ዱባይን ያጥለቀለቃት ጎርፍ ደመናን ወደ ዝናብ በሚቀይረው ቴክኖሎጂ የተፈጠረ ይሆን?

በጎርፍ የተጥለቀለቀችው ዱባይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዱባይ ከሰሞኑ አውሎ ንፋስ በቀላቀለ ከባድ ዝናብ መመታቷን ተከትሎ በጎርፍ ተጥለቅልቃ ነበር።

በ75 ዓመት ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ የተባለው ዝናብ ከፍተኛ ንብረት አውድሟል፣ እንቅስቃሴ ቀጥ እንዲል አድርጓል፣ እንዲሁም ሕይወት ቀጥፏል።

ከዚህ ዝናብ ጋር ተያይዞም ደመናን ወደ ዝናብ ስለሚቀይረው ቴክኖሎጂ በርካታ መላምቶች እየተሰነዘሩ ነበር።

በሰው ሰራሽ መንገድ ደመናን ወደ ዝናብ መቀየር ወይም ‘ክላውድ ሲዲንግ’ የመጣ ጎርፍ ነው የሚሉ ወሬዎችም እየተሰሙ ነው።

በዱባይ የተከሰተው ዝናብ ያልተመለደ ነበር? ለዚህ ከባድ ዝናብ መንስዔውስ ምንድን ነው?

ዝናቡ ምን ያህል የከፋ ነበር?

በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ዳርቻ ላይ የምትገኘው ዱባይ ከዓመት እስከ ዓመት በአብዛኛው በጣም ደረቅ የምትባል ናት።

ነገር ግን አገሪቷ ከ100 ሚሊሜትር (3.9 ኢንች) በአማካይ ዓመታዊ የዝናብ መጠን ቢኖራትም አልፎ አልፎ ከፍተኛ ዝናብ ያጋጥማታል።

ከዱባይ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በአልአይን ከተማ ከሰሞኑ ባጋጠመው ከፍተኛ ዝናብ ወደ 256 ሚሊሜትር (10 ኢንች) የዝናብ መጠን በ24 ሰዓታት ውስጥ ብቻ ተመዝግቧል።

ለዚህ ከፍተኛ ዝናብ መንስዔው ሞቃታማ እና እርጥብን አየርን የሳበው እና ሌሎች የአየር ሁኔታዎች እንዳይገቡ የከለከለው ዝቅተኛ ግፊት ያለው የአየር ሁኔታ ሥርዓት መቋረጡ ነው ተብሏል።

“ይህ የዓለማችን ክፍል ያለ ዝናብ ረጅም ጊዜ የሚቆይ እንዲሁም መደበኛ ያልሆነ ከፍተኛ ዝናብ ይከሰትበታል። ነገር ግን ከሰሞኑ የተከሰተው ከባድ ዝናብ በጣም ያልተለመደ ነው” ሲሉ የባሕረ ሰላጤው የአየር ንብረት እና በዩኒቨርስቲ ኦፍ ሬዲንግ የሜትሮሎጂ ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ማርተን አምባውም ያስረዳሉ።

የአየር ንብረት ለውጥ ምን ሚና አለው?

ከሰሞኑ በተከሰተው ከባድ ዝናብ የአየር ንብረት ለውጥ ምን ያህል ሚና እንደተጫወተ በትክክል ማወቅ በአሁኑ ወቅት አይቻልም።

እሱን ለማወቅ ተፈጥሯዊ፣ ሳይንሳዊ እና ሰዋዊ ሁኔታዎችን መተንተን ስለሚያስፈልግ ያ ብዙ ወራት ሊፈጅ ይችላል።

ነገር ግን የተመዘገበው ታሪካዊ የተባለው የዝናብ መጠን የአየር ንብረት ለውጥ ሚና እንዳለው የማይካድ ነው። በቀላል አነጋገር ሞቃት አየር የበለጠ እርጥበት ይይዛል በአሃዝም ስናሰላው ለእያንዳንዱ ዲግሪ ሴልሺየስ 7 በመቶ ተጨማሪ እርጥበት እንደማለት ነው።

