በጎርፍ በተጥለቀለቀችው ኤምሬትስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ?

የተጥለቀለቀ አካባቢ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከሁለት ቀናት በፊት በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና በሌሎች አገራት አውሎ ንፋስ በቀላቀለው ከባድ ዝናብ አማካኝነት ጉዳት የደረሰበት ኢትዮጵያዊ እንደሌለ በገልፍ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለቢቢሲ ተናገሩ።

በዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ታሪክ በ75 ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ መሆኑ የተመዘገበለት ከባድ ዝናብ የጎርፍ መጥለቅለቅን አስከትሏል።

በዱባይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለቢቢሲ እንደተናገሩት በከተማዋ የጣለው ዝናብ ተሽከርካሪዎችን ጠርጎ ከመውሰድ በተጨማሪ የተለያዩ ንብረቶች ላይ ጉዳት አድርሷል። መንገዶች በጎርፍ በመጥለቅለቃቸው የሰው እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ተገድቦ ቆይቷል።

አንድ ግለሰብ መኪናው በጎርፍ በመወሰዱ ህይወቱ ማለፉ ተገልጿል።

ከሦስት ቀን በፊት የአገሪቱ መንግሥት ለሕዝቡ ባስተላለፈው የማስጠንቀቂያ መልዕክት ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፤ ሰዎችም ወደ ሥራ ቦታ እንዳይሄዱ እና ከቤት እንዲሠሩ ተደርጓል።

የጎርፍ መጥለቅለቁ በአንዳንድ ቦታዎች የከፋ ሁኔታ ማስከተሉን በረከት የተባለው ኢትዮጵያዊ የዱባይ ነዋሪ ተናግረዋል። “ሁሉም የከተማው ክፍል በጎርፍ ተጥለቅልቋል። በተለይ ዴራ የሚባለው አካባቢ ውሃው መሄጃ ስለሌለው የውሃ መጠኑ ከፍ ያለ ነው” ብሏል።

በአንጻሩ በሌሎች የዱባይ አካባቢዎች አንጻራዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን በረከት ገልጿል። ምንም እንኳ ትምህርት ቤቶች ሲሆኑ፣ ነዋሪዎችም ዛሬ ወደ ሥራ መሄድ አልጀመሩም፤ ነገር ግን የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ በብዛት መጀመሩን ተናግሯል።

ረቡዕ ዕለት የዱባይ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ መነሻ እና መድረሻ አድርገው የነበሩ 300 በረራዎች መሰረዛቸውን እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ መዘግየታቸውን ፍላይ አዌር ዳታ የተባለው የበረራ መረጃ ገልጿል።

የተጥለቀለቀ አካባቢ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከዱባይ ቀጥሎ በምትገኘው ሻርጃ ከተማ የሚኖረው አበበ የተባለ ነዋሪ እንደገለጸው ደግሞ ጎርፉ ሁሉንም አካባቢዎች በማጥለቅለቁ ያለፉትን ሦስት ቀናት ከቤት አለመውጣቱን ተናግሯል።

አብዛኛው የከተማው ክፍል አሁንም በውሃ በመሞላቱ እና ተሽከርካሪዎች መንቀሳቀስ ባለመቻላቸው ሰው ምግብ እና የዕለት መገልገያ ሸቀጦችን ለመሸመት መውጫ ማጣቱን ገልጿል።

ምድር ላይ የሚገኙ ንግድ ቤቶች አብዛኞቹ በተፈጠረው ጎርፍ በመሞላታቸው ግብይት ለመፈጸም አስቸጋሪ ነው ብሏል። በኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ የጠየቅናቸው ነዋሪዎቹ፣ እስካሁን በኢትዮጵያውያን ላይም ሆነ በሌሎች ሰዎች ላይ ጉዳት ስለመድረሱ የሰሙት ነገር አለመኖሩን ተናግረዋል።

የማቆሚያ ቦታ ላይ የነበሩ ተሽከርካሪ አብዛኞቹ እስከ ጣሪያቸው ድረስ በውሃ ተውጠው እንደነበር አቶ በረከት ተናግሯል። ብዙዎቹ መኪኖች የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ በመሆናቸው ውሃ ሲገባባቸው የመበላሸት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው። በመሆኑም ከንብረት አኳያ በርካታ ተሽከርካሪዎች ተጎድተው ሊሆን እንደሚችል እና በዚህ ጉዳት ኢትዮጵያውያንም ሰለባ ሊሆኑ እንደሚችሉ ገልጿል።

ዛሬ [ሐሙስ] ተንቀሳቅሸባቸዋለሁ ባላቸው እንደ ዱባይ ሞል እና ጁሜራ የመሳሰሉ አካባቢዎች ውሃው ሙሉ በሙሉ መወገዱን እና የሰዎች እንቅስቃሴም እየጨመረ መሆኑን ተናግሯል። በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ መንግሥት የውሃ መሳቢያ ቦቴዎችን አሰማርቶ የተጠራቀመውን ውሃ እያስመጠጠ ነው ብሏል።

ለአስር ዓመታት እንደኖረ የሚናገረው በረከት፣ እንደዚህ አይነት ዝናብ አይቶ እንደማያውቅ ተናግሯል። ዝናቡ እንደቆመ የተፈጠረው የውሃ መጠን በአብዛኛው ሰዎችን እስከ ወገባቸው ድረስ የሚያሰጥማቸው እንደነበር በረከት ተናግሯል።

የተከሰተው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ሁሉም ግዛቶች እንደሆነ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል። በመሆኑም ረቡዕ እና ማክሰኞ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ሰው ከቤት ያልወጣበት ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበር ገልጸዋል።

ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በተጨማሪ በኦማን እና ሳዑዲ አረቢያም ተመሳሳይ ሁኔታ ተፈጥሯል።

በኦማን ሳሃም በተሰኘችው አካባቢ ነፍስ አዳኞች የአንዲት ታዳጊ አስከሬን ማግኘታቸው የተገለጸ ሲሆን በዚህም በአገሪቱ ከእሁድ ጀምሮ የሞቱ ሰዎችን ቁጥር 19 አድርሶታል።

የተጥለቀለቀ አካባቢ

የፎቶው ባለመብት, Reuters