ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፕሬዝደንታዊ ዕጩዎቹ ከልጅነት እስከ ዕውቀት - ከዚህ ቀደም ያልታዩ የሃሪስ እና የትራምፕ ፎቶዎች
የአሜሪካ ምርጫ ሲቃረብ መራጮች በዕጩዎች ፎቶ ይጨናነቃሉ። ዕጩዎች የምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርጉ፤ ደጋፊዎቻቸውን ሲጨብጡ፤ አውሮፕላን ሲሳፈሩ እና ሲወርዱ።
ነገር ግን የብዙዎቹ ዕጩዎች የቀድሞ ፎቶዎች ብዙም ብቅ ሲሉ አይታዩም።
ከላይ የሚታዩት ዶናልድ ትራምፕ እና ካማላ ሃሪስ ዋይት ሐውስ ምን እንደሆነ እንኳ ሳያውቁ በፊት በሦስት ዓመታቸው የተነሷቸው ፎቶዎች ናቸው።
እነሆ በርካታ አስርት ዓመታት አልፈው ዲሞክራቷ ዕጩ ፕሬዝደንት ካማላ ሃሪስ እና ዶናልድ ትራምፕ ተፋጠዋል።
ካማላ ልጅነታቸውን ያሳለፉት በካሊፎርኒያ ግዛት ኦክላንድ ከተማ ነው፤ ትራምፕ ደግሞ በኒው ዮርክ ግዛት ኩዊንስ ነው ያደጉት።
ሃሪስ እና እህታቸው ማያ የካንሰር ጥናት ባለሙያ እና የማኅበረሰብ አንቂ በሆኑት ሕንዳዊት እናታቸው ሺያማላ ጎፓላን ሃሪስ እንክብካቤ ነው ያደጉት።
የትራምፕ አባት ፍሬድ ትራምፕ ደግሞ የጀመርን ስደተኞች ልጅ ሲሆኑ፣ እናታቸው ማሪ አን ትራምፕ ደግሞ ስኮትላንድ ነው የተወለዱት።
ትራምፕ በ13 ዓመታቸው የኒው ዮርክ ወደ ሚገኘው ወታደራዊ አካዳሚ ገብተዋል።
ሃሪስ በካናዳ ሞንትሪያል ግዛት ለ5 ዓመታት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምረዋል። እናታቸው ማክጊል ዩኒቨርሲቲ ለማስተማር ሲሉ ነው ልጆቻቸውን ይዘው ወደ ካናዳ ያቀኑት።
የኮሌጅ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በአብዛኛው የጥቁሮች ነው በሚባለው ዋሺንግተን በሚገኘው ሀዋርድ ዩኒቨርሲቲ ነው።
ትራምፕ ከዚህ ቀደም ሲናገሩ እንደተደመጡት ከአውሮፓውያኑ 1959 ጀምሮ በወታደራዊ አካዳሚው ያሳለፏቸው እምስት ዓመታት ወታደዊ እና የአመራር ክህሎት እንዲያዳብሩ አድርጓቸዋል።
ትራምፕ ወደ ቪየትናም ጦርነት ሳይዘምቱ የቀሩት አጥንታቸው ላይ በነበረ ችግር ምክንያት መሆኑ ይነገራል።
ሃሪስ ገና ከልጅነታቸው ነው የሲቪል መብቶችን እንቅስቃሴን ከእናታቸው ጎን ሆነው ሲከታተሉ ያደጉት። በየዓመቱ የማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር የነፃነት ቀን ሲከበር ቀርተው አያውቁም።
ከፔንሲልቬኒያ ዋርተን ስኩል ድግሪያቸውን ያገኙት ትራምፕ አባታቸውን ተክተው የቤተሰቡን ግዙፍ ሀብት እንደሚያስተዳድሩ ተስፋ የተጣለባቸው ከታላቅ ወንድማቸው ሞት በኋላ ነው።
ሃሪስ ወደ ካሊፎርኒያ ተመልሰው በግዛቷ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ውስጥ እያደጉ መጡ። የካሊፎርኒያ ዐቃቤ ሕግ ሳሉ ነው በአውሮፓውያኑ 2016 በተደረገው ምርጫ የሴኔት ተወካይ ለመሆን ተወዳድረው ያሸነፉት።
እሳቸው ኮንግረስ ሲገቡ ትራምፕ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ፕሬዝደንት ለመሆን እየተፎካከሩ ነበር። ያሸንፋሉ የሚል ትልቅ ግምት ያልተሰጣቸው ትራምፕ ሂላሪ ክሊንተንን በመርታት ነበር ወደ ዋይት ሐውስ አቀኑ።
ከሦስት ዓመታት በኋላ ሃሪስ ምክትል ፕሬዝደንት ሆነው እንዲወዳደሩ በወቅቱ ፕሬዝደንት በጆ ባይደን ተመረጡ። ሁለቱ ተጣምረው ትራምፕ እና ማይክ ፔንስን በመርታት ዋይት ሐውስን ተረከቡ።