ይህ ደግሞ የዝናብ መጠን ይጨምራል።

“የዘነበው የዝናብ መጠን ከፍተኛ እና ክብረወሰን የሰበረ ነው። እየተከሰተ ካለው የአየር ሙቀት መጨመር ጋርም የሚጣጣም ነው። ይህ ሙቀት ከፍተኛ እርጥበት እንዲሁም አውሎ ንፋስ በማስከተል ከፍተኛ ዝናብ እና የጎርፍ መጥለቅለቅን ያስከትላል” የሚሉት ደግሞ በሬዲንግ ዩኒቨርስቲ የአየር ንብረት ሳይንስ ፕሮፌሰር የሆኑት ሪቻርድ አለን ናቸው።

በቅርቡ የተደረገ ጥናት እንደሚያመለክተው የዓለም ሙቀት እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ የተባበሩት የአረብ ኤምሬትስ የዝናብ መጠን በክፍለ ዘመኑ መጨረሻ 30 በመቶ ገደማ ሊጨምር ይችላል።

“የሰው ልጅ ነዳጅ፣ ጋዝ እና የድንጋይ ከሰልን መጠቀም ከቀጠለ የአየር ንብረት መሞቆ ይቀጥላል። የዝናብ መጠንም እየጠነከረ ይሄዳል። በጎርፍ አደጋ ሰዎች ሕይወታቸውን ያጣሉ” ሲሉ በለንደን የኢምፔሪያል ኮሌጅ የአየር ንብረት ሳይንስ ከፍተኛ ምሑር የሆኑት ዶክተር ፍሬድሪክ ኦቶ ያስረዳሉ።

በጎርፍ የተጥለቀለቀችው ዱባይ

የፎቶው ባለመብት, reuters

ለዚህ ከፍተኛ ዝናብ ምክንያቱ ክላውድ ሲዲንግ ነበር?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በሰው ሰራሽ መንገድ ደመናን ወደ ዝናብ መቀየር ወይም ‘ክላውድ ሲዲንግ’ የሚባለው፣ ቴክኖሎጂን በመጠቀምን ደመናን አጠራቅሞ ተጨማሪ ዝናብ ማግኘት ነው።

ይህንን ለማድረግም አውሮፕላኖችን በመጠቀም እንደ ‘ሲልቨር አዮዳይድ’ የመሳሰሉ ጥቃቅን ንጥረ ነገሮችን ላይ በተበታተኑ የደመና ቅንጣቶች ላይ በመበተን የሚፈጠር ሂደት ነው።

ከዚያም ደመና ተከማችቶ ወደ በረዶ ከዚያም ወደ ዝናብ የሚቀየርበት ሂደት ይፈጠራል።

ዘዴው ለአስርት ዓመታት ሲሠራበት የቆየ ሲሆን የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ያለባትን የውሃ እጥረት ችግርን ለመፍታት በቅርብ ዓመታት ውስጥ ተጠቅማበታለች።

አገሪቷ የገጠማትን የጎርፍ መጥለቅለቅ ተከትሎ በነበሩት ሰዓታት ውስጥ በማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ አስከፊው የአየር ሁኔታ የተከሰተው በቅርቡ አገሪቱ እያደረገችው ካለው ደመናን ወደ ዝናብ የመቀየር ቴክኖሎጂ (ክላውድ ሲዲንግ) ምክንያት እንደሆነ በርካቶች ተናገሩ። ይህ ግን ስህተት ነበር።

በክላውድ ሲዲንግ ላይ የተሰማሩ አውሮፕላኖች ከፍተኛው ዝናብ ከመዝነቡ በፊት በነበሩት እሁድ እና ሰኞ ዕለት ተሰማርተው የነበሩ መሆናቸውን የብሉምበርግ ዘገባ ያሳያል።

ነገር ግን ዱባይ ጎርፍ በተጥለቀለቀችበት ማክሰኞ ዕለት ክላውድ ሲዲንግ አልነበረም።

ቢቢሲ አገሪቷ ክላውድ ሲዲንግ መቼ እንዳከናወነች በገለልተኝነት ማረጋገጥ ባይችልም፤ ነገር ይህ ቴክኖሎጂ በአውሎ ንፋሱ ላይ ሊኖረው የሚችለው ተጽዕኖ መጠነኛ እንደሆነ የሚናገሩት ባለሙያዎች የከፋውን ዝናብ መንስዔ በዚህ ቴክኖሎጂ ላይ ማሳበብ “አሳሳች ነው” ይላሉ።

“ክላውድ ሲዲንግ በዱባይ ዙሪያ ያሉ ደመናዎች በረዶ እንዲያከማቹ እና ዝናብ እንዲጥሉ አስተዋጽኦ አድርጎ እንኳን ቢሆን፣ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከባቢ አየሩ የበለጠ ውሃ ተሸክሞ ደመናን መፍጠሩ የማይቀር ነው” ይላሉ ዶክተር ኦቶ።

