ትራምፕ እና የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ በደቡብ ኮሪያ ሊገናኙ ነው

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጥቅምት 30 በእስያ ከሚካሄደው ጉባኤ ጎን ለጎን ከቻይናው አቻቸው ዢ ጂንፒንግ ጋር በደቡብ ኮሪያ ይገናኛሉ ሲል ዋይት ሐውስ አረጋገጠ።

የዢ እና ትራምፕ ስብሰባ ለሳምንታት ዝግጅት ሲደረግበት ቢቆይም ግን በሁለቱ የግዙፍ ምጣኔ ኃብት ባለቤቶች መካከል ያለው ውጥረት እየጨመረ በመምጣቱ ጥያቄ ውስጥ ገብቶ ቆይቷል።

ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከተመለሱ በኋላ በሁለቱ መሪዎች መካከል የሚደረግ የመጀመሪያው የፊት ለፊት ግንኙነት ይሆናል።

ትራምፕ ቻይና ብርቅዬ የማዕድናት ኤክስፖርት ላይ የጣለችውን ጥብቅ ገደቦችን ካላነሳች ትራምፕ ከህዳር ወር ጀምሮ በቻይና ምርቶች ላይ 100% ተጨማሪ ታሪፍ እንደሚጥሉ አስፈራርተዋል።

የዋይት ሐውስ የፕሬስ ፀሐፊ ካሮሊን ሊቪት ሐሙስ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በሁለቱ መሪዎች መካከል ያለውን ስብሰባ እንደሚካሄድ አረጋግጠዋል።

የሁለትዮሽ ስብሰባው ከጥቅምት 31 እስከ ሕዳር 1 በደቡብ ኮሪያ ጂዮንግጁ ከሚካሄደው የእስያ ፓስፊክ የኢኮኖሚ ትብብር ጉባኤ (አፔክ) ጎን ለጎን ይካሄዳል።

"ከቻይና ፕሬዝዳንት ዢ ጋር እገናኛለሁ። ረጅም ጊዜ የሚወስድ ስብሰባ አለን። ብዙ ጥርጣሬዎቻችንን፣ ጥያቄዎቻችንን እና አስደናቂ ሃብቶቻችንን በጋራ መፍታት እንችላለን" ሲሉ ትራምፕ ቀደም ብለው ተናግረዋል።

"አንድ ነገር እንደሚሳካ አስባለሁ። በጣም ጥሩ ግንኙነት አለን፣ ያም ትልቅ ይሆናል።"

ትራምፕ ወደ ደቡብ ኮሪያ በሚያደርጉት ጉዞ የአገሪቱን መሪ ሊ ጄ ማዩንግን ከማግኘት በተጨማሪ ለመሪዎች በሚዘጋጀው የእራት ግብዣ ለመሳተፍ ተዘጋጅተዋል።

ትራምፕ ወደ እስያ በሚያደርጉት ጉዞ እሑድ ዕለት በማሌዥያ በሚካሄደው የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገራት ማህበር (አሴያን) ጉባኤ ላይ ለአጭር ጊዜ ይሳተፋሉ።

ከማሌዥያ፣ ከደቡብ ኮሪያ እና ከጃፓን መሪዎች ጋርም ይገናኛሉ። በተለይም ከአዲሷ የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሳና ታኪቺ ጋር ይገናኛሉ ሲሉ የዋይት ሐውስ የፕሬስ ፀሐፊ ተናግረዋል።

ትራምፕ እና ዢ በዚህ ዓመት ቢያንስ ለሦስት ጊዜ ተነጋግረዋል። በተለይም በመስከረም ወር ባደረጉት ንግግር በቲክ ቶክ በአሜሪካ ውስጥ ስላለው እንቅስቃሴ ከስምምነት ደርሰዋል።

ለመጨረሻ ጊዜ ፊት ለፊት የተገናኙት በ2019 በትራምፕ የመጀመሪያ የፕሬዚዳንትነት ዘመን ነበር።

ትራምፕ ከዢ ጋር በቀጥታ መነጋገር በአሜሪካ እና ቻይና መካከል እንደ ታሪፍ፣ የንግድ አለመግባባቶች፣ የፌንታኒል ዝውውር እና ሌሎች ጉዳዮች ያሉ ቀጣይ ውጥረቶችን ለመፍታት በጣም ውጤታማው መንገድ እንደሆነ ተናግረዋል።

አሜሪካ እና ቻይና በግንቦት ወር የተካሄደውን የንግድ ስምምነት አጥብቀው በመያዝ በሁለቱም አገራት መካከል ስጋት የፈጠሩትን የሦስት አሃዝ ታሪፍ ዛቻዎች ማስቀረት ችለዋል።

በጥቅምት ወር ግን ቻይና ብርቅዬ ማዕድናት ላይ የኤክስፖርት ቁጥጥሯን አጠናክራለች። ይህም ትራምፕ በቻይና ምርቶች ላይ ተጨማሪ 100% ታሪፍ ለመጣል እንዲያስፈራሩ መንገድ ከፍቷል። በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍም፣ ቤጂንግን ዓለምን "በምርኮ" ለመያዝ እና "በጣም ጠላት" ሆናለች በማለት በመክሰስ ተችተዋል።

ትራምፕ አክለውም በቀጣዩ ስብሰባ እንደማይሳተፉ አስፈራርተዋል።

ቻይና ብርቅዬ ማዕደእናትን እና ሌሎች ቁልፍ ቁሳቁሶችን በማምረት ላይ ትገኛለች። እነዚህም በመኪናዎች፣ በስማርት ስልኮች እና በሌሎች በርካታ ምርቶች ውስጥ ቁልፍ ናቸው።