ለ15 ወራት ደሞዛቸው ያልተከፈላቸው የትግራይ የሕክምና ባለሙያዎች

የፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ኃይሎች ወደ ጦርነት ከመግባታቸው በፊት ማጀታቸው የሞላ፣ ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት የሚልኩ፣ ለቤተሰቦቻቸው እና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው የሚተርፉ ነበሩ።

በመቀለ የሚገኙ እና ቢቢሲ ያነጋገራቸው መምህራን፣ የሕክምና ባለሙያዎች እና ሌሎች የመንግሥት ተቀጣሪዎች ከሁለት ዓመት በፊት የነበራቸው ሕይወት የዛሬውን አይመስልም ነበር።

ዛሬ በትግራይ ያለው ጦርነት ተባብሶ፣ በክልሉ የማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ሥራ አቁመው፣ የሰብዓዊ እርዳታ ተመናምኖ ሁሉም የሰው እጅ ጠባቂ እንደሆነ ይናገራሉ።

ለሌሎች ይዘረጋ የነበረ እጅ ዛሬ ለምጽዋት ደጅ ይጠናል። ለገባ ለወጣ ይቆረስበት የነበረ መሶብ ጦሙን አድሯል።

ዕድለኛ የሆነ 15 ኪሎ ግራም የእርዳታ ስንዴ ዱቄት ተቀብሎ ልጆቹን ያበላል።

የተቀረው እና ምንም ማድረግ የማይችለው ደግሞ የተሻለ ቀን እንዲመጣ፣ ጦርነቱ እንዲያበቃና ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ይጸልያል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ኅብረት እና አሜሪካ እየተባባሰ የመጣው ከባድ ውጊያ ያለውን ሁኔታ አስከፊ ሊያደርገው እንደሚችል በመግለጽ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።

ወደ ትግራይ ክልል ጋዜጠኞች እንዲገቡ ባለመፍቀዱ እና ማኅበራዊ አገልግሎቶች በመቋረጣቸው ምክንያት፣ የግጭቱ መጠን እና ያስከተለው ሰብአዊ ቀውስ ስፋት በዝርዝር ለመረዳት አስቸጋሪ አድርጎታል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸውን የሕክምና ባለሙያዎች ሕይወት እናንተ ቤት ምን ይመስላል ሲል ጠይቋቸዋል።

‘ከተፈናቃዮች ጋር ተሰልፌ የእርዳታ ስንዴ ተቀበልኩ’

በአይደር ሆስፒታል የቀዶ ጥገና ባለሞያ የሆኑት ዶ/ር ፋሲካ ዓምደሥላሴ ለረዥም ወራት ደሞዝ እንዳልተቀበሉ እና ከብዙ ወራት በኋላ “ዕድል ቀንቶ” የሰብአዊ እርዳታ ድርጅቶች የሚሰጡትን የእርዳታ ስንዴ መቀበላቸውን ይናገራሉ።

“ሕይወት አድን ምግብ ካላገኙ በሚሊዮን ከሚቆጠሩ ህጻናት ጋር ሲነጻጸር ልጆቼ ዕድለኞች ናቸው” በማለት ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር የሰጣቸውን እርዳታ የሚያሳይ ምስልና ጽሑፍ በትዊተር ገጻቸው ላይም አስፍረው ነበር።

“እርዳታ ሳገኝ በጣም ተደሰትኩ፤ ከዚህ የባሰ መጥፋት፣ ህመም እና ሞት ነው የሚመጣው። በርካታ መልካም ሕይወት የነበራቸው ሰዎች፣ አስተማሪዎች . . . ወደ ጎዳና ወጥተው እያየናቸው ነው። የጉልበት ሥራ የሚሰሩ፣ መንገድ ላይ ሳሙና የሚሸጡ ብዙ የመንግሥት ሠራተኞች አሉ” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የሆስፒታሉ ሠራተኞች በግንቦት ወር 2013 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ደሞዛቸው እንደተከፈላቸው ገልፀው፣ ነገር ግን በዚያው ዓመት ሰኔ ወር ላይ የትግራይ ኃይሎች ከተማዋን ከተቆጣጠሩ በኋላ የወር ደሞዛቸው አልተከፈላቸውም።

