ባይሳ።

አሁን ጥያቄው አንድ ነው። ቁስላችን ይጠግጋል? መቼ? ወይስ ገና ለትውልድ ያልፋል?

‘ወደ ትውልድ እንዳያልፍ ማድረግ እንችላለን። ያን ለማድረግ ዕድል አለ። ካልዘገየን። የሰላምን መንገድ ከመረጥን። ‘ ይላሉ አቶ ባይሳ ዋቅዋያ። ብዙ እልቂት ያዩት። ለሦስት ዓመት ሳራዬቮ የከተሙት።

በሁለት ዓመት ይህን ካየን፣ በአራት ዓመት ምን ልናይ ይሆን?