የትራምፕ የምርጫ ዘመን ማብቂያ እና የባይደን እና ሃሪስ የመጀመሪያዎቹ ዓመታት በኮቪድ ወረርሽኝ እና በተለያዩ አመፆች የታጀቡ ነበሩ።
በተለይ በሚኒያፖሊስ ፖሊስ ጆርጅ ፍሎይድ የተባለ ጥቁር አሜሪካዊ መግደሉን ተከትሎ በመላው አሜሪካ ከባድ አመፅ ተቀስቅሶ ነበር።
ሃሪስ ምክትል ፕሬዝደንት ሆነው ተፅዕኖ ለመፍጠር ተቸግረው ነበር። ነገር ግን ጎልተው መውጣት የቻሉት በ2022 የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሕገ-መንግሥታዊው ፅንስ የማቋረጥ መብትን ሲከለክል ነው።
ፕሬዝደንት ባይደን ፅንስ የማቋረጥ መብትን በተመለከተ የዋይት ሐውስን ዘመቻ እንዲመሩ ምክትላቸው ሃሪስን ወደፊት ማምጣት ጀመሩ።
የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች በአብዛኛው ወግ አጥባቂ እንዲሆኑ መንገድ የጠረጉት ትራምፕ ናቸው። ይህ ደግሞ ፍርድ ቤቱ ፅንስ ማቋረጥን በተለመከተ ጠበቅ ያለ አቋም እንዲይዝ አድርጎታል።
ትራምፕ በፕሬዝደንታዊ ጽህፈት ቤት (ኦቫል ኦፊስ) ቆይታቸው ከፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ራሳቸው ያገለሉ ሲሆን የስደተኞች ቁጥር እንዲቀንስም ሲጥሩ ቆይተዋል።
ሃሪስ ምክትል ፕሬዝደንት ሆነው ለመጀመሪያ ጊዜ የተጓዙት ወደ ጓቲማላ ነው። ወደዚያ ያቀኑት ሜክሲኮን ተጠቅመው ከላቲን አሜሪካ በደቡባዊ የአሜሪካ ድንበር በኩል የሚመጡ ስደተኞችን ጉዳይ አንድ ለማለት ነው።
እሳቸው ምክትል ፕሬዝደንት ሳሉ በዩክሬን እና ጋዛ ውስጥ ጦርነት ተቀስቅሷል። የዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮች ከአፍጋኒስታን ነቅለው የወጡትም በባይደን ዘመነ መንግሥት ነው።
ትራምፕ ሥልጣና ከያዙ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋዊ ጉብኝት ያደረጉት በሳዑዲ አረቢያ ነው።
ትራምፕ የሚከተሉት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አሜሪካ በሌሎች ሀገራት ጦርነት ውስጥ እጇን ከማስገባት እንድትቆጠብ የሚሰብክ ነው።
የሃሪስ ባል ዳግ ኤምሆፍ ይባላል። ዳግ ሚስታቸውን ወክለው በተለያዩ አካባቢዎች የምርጫ ቅስቀሳ በማድረግ ላይ ናቸው።
ኤምሆፍ ከጀመሪያ ትዳራቸው ሁለት ልጆች ያፈሩ ሲሆን፣ አሁን ከሃሪስ ጋር ይኖራሉ። ልጆቻቸው ኮል እና ኤላ ይባላሉ።
የዶናልድ ትራምፕ ቤተሰብ አባላት በፖለቲካ ሕይወታቸው ውስጥ ትልቅ ሚና አላቸው። የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ትራምፕ ግን በ2024 የምርጫ ቅስቀሳቸው ብዙም ሲሳተፉ አልተስተዋሉም።
ትራምፕ ከመጀመሪያ ሚስታቸው ኢቫና ሦስት ልጆች አሏቸው። ዶናልድ ጁኒዬር፣ ኢቫንካ እና ኤሪክ። ከሁለተኛ ሚስታቸው ደግሞ ቲፋኒን አፍርተዋል። ትራምፕ ከአሁኗ ሚስታቸው ሜላኒያ አንድ ወንድ ልጅ አላቸው።
ሃሪስ የ2024 የአሜሪካ ምርጫን የተቀላቀሉት አርፍደው ነው። ፕሬዝደንት ባይደን ራሳቸውን ከምርጫው በማግለላቸው ነው ዲሞክራቲክ ፓርቲ እሳቸውን ያጨው።
በዚህም የመጀመሪያዋ ጥቁር እና እስያዊት-አሜሪካዊት ሴት ዕጩ ፕሬዝደንት በመሆን በታሪክ ተመዝግበዋል።
ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ ለሦስተኛ ጊዜ ከፓርቲያቸው ዕጩነት በማግኘት ነው እየተወዳደሩ ያሉት። ይህ ብዙም አልተለመደም።
ትራምፕ ዕጩነታቸውን የተቀበሉት የግድያ ሙከራ በተደረገባቸው ሰሞን ስለነበር ጆሯቸውን በፋሻ ጠቅልለው ነበር በሪፐብሊካኖች ጉባኤ ላይ የቀረቡት።