አንድ ሠራተኛ በመቀለ አይደር ሆስፒታል ውስጥ በሚሊዮኖች የሚገመት ዋጋ ባላቸው የህክምና መሳሪያዎች ላይ ጉዳት አደረሰ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በትግራይ ክልል መቀለ ከተማ የሚገኘው የአይደር ሪፈራል ሆስፒታል ባልደረባ በሚሊዮኖች የሚገመት ዋጋ ያላቸው በርካታ የህክምና መሳርያዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን የሆስፒታሉ ዳይሬክተር ዶ/ር አብርሃ ገብረግዚአብሄር ለቢቢሲ ተናገሩ።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ውድ በሆኑ የሆስፒታሉ የህክምና መሳሪያዎች ላይ በሠራተኛው አማካይነት የተፈፀመው ድርጊት ያጋጠመው ቅዳሜ መጋቢት 21/2016 ዓ.ም. ምሽት ላይ ነው።
ከሰሞኑ አንድ ግለሰብ ፊቱ በካርቶን ተሸፍኖ የህክምና መሳሪያዎችን ሲያወድም የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሲሰራጭ ሰንብቷል።
የሆስፒታሉ ሠራተኛ በህክምና መሳሪያዎቹ ላይ ለምን ጉዳት እንዳደረሰ የታወቀ ነገር የሌለ ሲሆን፣ የፖሊስ የምርመራ ውጤት እየተጠበቀ ነው።
በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ የሚታየው እና በሆስፒታሉ ውስጥ እንደተፈጸመ የተገለጸው ንብረት የማውደም ድርጊት ትክክለኛ መሆኑን ሜዲካል ዳይሬክተሩ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
“በማኅበራዊ ሚዲያ ያያችሁት አጭር ቪዲዮ የእኛ ነው፤ እውነት ነው። አመራሩ እና ሠራተኞች በሚገናኙበት በዋትስአፕ መተግበሪያ ላይ ለመረጃ ልውውጥ የተሰራጨ ነው” ሲሉ አረጋግጠዋል።
በቪዲዮው ላይ ያለው ግለሰብ የአይደር ሆስፒታል ሠራተኛ መሆኑን እና በቁጥጥር ስር መዋሉን ዶ/ር አብርሃ ለቢቢሲ ጨምረው አረጋግጠዋል።
“ግለሰቡ ተይዟል፤ ተረኛ ሠራተኞችም በምርመራ ላይ ነው የሚገኙት። እሱም እንደ አንድ ተረኛ ሠራተኛ በምርመራ ላይ ነው” በማለት ሆስፒታሉ ከፖሊስ ምላሽ እየተጠባበቀ መሆኑን ተናግረዋል።
ሠራተኛው በፈጸመው የንብረት ውድመት በሆስፒታሉ ውስጥ የሚገኙ በከፍተኛ ወጪ የሚገዙ የምርመራ እና የህክምና መሳሪያዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጿል።
የጉበት፣ የኩላሊት እጥበት፣ የሰውነት ሆርሞን መለኪያ እና የካንሰር አመላካቾች እንዲሁም በተለያዩ እንደ የልብ ህመም ያሉ ድንገተኛ ሁኔታዎች መመርመሪያዎች፣ የሆርሞኖች፣ የሰውነት ስብን መለኪያ መሳሪያዎች ከተጎዱት የሆስፒታሉ መገልገያዎች መካከል ይገኙበታል።
ሠራተኛው በፈጸመው ጥቃት ጉዳት ከደረሰባቸው የህክምና መሳሪያዎች አንዱ ለተለያዩ ምርመራዎች የሚውለው ኮባስ 6000 የሚል መጠሪያ ያለው ሲሆን፣ በትግራይ ያለው ብቸኛው እና ትልቁ የሆስፒታሉ መሳሪያ “አሁን ከአገልግሎት ውጪ ሆኗል” ብለዋል።
መሳሪያው ቀደም ብሎ በ20 ሚሊዮን ብር የተገዛ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ዋጋው 30 ሚሊዮን ብር መድረሱን ይናገራሉ።
ዳይሬክተሩ መሳሪያው ይጠገን እንደሆነ ተጠይቀው “ኬሚካሎችን በመጠቀም ነው የሚሠራው። ስለዚህ ኬሚካሎች ከአንድ ወደ ሌላው የማሽኑ ክፍል የሚተላለፉባቸው ቀጭን ቱቦዎች አሉ፤ ሁሉም ተበላሽተዋል” ብለዋል።
“የኤሌክትሮ መካኒካል ኤሌክትሪክ ሽቦው ተቆርጧል። ስለዚህ ጉዳቱ በጣም ከባድ ስለሆነ አሁን ተስተካክሎ ወደ አገልግሎት ይመለስ ወይስ በአዲስ ማሽን ይተካ እንደሆነ መልስ አላገኘንም። ተጨማሪ ምርመራዎች ይካሄዳሉ” ብለዋል።
በመሳሪያው ላይ ጉዳቱ ከደረሰ በኋላ ተረኛ ሠራተኞች በህክምና መሳሪያዎቹ ላይ ምርመራ እያካሄዱ በነበረበት ወቅት ስህተት በመፈጠሩ ተጨማሪ ፍተሻ በማድረግ የተለያዩ ችግሮችን ማግኘታቸውንም የሆስፒታሉ ዳይሬክተር ገልጸዋል።
የመቀለ አይደር ሪፈራል ሆስፒታል በክልሉ ውስጥ ትልቁ ሆስፒታል ሲሆን፣ ከተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ ህክምና ሪፈር የሚደረጉበት ነው።