ክላውድ ሲዲንግ አብዛኛውን ጊዜ የሚፈጸመውም ያለው የንፋስ፣ የእርጥበት እና ሌሎች የአየር ሁኔታዎች ዝናብ ለማምጣት ክምችታቸው በቂ በማይሆንበት ወቅት ነው።

ነገር ግን ባለፉት ሳምንታት በነበሩ ትንበያዎች በባሕረ ሰላጤው አገራት ከፍተኛ ጎርፍ የመጥለቅለቅ ስጋት እንዳለ አስጠንቅቀው ነበር።

“እንዲህ ቀጣናውን በሚያሰጉ ከበድ ያሉ ትንበያዎች ባሉበት ወቅት ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቀው ክላውድ ሲዲንግ ተግባራዊ አይሆንም። በእንደዚህ ሁኔታዎችም ክላውድ ሲዲንግ አስፈላጊ አይደለም” ይላሉ በአቡ ዳቢ ኸሊፋ ዩኒቨርስቲ የጂኦፊዚካል ሳይንስ ዲፓርትመንት ኃላፊ ፕሮፌሰር ዲያና ፍራንሲስ።

የቢቢሲ የአየር ሁኔታ እና ሚትዎሮሎጂ ባለሙያ ማት ቴይለር በበኩሉ የከፋ የአየር ሁኔታ በቀጣናው ሊከሰት እንደሚችል አስቀድሞ መተንበዩን ይናገራል።

“ቀጣናው በጎርፍ ከመጥለቅለቁ በፊት የኮምፒውተር ሞዴሎች ከዓመታዊ የዝናብ መጠን በላይ የሚሆን ዝናብ በ24 ሰዓታት ውስጥ እንደሚዘንብ አስቀድሞ ተንብየዋል” ይላል።

“የተከሰተው ከካድ ዝናብ ከባህሬን እስከ ኦማን ያሉ ግዛቶችን በመሸፈን የከፋ የጎርፍ አደጋ ያስከተለ ሲሆን፣ ክላውድ ሲዲንግ ሊያመጣው ከሚችለው በላይ ነው” በማለት ባለሙያው ለቢቢሲ ያስረዳል።

በተባበሩት አረብ ኤምሬት ግዛቶች ውስጥ ያሉ የክላውድ ሲዲንግ ተግባራት የሚተዳደሩት የመንግሥት ግብረ ኃይል በሆነው የብሔራዊ ሚትሮሎጂ ማዕከል (ኤንሲኤም) ነው።

ዩኤኢ ለከፋ ዝናብ ምን ያህል ተዘጋጅታ ነበር?

ከባድ ዝናብ ወደ ገዳይ ጎርፍነት እንዳይቀየር እና ድንገተኛ መጥለቅለቅ እንዳያደርስ ለመቋቋም ጠንካራ መከላከያ ያስፈልገዋል።

ዱባይ ሙሉ በሙሉ በከፍተኛ ሁኔታ ከተማ የምትባል ናት። የዝናቡን እርጥበት ለመምጠጥ ትንሸም ቢሆን አረንጓዴ ቦታ የለም፤ እንዲሁም የተዘረጋው የፍሳሽ ማስወገጃ ሥርዓት እንዲህ ያለውን ከፍተኛ የዝናብ መጠን መቋቋም አልቻለም።

“ተደጋጋሚ እና የከፋ ዝናብ ሊከሰት እንደሚችል ከአዲሱ እውነታ ጋር ለመላመድ ስልቶችን መቀየስ እና እርምጃዎች ሊኖሩ ይገባል” ሲሉ ፕሮፌሰር ፍራንሲስ ያስረዳሉ።

“ለምሳሌ የመንገዶች እና የመገልገያ መሠረተ ልማቶችን ማስተካከል፣ የበልግ የዝናብ ውሃን የሚያጠራቅሙ የውሃ ማጠራቀሚያዎችን በመገንባት በዓመቱ ውስጥ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ ያስፈልጋል” ይላሉ።

በዚህ ዓመት ጥር ወር የተባበሩት አረብ ኤምሬት (ዩኤኢ) የመንገድ እና ትራንስፖርት ባለሥልጣን በዱባይ የጎርፍ አደጋን ለመቆጣጠር የሚያግዝ አዲስ ተቋም አቋቁሟል።