ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በእርቃን ፎቶዎች በማስፈራራት ለአንድ ታዳጊ ሞት ምክንያት የሆነው ናይጄሪያዊ ለአሜሪካ ተላልፎ ተሰጠ
አንድን አሜሪካዊ ታዳጊ እርቃን ፎቶዎችን እንዲልክ በማታለል እና ገንዝብ ካልከፈለ ለአደባባይ እንደሚያውላቸው በማስፈራራት ለሞቱ ምክንያት እንደሆነ የተጠረጠረ ናይጄሪያዊ ለአሜሪካ ተላልፎ ተሰጠ።
የናይጄሪያው ኦሱን ግዛት ነዋሪ የሆነው የ24 ዓመቱ ሃሰንቡንሁሴን አቦሎር ላዋል፣ ከናይጄሪያ መንግሥት ጋር ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ ባለፈው ቅዳሜ ለአሜሪካ መንግሥት ተላልፎ ተሰጥቶ ወደ ዚያው መወሰዱ ተዘግቧል።
ግለሰቡ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ የሞት ላይፈረድበት ቢችልም በአስርት ዓመታት የሚቆጠር የእስር ቅጣት ይጠብቀዋል ተብሏል።
ላዋል ሰኞ ዕለት ብርቱካናማ ቀለም ያለው የእስረኞች ዩኒፎርም ለብሶ፣ እግሩ እና እጁ በሰንሰለት ታስሮ በደቡብ ካሮላይና፣ ኮሎምቢያ በሚገኘው የፌደራል ፍርድ ቤት መቅረቡን የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ግለሰቡ ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት ሞት ያስከተለውን የታዳጊውን ብዝበዛ ጨምሮ የሕፃናት ወሲባዊ ጥቃትን የሚያሳዩ ምሥሎችን በማዘጋጀት እና በማሠራጨት የቀረቡበትን ክሶች "ጥፋተኛ አይደለሁም" ሲል ተከራክሯል።
ናይጄሪያ ግለሰቡን አሳልፋ እንድትሰጥ ያደረገው ይህ የወንጀል ምርመራ የተጀመረው አሜሪካዊው የ17 ዓመቱ ታዳጊ ጋቪን ጉፌይ በግለሰቡ ዒላማ ከሆነ በኋላ ራሱን ማጥፋቱን ተከትሎ ነበር።
ተከሳሹ ግለሰብ በማኅበራዊ ሚዲያ ወጣት ሴት መስሎ በመቅረብ እና ታዳጊውን በማታለል ያልተገቡ ፎቶዎችን እንዲልክ አድርጓል።
ከዚያም ገንዘብ ካልከፈለ በስተቀር ፎቶዎቹን እንደሚያሠራጭ እንዲሁም ስሙን እንደሚያጠፋው በተደጋጋሚ መልዕክቶችን በመላክ ሲያስፈራራው እንደነበርም ተገልጿል።
ናይጄሪያዊው ላዋል በኋላ ላይ በተጠቂው ታዳጊ ቤተሰቦች ላይም ተመሳሳይ ድርጊት ፈፅሟል ተብሏል።
በአሜሪካ የሕፃናት ወሲባዊ ብዝብዛ ክስ ቢያንስ በ30 ዓመታት እስር ያስቀጣል። የዋስትና መብትም አያሰጥም።
ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን ለመመልከት ለቀጣይ ሰኞ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ድርጊት ሰለባ ከሆነ በኋላ ራሱን ያጠፋው ብሪታኒያዊ ታዳጊ ወላጆች ድርጊቱን የሚፈፅሙ በናይጄሪያ የሚገኙ ወንጀለኞች ተጋላጭ የሆኑ ሕፃናትን 'ማሸበር' እንዲያቆሙ ተማፅነው ነበር።
የደንብሌን ነዋሪ የሆነው ልጃቸው ሙራይ ዶዊይ ባለፈው ዓመት ሕይወቱ ሲያልፍ የ16 ዓመት ታዳጊ ነበር።
ታዳጊው በወንጀለኞች በመታለል እርቃን ፎቶዎቹን ከላከ በኋላ ገንዘብ እንዲከፍል ሲጠየቅ እንደነበር ይታመናል።
በአውሮፓውያኑ 2024 መስከረም ላይም የ17 ዓመት ታዳጊን ግላዊ ፎቶ አታሎ በመውሰድ እና ገንዘብ እንዲከፍል ሲያስፈራሩ የነበሩ የናይጄሪያ ዜጋ የሆኑ ሁለት ወንድማማቾች በአሜሪካ የ17 ዓመት ከስድስት ወር እስራት ተፈርዶባቸዋል።
ይህም ግላዊ ወይም እርቃን ፎቶዎችን አታሎ በመውሰድ ገንዘብ እንዲከፍሉ በማስፈራራት ጥቃት የሚፈፅሙ ናይጄሪያውያን ላይ የተሳካ ከባድ ቅጣት ሲተላለፍ ይህ የመጀመሪያው ሆኗል።
የኢንስታግራም ባለቤት ሜታ በበኩሉ በናይጄሪያ በርካታ ሰዎችን ለተመሳሳይ ድርጊት ዒላማ ለማድረግ ሲሞክሩ የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ገጾችን ማጥፋቱን ገልጿል።
የናይጄሪያ ብሔራዊ የሳይበር ወንጀል ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ኡቼ ኢፌንይ ሄንሪ ቀደም ብሎ የናይጄሪያ መንግሥት መሰል የሳይበር ወንጀሎችን ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሆነ ለማሳየት ዘመናዊ የሳይበር ወንጀል ማዕከል ለመግንባት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ፓውንዶችን ማውጣቱን ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።