ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኔታንያሁ የእስራኤልን የጸጥታ ኃላፊን ከስልጣን አነሱ
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ መስከረም 26 ቀን 2016 ሐማስ ያደረሰውን ጥቃት ሊደርስ እንደሚችል መገመት ባለመቻላቸው የአገሪቱን የደህንነት ኃላፊ ከስልጣን አባረሩ።
የእስራኤል ካቢኔ ሐሙስ ባደረገው ስብሰባ እአአ ጥቅምት 2021 የሺን ቤት ዋና ኃላፊ ሆነው ለአምስት ዓመታት የተሾሙት ሮነን ባርን ከስልጣን መነሳታቸውን አጽድቋል።
ኔታንያሁ ባርን ከስልጣን ለማንሳት ማሰባቸው እሁድ ዕለት በቪዲዮ ባስተላለፉት መግለጫ አስታውቀዋል። በሁለቱ መካከል "የቀጠለውን ያለመተማመን በየጊዜው መስፋቱን" በምክንያትነት ጠቅሰዋል።
እርምጃው ቁጣን የቀሰቀሰ ሲሆን በእየሩሳሌም የፀረ-መንግስት ሰልፎችን የበለጠ አቀጣጥሏል። በዚህም በሺዎች የሚቆጠሩ የአገሪቱ ዜጎች እስራኤል በጋዛ ላይ የጀመረችውን አዲስ ጥቃት የተቃወሙ ሰልፈኞች ጎን ቆመዋል።
ከማክሰኞ ጀምሮ እስራኤል የሐማስ ዒላማ ባለችው የፍልስጤም ግዛት ከፍተኛ ጥቃት አድርሳለች። በዚህም ለሁለት ወራት ገደማ የዘለቀውን የተኩስ አቁም እንዲቋረጥ ሆኗል።
የሺን ቤት የእስራኤል የአገር ውስጥ የስለላ ድርጅት ሲሆን በጦርነቱ ውስጥ ቁልፍ ሚና ይጫወታል። ተግባሩ እና አባላቱ በመንግስታዊ ምስጢርነት ይያዛሉ።
ባር ከስልጣን እንዲባረሩ መወሰኑን ፖለቲካዊ ሲሉ ገልፀውታል።
ቀንደኛ የኔታንያሁ ተቺ እና ከኃላፊነታው የመባረር ሂደት የገጠማቸው የእስራኤሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጋሊ ባሃራቭ-ሚያራም የድርጊቱ ህጋዊነት እስካልተገመገመ ድረስ ባር ከስልጣን ሊባረሩ አይችሉም ሲሉ ተከራክረዋል።
ከስብሰባው በፊት ኔታንያሁ ለካቢኔያቸው አባላት በላኩት ደብዳቤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ እና በባር መካከል ያለውን "የማያቋርጥ ሙያዊ እና የግል እምነት ማጣትን" በመጥቀስ የስልጣን ዘመናቸው ከአንድ ወር በኋላ እንዲጠናቀቅ ሃሳብ አቅርበዋል።
የእስራኤል እና የጋዛ ጦርነትን የቀሰቀሰውን የሐማስ ጥቃት በመጥቀስ "መስከረም 26 ከተፈጠረው ሁኔታ በተጨማሪ ሙያዊ አመኔታ ማጣት በጦርነቱ ወቅት እና ባለፉት ጥቂት ወራት ተጠናክሯል" ብለዋል።
በጥቃቱ አንድ ሺህ 200 ሰዎች ሲገደሉ 251 ሰዎች ታግተዋል።
እስራኤል በጋዛ ውስጥ በፈጸመችው ጥቃት ከ48 ሺህ189 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ከጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።
ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ሕፃናት መሆናቸውንም በሐማስ አስተዳደር ሥር ካለው የጤና ሚኒስቴር የወጣው መረጃ አመልክቷል።
እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው የተቀናጀ እና የማያባራ ጥቃት ሁለት ሦስተኛው የጋዛ ሕንጻዎች መውደማቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።