ዶ/ር ፋሲካ፣ አክለውም በባሕር ማዶ ወዳጅ ዘመድ ያላቸው የእነርሱን ድጋፍ እየጠበቁ አንደሚኖሩ አስታውሰው፣ ነገር ግን ሁሉም የሚደግፈው ዘመድ አለው ማለት እንዳልሆነ ያብራራሉ።

አክለውም “በሰብአዊ እርዳታ የሚመጣው ስንዴ ተቀብለው ለወፍጮ ቤት የሚሆን ገንዘብ የሚቸገሩ አሉ” ሲሉ የችግሩን ግዝፈት ለማሳየት ይጥራሉ።

በአይደር ሆስፒታል ድንገተኛ ክፍል ውስጥ የሚሰራ እና ከሰኔ 30 ጀምሮ ወርሃዊ ደሞዙን ያላገኘው ስሜን አትግለፁ ያለን ዶክተር “ባልደረቦቼ በሙሉ ችግር ውስጥ ናቸው” ይላል።

ይህ ዶክተር ላለፉት ሦስት ዓመታት በሆስፒታሉ ውስጥ ያገለገለ ሲሆን፣ ባለትዳርና የአንድ ልጅ አባት ነው።

“ከዚህ በፊት ሕይወቴን እየመራሁ ወላጆቼን ጭምር እረዳ ነበር። አሁን ግን ለአካለ መጠን እንዳልደረሰ ልጅ ተመልሰው ወላጆቼ እየረዱኝ ነው። እነሱ ገጠር ሆነው የሚያገኟትን እህል እየተካፈልን ነው የምንኖረው።”

አብዛኛዎቹ የሆስፒታሉ ሠራተኞች እንደሌላው ማኅበረሰብ እርዳታ ይጠብቃሉ የምትለው ነርስ ፍሬ በበኩሏ፣ “ከገበሬ ዘመዶቼና ወዳጆቼ የሚላክልኝን እየጠበቅኩ ቀን እገፋለሁ” ትላለች።

ከጦርነቱ በፊትም ቢሆን በክልሉ ውስጥ በነበሩ ማኅበራዊ ችግሮች እና ዝቅተኛ የሥራ ዕድል ምክንያት በርካታ የቤተሰብ አባላት እርስ በእርስ በመተጋገዝ ላይ ነበር የሚኖሩት።

“የቤተሰብና የዘመድ ኃላፊነት የተሸከምን ዜጎች እንደመሆናችን መጠን ያለ ክፍያ ልጆችን ማሳደግ ከባድ ነው። ምግብ ተበልቶ በሕይወት መቆየት ከባድ ሆኖ ሳለ በህክምና ሥነ-ምግባር ስለ ሌሎች ሕይወት መጨነቅ ስላለብን፣ ሥራ መቋረጥ የለበትም በሚል በባዶ ሆዱ ወደ ሥራ ቦታ መጥቶ ነው እየሰራ ያለው” ስትል ነርስ ፍሬ ትገልጻለች።

የመቀለ ዩኒቨርስቲ አካል የሆነው አይደር ሪፈራል ሆስፒታል በትምህርት ሚኒስቴር ስር የሚተዳደር ነው።

ቢቢሲምለሠራተኞቹ የደመወዝ አልተከፈለንም ጥያቄ ምላሽ ለማግኘት ከትምህርት ሚኒስቴር እና ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በስልክና በጽሑፍ መልዕክት ብንሞክርም ጥረታችን አልተሳካም።

በባዶ ሆድ የተራቡ ሰዎችን ማከም

በትግራይ ከአንድ ዓመት በላይ የባንክ እና የትራንስፖርት አገልግሎት የተቋረጠ ሲሆን መሠረታዊ ሸቀጦች ከአፋር እና ከአማራ ክልሎች "በሕገ-ወጥ" መንገድ እንደሚገቡ የቢቢሲ ምንጮች ገልጸዋል።

በዚህም ምክንያት ከፍተኛ የመሠረታዊ ሸቀጦች የዋጋ ንረት እና የገንዘብ እጥረት እንዳለ፣ ካለው የነዳጅ እጥረት የተነሳም የትራንስፖርት ዋጋ በመናሩ የዕለት ኑሯቸው መክበዱን ነዋሪዎች ያስረዳሉ።

