ከ400 በላይ ፍልስጤማውያን የተገደሉበትን የጋዛ ጥቃት ገና የመጀመሪያው እንደሆነ ኔታንያሁ ተናገሩ

ከ400 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸው ሪፖርት የተደረገበትን የጋዛ ጥቃት ገና የመጀመሪያው እንደሆነ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ተናገሩ።

እስራኤል በጋዛ ሰርጥ በሐማስ ላይ "ውጊያዋን በሙሉ ኃይል ጀምራለች" ሲሉ ኔታንያሁ ማክሰኞ ምሽት፣ መጋቢት 8/ 2017 ዓ.ም ገልጸዋል።

ጥር ወር ላይ ከተደረሰው የጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት በኋላ እስራኤል የፈጸመችው ከባዱ የአየር ጥቃት ነው ተብሏል።

ጥቃቱ በተፈጸመበት ወቅት በርካቶች ለረመዳን ጾም የቀኑን የመጨረሻ ምግባቸውን እየበሉ እንደነበር የዓይን እማኞች ተናግረዋል።

በቦታው አስከሬኖች ወዳድቀው፣ የቆሰሉ ሰዎች ህክምና ለማግኘት እየተማጸኑ እንዲሁም እሳት ተቀጣጥሎ የነበረ ሲሆን፤ ሁኔታውንም አሰቃቂ ብለውታል።

ኔታንያሁ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት "ድርድሩ የሚቀጥለው በእሳት ውስጥ ብቻ ነው፤ ይህም ገና ጅምር ነው" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተያየት የተሰማው የእስራኤል ጦር በጋዛ የሃማስ ይዞታዎች ናቸው በሚል ከፍተኛ የአየር ጥቃት ከከፈተ በኋላ ነው።

የጋዛ የጤና ሚኒስቴር በዚህ ጥቃት ከ400 በላይ ሰዎች መገደላቸውን እንዲሁም በመቶዎች የሚቆጠሩ መቁሰላቸውን አስታውቋል።

ማክሰኞ ዕለት በቤት ላሂያ፣ ራፋህ፣ ኑሴይራት፣ አልማዋሲ ላይ እስራኤል የፈጸመቻቸው የአየር ጥቃቶች ከጥር ጀምሮ የነበረውን አንጻራዊ ሰላም ያደፈረሱ ሲሆን፤ ሆስፒታሎችም በድጋሜ በቆሰሉ ፍልስጤማውያን ተሞልተዋል።

የተኩስ አቁሙ አሸማጋይ የሆነችው ግብጽ ይህንን የእስራኤል ጥቃት በጽኑ አውግዛለች።

የአየር ጥቃቶቹ በተኩስ አቁም ስምምነቱ ላይ የተፈጸመ "አይን ያወጣ ጥሰት ነው" እንዲሁም "በአደገኛ መልኩ እያገረሸ መሆኑንም" ማሳያ ነው ሲሉ የሃገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ታሚም ካሊፍ ተናግረዋል።

"ጦርነቱ እንደገና በመጀመሩ በጣም ደነገጥኩ። ነገር ግን በተመሳሳይ ወቅት ከእስራኤል የምንጠብቀው ይህንን ነው" ሲል የጃባሊያ አልባላድ ነዋሪ የሆነው ሃኤል ለቢቢሲ አረብኛ ተናግሯል።

"እንደ አንድ ዜጋ ደክሞኛል። አንድ ዓመት ተኩል፤ በቅቶናል። በቂ ነው" ሲል አክሏል።

በአየር ጥቃቱ የጋዛ ምክትል የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሜጀር ጄነራል ማህሙድ አቡ ዋትፋ እንዲሁም የሐማስ ከፍተኛ የጸጥታ ባለስልጣን መገደላቸውን እስራኤል አስታውቃለች። ኔታንያሁ ባደረጉት ንግግር አገራቸው በጋዛ የታገቱ እስራኤላውያንን ለማስለቀቅ ከሐማስ ጋር ለመደራደር ሞክሯል ብለዋል።

የጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት የመጀመሪያው ምዕራፍ ከሁለት ሳምንት በፊት ተጠናቋል።

እስራኤል የመጀመሪያው ምዕራፍ የተኩስ አቁም ስምምነትን መራዘምን ሐማስ እንዲቀበል ትፈልጋለች።

ሐማስ በበኩሉ ሁሉም ታጋቾች እንዲለቀቁ እንዲሁም የእስራኤል ጦር ከጋዛ ሙሉ በሙሉ እንዲወጣ እና ዘላቂ መረጋጋትን ማምጣት ያለመው ሁለተኛው ምዕራፍ ተግባራዊ ይሁን እያለ ነው።

ሆኖም እስራኤል እና አሜሪካ ስምምነቱን በመቀየር አንደኛው ምዕራፍ እንዲራዘም እና ታጋቾች እንዲለቀቁ ለማድረግ እየሞከሩ ነው።

ይህም ማለት የእስራኤል ጦር ከጋዛ መውጣትን እንዲሁም ዘላቂ የተኩስ አቁምን የሚያዘገየው ይሆናል።

ነገር ግን በአሜሪካ፣ በኳታር እና ግብጽ አሸማጋይነት የተለወጠውን ስምምነት ተቀባይነት እንደሌለው የገለጸው ሐማስ ውድቅ አድርጎታል።

እስራኤል በተጨማሪም ባለፈው ሳምንት በመላው ጋዛ ሰርጥ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እንዲቋረጥ ትዕዛዝ ሰጥታለች።

የአገሪቱ የኃይል ሚኒስትር ሐማስ ቀሪ ታጋቾችን እንዲለቅ ጫና ለመፍጠር በሚል ይህ እርምጃ እንደተወሰደ ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ ኤሊ ኮኸን ይህንን ያስተላለፉት እስራኤል ከሁለት ሚሊዮን በላይ ህዝብ በሚኖርባት ጋዛ ማንኛውንም የእርዳታ አቅርቦት ካቋረጠች ከአንድ ሳምንት በኋላ ነው።

ሐማስ መስከረም መጨረሻ ላይ በፈጸመው ጥቃት 1200 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ 253 ሰዎች ታግተው መወሰዳቸው ይታወሳል።

እስራኤል በጋዛ ውስጥ በፈጸመችው ጥቃት ከ48 ሺህ189 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ከጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ሕፃናት መሆናቸውንም በሐማስ አስተዳደር ሥር ካለው የጤና ሚኒስቴር የወጣው መረጃ አመልክቷል።

እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው የተቀናጀ እና የማያባራ ጥቃት ሁለት ሦስተኛው የጋዛ ሕንጻዎች መውደማቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።