ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፖሊስ ከ100 በላይ ሐሰተኛ መረጃን ያሰራጫሉ ያላቸውን መለየቱንና የተወሰኑትን መያዙን ገለጸ
የኢትዮጵያ ፌደራል ከአንድ መቶ በላይ የሚሆኑ የበይነ መረብ የመገናኛ ብዙኃን መድረኮች የጥላቻ እና ሐሰተኛ መረጃን እያሰራጩ ነው በማለት ሲከስ አስሩን ደግሞ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገለጸ።
የፌደራል ፖሊስ ዛሬ ረቡዕ ግንቦት 24/2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ላይ “የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት የሚያናጉ፣ በብሔር እና በሃይማኖት ጉዳዮች ላይ ግጭት ቀስቃሽ መረጃ የሚያሰራጩ እንዲሁም በሐሰተኛ ፕሮፓጋንዳ የሚያሰራጩ” ያላቸውን 111 የበይነመረብ መገናኛ ብዙኃን መለየቱን አመልክቷል።
ፖሊስ ለየኋቸው ካላቸው 111 የበይነ መረብ ሚዲያዎች ውስጥ “ብሔርን ከብሔር ሃይማኖትን ከሃይማኖት በማጋጨት የአገርን ሰላምና ደኅንነት ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ ናቸው” ያላቸውን አስሩን ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያደረገ መሆኑን ገልጿል።
ይህ የፖሊስ መግለጫ የወጣው ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ 18 የሚደርሱ ጋዜጠኞችና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ለእስር ከተዳረጉ በኋላ ሲሆን፣ ይህ የፀጥታ ኃይሎች እርምጃም በሰብአዊ መብትና በጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪዎች ዘንድ ስጋትን ፈጥሯል።
ፖሊስ አሰባሰብኩት ባለው መረጃ የተጠቀሱት የበይነ መረብ የመገናኛ ብዙኃን መድረኮች ምንም አይነት ፈቃድ የሌላቸው የጥላቻና ሐሰተኛ መረጃን የሚያሰራጩ ናቸው ብሏል።
የፖሊስ ቃል አቀባይ ኮማንደር ፋሲካ ፈንታ በመገናኛ ብዙኃኑ መድረኮች ላይ የሚካሄደው ምርመራ ገና ያልተጠናቀቀ በመሆኑ ማንነታቸውን ለመግለጽ እንደማይችሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ፖሊስ በመግለጫው በበይነ መረብ መገናኛ መድረኮቹ ላይ ባደረገው ክትትል “ምንም አይነት ህጋዊ ፍቃድ የሌላቸውና በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 መሰረት ያልተመዘገቡ” መሆናቸውን ከኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን ማረጋገጡም ገልጿል።
የአማራ ክልል ሕግ የማስከበር ዘመቻ በሚል ከሁለት ሳምንት በፊት ጀምሮ በክልሉ ውስጥ እየወሰደ ካለው እርምጃ ጋር በተያያዘ በባሕር ዳር በሁለት የተለያዩ የበይነ መረብ መድረኮች ላይ የሚሰሩ ዘጠኝ የሚደረሱ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል።
በማስከተልም በአዲስ አበባ ውስጥ የፍትህ መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር የሆነውን ተመስገን ደሳለኝን ጨምሮ በርካታ በተለያዩ የበይነ መይነ መረብ መድረኮች ላይ የሚሰሩ ጋዜጠኞች በፖሊስ ተይዘው በእስር ላይ ይገኛሉ።
በዚህም ባለፉት ሁለት ሳምንታት በአጠቃላይ 18 የሚሆኑ ጋዜጠኞችና የመገናኛ ብዙኃን ሙያተኞች ፍርድ ቤት ቀርበው ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል።
ይህንን ተከትሎ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እንዲሁም የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪው ሲፒጄ እስሩ እንዳሳሰባቸው ባለፈው ሳምንት ባወጡት መግለጫዎች አመልክተዋል::
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ላይ የተፈፀመው እስር በተለይ አሳሳቢ የሚሆንበት ምክንያት ከሚዲያ ሕግ በተቃራኒ መሆኑ ሳይሆን፣ የሚያስከትለው ውጤት ከመገናኛ ብዙኃንና ሐሳብን በነጻነት ከመግለጽ ባሻገር ስለሚሰፋ ነው” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ኮሚሽነሩ ጨምረውም ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የሚፈፀም እስር እንዲሁም ተጠርጣሪዎች ከታሰሩ በኋላ የት እንደሚገኙ በይፍ አለማሳወቅ መበራከቱን ተችተው፣ ሁሉም ጋዜጠኞችና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በአፋጣኝ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል።
ዋና ኮሚሽነሩ በተጨማሪም “በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት ተፈፅመዋል የተባሉት ወንጀሎች ምንም ይሁኑ ምንም፣ አዲስ የተረቀቀውን የሚዲያ ሕግ ለመጻረር ሰበብ መሆን አይገባቸውም። ሕጉ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ማሰርን በግልጽ ይከለክላል” ብለዋል።