“ለራስና ለልጆች መሆን አለመቻል ሕይወት ዓላማ እንዲያጣ ያደርጋል። በአሁኑ ጊዜ መኮረኒ፣ ሩዝ፣ ዘይት ውድ ናቸው” ሲሉ ሌላ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የሕክምና ባለሙያ ተናግረዋል።

አብዛኞቹ የመንግሥት ሠራተኞች የሚኖሩት በኪራይ ቤት በመሆኑ፣ ገንዘብ አለማግኘት አከራይና ተከራይ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ እንዲገቡ አድርጓል የሚለው ደግሞ በመቀለ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህርና የጤና ባለሙያ የሆነው ዶክተር ነው።

“አብዛኛው ሠራተኛ አይደለም ለቤት ኪራይ ለታክሲም መክፈል አይችልም። እኔ የሰው ፊት ላለማየት ስል የሞቀ ቤት ባይሆንም 70 ካሬ መንደር በሚገኘው ያላለቀ ቤት ውስጥ ነው የምኖረው። ኤሌክትሪክ እና ውሃ በጭራሽ አይታሰቡም፤ ከጉድጓድ የሚመጣ ውሃ ነው የምንጠጣው። ውሃ ማከሚያ መድኃኒት እንኳ አናገኝም።”

የትግራይ ክልል ከአንድ ዓመት በላይ ከበባ ላይ በመቆየቱ ምክንያት የሕክምና ባለሞያዎች እና ታካሚዎች የሚያደርጉት ግራ ገብቷቸዋል የሚሉት አስተያየት ሰጪዎቹ፤ “የሰብአዊ እርዳታ እንዲሁም የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት ተከትሎ በርካታ ታካሚዎች እጃችን ላይ እየሞቱ ይገኛሉ” ይላሉ።

ህጻናት በምግብ እጥረት ዋነኛ ተጠቂዎች መሆናቸውን የገለፁት የሕክምና ባለሙያዎቹ፣ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በትግራይ 2,500 የሚጠጉ ህጻናት በምግብ እጥረት መሞታቸውን ቢቢሲ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ይህ አኃዝ ግን መሬት ላይ ያለውን እውነታ እንደማያሳይ የህክምና ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

የሰብአዊ እርዳታ ሰጪ ተቋማት ጦርነቱ አስከፊ የሆነ ሰብአዊ ቀውስ ማስከተሉና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ገድሎ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች አፈናቅሏል ሲሉ ይገልጻሉ።

“ሁኔታው በጣም አሳሳቢ ከመሆኑ የተነሳ ደሞዛችን ሳይከፈለን መስራታችን ብቻ ሳይሆን ችግሩ ታካሚዎች ላይ ጭምር ሲታይ ከባድ ያደርገዋል። ተርበን መጥተንም የተራቡ ሰዎች ማከም፣ እንዲህ አይነት ምግብ ብሉ ማለት ይከብዳል። የምንሰራበት ሆስፒታል ሳይቀር የሚዘጋበት ደረጃ ላይ ደርሷል” ሲል ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀው ዶክተር ተናግሯል።

አክሎም “ብዙውን ጊዜ የምናሳልፈው በሥራ ላይ ነው፤ ባለን ጊዜ ደግሞ ዛሬ ወይም ነገ እርዳታ እናገኛለን ብለን ስንጠብቅ እንውላለን። ገጠር የሚኖሩ ወላጆቼ እርሻ ስላላቸው አሁን እየረዱኝ ነው” ብሏል።

“በእግዚአብሔር ጸጋ ነው የምኖረው” የምትለው ነርስ ፍሬ፣ ከሰባት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ልጆች እንዳሏትና ልጆቿ የለመዱት ምግብ እንድታቀርብላቸው ሲጠይቋት እንደምትጨነቅ ትናግራለች።

“ምግብ ሳይበሉ የሚያድሩበት ጊዜም ስላለ፣ ለጥያቄያቸው መልስ ማጣት የሚፈጥረው ህመም ከባድ ነው። በጭንቀት ራሴን እንዳልጎዳ እፈራለሁ።”

በሰኔ ወር መጀመሪያ 2022 የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ክብሮም ገብረሥላሴ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በክልሉ ትልቁ ሆስፒታል በመብራት መቆራረጥ እና በመድኃኒት እጦት ምክንያት ተገቢውን አገልግሎት መስጠት አቁሟል ብለው ነበር።

ነገር ግን በጦርነቱ ምክንያት በተፈጠሩ ተደራራቢ ችግሮች ምክንያት፣ ሆስፒታሉ የሚሰጠው የህክምና አገልግሎት የሚፈለገው ያህል ባይሆንም ሠራተኞች በግል ችግራቸው ምክንያት ሥራ ለማቆም አስበው አያውቁም ስትል ነርስ ፍሬ ገልጻለች።

“መንግሥት ግዴታውን እንዳልተወጣ አውቃለሁ፤ ሆኖም እኔ ወደ ሥራ ገበታ ባለመምጣቴ የሚጠፋ ሕይወት አለ ብዬ ስለማስብ ነው ወደ ሥራ የምመጣው። እኛ አገልግሎት ካቆምን ነገ እዚህ አገር ማን ይኖራል? ብዙ ታማሚዎች በመድኃኒት፣ በምግብ እና በኦክሲጅን እጦት ሞተዋል። ነገር ግን ሊተርፍ የሚችለውን ሰው ማዳን በመቻሌ ውጤታማ ነኝ ብዬ አስባለሁ።”

ዶ/ር ፋሲካ ዓምደሥላሴ ሕክምና ባለሙያዎቹ እየሰሩ የሚገኙበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ሲያስረዱ

“ቁርስ ሳይበሉ ወደ ሥራ ቦታ መጥተው የወደቁ ነርሶች አሉ፤ በጣም አሳዛኝ ሁኔታ ላይ ነን። አንድ ሰው ያመጣው ምግብም ቅመሺ ተብላ ልጆቼን ቁርስ ሳልሰጣቸው ነው የመጣሁት ብላ ያለቀሰች ነርስ አለች። በችግር ምክንያት የሚለምኑና ወደ ቤተሰቦቻቸው የተመለሱ አሉ” ይላሉ።

“የምንኖረው ሕይወት፣ ይሆናል ብለን አስበነው የማናውቅ ነው” የሚለው ሌላው በሆስፒታሉ ውስጥ መምህርና የጤና ባለሙያ የሆነው ዶክተር በበኩሉ፣ በትራንስፖርት እና በገንዘብ ችግር ምክንያት ቤተሰቦቹ ያሉበት ሁኔታ እንደማያውቅ ይናገራል።

“ሕይወታችን በቃላት ከሚገለጸው በላይ ነው፤ ነገር ግን ሥራ አላቆምንም። ለማንኛውም እኛ የምንሄደው መድኃኒት ቢያጡም ‘አይዟችሁ’ ለማለት ከታካሚዎች መራቅ ስለሌለብን ነው። ሙያችን ገንዘብ አልተከፈለንም በሚል የሚተው አይደለም። እዚህ የታመሙትን ትተን ቤት እንድንቀመጥ ህሊናችን አይፈቅድልንም። የተራቡትን ማብላት ባልችልም የታመሙትን መድኃኒቱን ሰጥቼ በሕይወት ማኖር እችላለሁ።”

የሆስፒታሉ ሠራተኞች በፌደራል መንግሥት ተቋም ተቀጥረው የሚሰሩ በመሆናቸው በጦርነቱ ምክንያት “ሆን ተብሎ” የወር ደሞዛችን ተይዟል የሚል ቅሬታ አላቸው።

“ብዙ የሰብአዊ እርዳታ ኤጀንሲዎች ገንዘብ አምጥተው ለሠራተኞቻቸው ይከፍላሉ፤ የቀጠረን አካል ግን ዝም አለ። ባንክ ዝግ ነው፤ ከዚህ በፊት የቆጠብኩት በችግር ጊዜ እንዳልጠቀምበት ጭምር ነው የተከለከልኩት። ይግባኝ የማይባል ፍርድ” በማለት አንድ ሠራተኛ ቅሬታውን ለቢቢሲ ገልጿል።

እስከ አሁን ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶች አልተሳኩም።

“በጣም የሚያሳስበኝ ነገር ይህ ሁኔታ መቼ እንደሚያበቃ ነው። ልጆቻችን ይዘን እንዳንወጣ የስደት መንገዱ በእግር የሚኬድ ስለሆነ በወታደሮች እንዳንገደል እንፈራለን። ሙሉ ለሙሉ ተከባችሁ በረሃብ ጥፉ የሚያስብል ሁኔታ ነው ያለው” ብሏል ዶክተሩ።